Print this page
Saturday, 05 October 2019 00:00

የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ‹‹መደመር›› መጽሐፍ በቅርቡ ለንባብ ይበቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተጻፈው መደመርን ከፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እንዲሁም ከውጭ ግንኙነት አንጻር በስፋት የሚተነትነው “መደመር” የተሰኘ መጽሐፍ በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ለንባብ ይበቃል ተብሏል፡፡  
ዶ/ር ዐቢይ ጠ/ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት ጀምሮ የመደመር እሳቤን ጥናትና ምርምር ሲያዳብሩት መቆየታቸውንና ይህን አጠቃላይ የመደመር እሳቤን ያስረዳል ያሉትን መጽሐፍ አዘጋጅተው እንዳጠናቀቁ፣ ምሁራንና ፖለቲከኞችም በመጽሐፉ ላይ ውይይት አድርገው ጽንሰ ሀሳቡን የማዳበር ሥራ እየተከናወነ  መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡   
መጽሐፉ በመጀመሪያዎቹ ምዕራፍ የመደመርን አጠቃላይ ጽንሰ ሀሳብ በስፋት የሚተነትን ሲሆን በሁለተኛ ክፍሉ መደመርን ከፖለቲካ አስተሳሰብ አንጻር፣ በሌላኛው ክፍሉ መደመርን ከኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንዲሁም መደመርን ከውጭ ግንኙነት መርሆዎችና ስትራቴጂዎች አንጻር እንደሚተነትን ተጠቁሟል::  
የመደመር የመጨረሻ ግቡ፤ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር፣ የዜጎችን ክብርና ብልጽግና ማረጋገጥ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በመላው አለም ተከብረው የሚኖሩበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ በመጽሐፉ ተጠቅሷል፡፡ የመደመር እሳቤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በቀጣይ ለመምራት ያስችላል ብለው ያቀረቡት ፍኖተ ካርታ እንደሆነም ታውቋል፡፡ በመደመር እሳቤ ላይም ታዋቂ አለማቀፍ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ምሁራንን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን እየተወያዩበት መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡   

Read 1537 times