Print this page
Saturday, 05 October 2019 00:00

“ህብር ኢትዮጵያ” አስቸኳይ የእርቀ ሠላም ጉባኤ እንዲካሄድ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


                             “የሀገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች ከጥላቻ መጠላለፍ መውጣት አለባቸው”


          ከመጪው አገራዊ  ምርጫ በፊት ሁሉም የፖለቲካ መድረክ ተሳታፊዎች ከጥላቻና ከመጠላለፍ የእልህ ፖለቲካ እንዲወጡ ጥሪ ያስተላለፈው “ህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ”፤ በአገሪቱ አስቸኳይ የእርቀ ሠላም ጉባኤ እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች ከ5 ወራት በፊት ተዋህደው የመሠረቱት “ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ”፣ ከትናንት በስቲያ (ሐሙስ) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ፤ ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት ሊከናወኑ ይገባል ያላቸውን አንኳር ጉዳዮች አስታውቋል፡፡  
“የጥላቻና የመጠላለፍ የእልህ ፖለቲካ ይቁም” በሚል ርዕስ መግለጫውን ይፋ ያደረገው  ፓርቲው፤ በተለይ የለውጥ ሃይሉና ሌሎች በስልጣን ላይ ያሉ ሃይሎች፣ እርስ በእርስ ከመገፋፋትና ከመወነጃጀል ወጥተው፣ ለሀገር ሠላምና የፖለቲካ መቃናት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከዚህ ቀደም ሀገሪቷ ያጋጠሟት የለውጥ ተስፋዎች በፖለቲካ ሃይሎች የእርስ በእርስ መገፋፋት ተደነቃቅፈው መቅረታቸውን ያስታወሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ዘለቀ ረዲ፤ አሁን ያለው የለውጥ ሃይልም እርስ በእርስ ከመገፋፋት ራሱን ካልገታ ለውጡን ሊያደናቅፈው ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡  
በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የደህንነት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ያስታወቀው ፓርቲው፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ  ወደ ምርጫ ለመግባት የሚደረገው ጥድፊያ ሀገር ከማፍረስ የዘለለ ሚና ሊኖረውም አይችልም ብሏል፡፡ ምርጫውን በተጣደፈ ጊዜ ውስጥ ማካሄድ የሚለውን ሃሳብ እንደማይደግፍ ያስታወቀው ህብር ኢትዮጵያ፤ ከምርጫው በፊት የሀገሪቱን ደህንነት አስተማማኝ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወን አለባቸው ብሏል፡፡
ቀጣዩን ምርጫ የሚወስኑ ህጐችንና አዋጆችን የማዘጋጀት ሂደት የሁሉንም ወገን መግባባት በሚያሟላ መልኩ እንዲካሄድና በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት የፀደቁ ውሣኔዎች ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚገባም ጠቁሟል:: በሀገሪቱ የተከሰቱ የፖለቲካ ቅራኔዎች የፈጠሯቸውን የእርስ በርስ አለመተማመኖች፣ አስቸኳይ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉባኤ በማዘጋጀት፣ ከምርጫው በፊት መፍታት እንደሚያስፈልግም  አሳስቧል፡፡
ከፖለቲካዊ ለውጡ ጐን ለጐን፣ በህዝቡ ላይ የተጫነው የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት ችግርም አስቸኳይ መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድም እንዲፈለግ ህብር ኢትዮጵያ ጠይቋል - በመግለጫው፡፡


Read 4699 times