Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 16 June 2012 12:27

የሥልጣን ሽግግር - ያለግርግር! ሌሴቶ ከ50 ዓመት በኋላ ታሪክ ሰራች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በደቡብ አፍሪካ የተከበበችው ወደብ አልባዋ ትንሿ ሌሴቶ ከብሪቲሽ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች ግማሽ ክ/ዘመን ብታስቆጥርም አንድም ጊዜ እንኳን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አድርጋ አታውቅም፡፡ አሁን ግን ተሳክቶላታል ብሏል - ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት፡፡ ባለፈው ጁን 8/2012 ዓ.ም የአገሪቱ ንጉስ የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በሌሴቶ ትልቁ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑትን የ72 ዓመቱን ቶማስ ታባኔ ቃለ መሃላ አስገብተዋል - በጠ/ሚኒስትርነት አገሪቱን እንዲመሩ፡፡ ቶማስ ታባኔ የጥምር መንግሥት የሚመሩ ሲሆን የእሳቸውን “All Basotho convention” ፓርቲ ጨምሮ በአጠቃላይ ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጥምር መንግሥቱ ውስጥ እንደሚካተቱ ታውቋል፡፡ የቀሩት ሁለቱ ፓርቲዎች “Lesotho Congress For Democracy” እና “Basotho National Party” መሆናቸውን ኢኮኖሚስት ጠቅሷል፡፡

ሜይ 26/2012 ዓ.ም በአገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ውጥረት ነግሶ መቆየቱን ያስታወሰው መፅሄቱ፤ በምርጫው ትልቅ ነጥብ ይዞ የወጣው የፓካሊታ ሞሲሲሊ “Congress party” ቢሆንም መንግሥት ለመመስረት የሚያበቃ አብላጫ መቀመጫ ሳያገኝ እንደቀረ ይጠቁማል፡፡ ከአራት አስጨናቂ ቀናት በኋላ ሚ/ር ሞሲሲሊ ሳይወዱ በግድ ወደ አገሪቱ ንጉስ ጋ በመቅረብ ለ14 አመታት ከቆዩበት ሥልጣናቸው እንዲለቁ ጥያቄ ያቀርቡላቸዋል፡፡ ንጉሱ ከስልጣን መልቀቁን አሻፈረኝ ይሉና ለ67 አመቱ ጠ/ሚኒስትራቸው ሌላ ሃሳብ ያቀርባሉ - የጥምር መንግሥት ለመመስረት ሞክር የሚል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይት ሲያደርጉ በነበሩባቸው ቀጣዮቹ ቀናት በሌሴቶ እንደተለመደው የድህረ ምርጫ ረብሻዎች ይፈጠራሉ የሚል ከፍተኛ ስጋት አረብቦ ነበር፡፡ ባስ ካለም እንደ 1994 ዓ.ም ዓይነት ኩዴታ ሊከሰት ይችል ነበር፡፡ ሆኖም ተአምራዊ በሚያስብል ሁኔታ በቅድመ ምርጫ ወቅት ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ ቃል የተገባቡት ሁሉም ፓርቲዎች ለመገንፈል በስሜት ሲናጡ የነበሩትን ደጋፊዎቻቸውን ማረጋጋት ቻሉ፡፡ በመጨረሻም ጁን 7/ 2012 ዓ.ም ከእሳቸው ጋር በጥምረት መንግስት ለመመስረት የሚሻ አንድም ፓርቲ ያላገኙት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ሞሲሲሊ ከስልጣን ለመውረድ ተስማሙ፡፡

ሞሲሲሊ ክብርና ሞገሳቸውን እንደጠበቁ ሥልጣን በማስረከባቸውም አያሌ ተቺዎቻቸው እንደተገረሙባቸው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ጠቁሟል፡፡ ምንም እንኳን በረዥሙ የአገዛዝ ዘመናቸው ማብቂያ ላይ ተወዳጅ ያልነበሩ ቢሆንም በድህነት በተጐሳቆለችው ውብ አገራቸው ላይ ትምህርት፣ ጤናና የዲሞክራቲክ መብቶችን በማስፋፋት በቅጡ መምራት የቻሉ መሪ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል - ፓካሊታ ሞሲሲሊ፡፡

በቅርቡ ይፋ በተደረገውና የአፍሪካ አገራትን መልካም አስተዳደር በሚመዝነው “የኢብራሂም ኢንዴክስ” ከ53 አገራት 8ኛ ደረጃን በማግኘት አድናቆት አትርፋለች - 2ሚ. ህዝብ ያላት ሌሴቶ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሞሲሲሊ በአገራቸው ህዝብ ዘንድ ተወዳጅ እንዳልነበሩ መካድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን በምዕራባውያን ለጋሶች ዘንድ ደግሞ ተወዳጅ ነበሩ - የሌሴቶው የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር፡፡

ለፖለቲካ ቀውስና አለመረጋጋት ዘወትር የተጋለጠች በሆነችው ሌሴቶ፤ ሁሉን ያስደመመና ያስደነቀ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መደረግ መቻሉ የሞሲሲሊን ስምና ታሪክ የበለጠ ያደምቀዋል ብሏል - ዘ ኢኮኖሚስት፡፡

 

 

Read 3211 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 12:32