Print this page
Saturday, 05 October 2019 00:00

“በጎንደር በተፈጠረው ግጭት የህውሓት እጅ አለበት” - የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

“ህውሓት እጁ እንደሌለበት የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ያውቃል” - አቶ ጌታቸው ረዳ

                  ሰሞኑን በጎንደር ከተማና አካባቢው ተከስቶ የነበረው ግጭትና አለመረጋጋት መስከኑን የገለጸው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፤ ‹‹ከግጭቱ ጀርባ ህውሓት ወይም የጎረቤት ክልል ተሳትፎ እንዳለ አረጋግጫለሁ” በማለት መረጃውን በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ “የሀሰት ውንጀላ ነው” ሲሉ ክሱን አጣጥለውታል፡፡  
ግጭቱ የቅማንት ኮሚቴ በሚል በትጥቅ በተደራጀ ቡድንና በክልሉ ልዩ ሃይል መካከል የተከሰተ መሆኑን የጠቆሙት የክልሉ ሰላምና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘው ተሻገር፤ “ከግጭቱ ጀርባ የትህነግ/ህወሓት እጅ እንዳለበት አረጋግጠናል፤ መረጃውንም በቅርቡ  ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
ከክልሉ ልዩ ሃይል ጋር ሲዋጋ  የነበረው ቡድን፣ መደበኛ ሰራዊት ያለው ዓይነት ከባድ መሳሪያ የታጠቀ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፤ በስናይፐር፣ በመትረየስና በተሟላ ወታደራዊ ትጥቅ የታጀበ ሀይል እንደነበር ለአሜሪካ ድምጽ አስረድተዋል፡፡ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በበኩላቸው፤ “ትህነግ ከግጭቱ ጀርባ እንዳለበት በቂ ማስረጃ አለን፤ ታጣቂዎቹ የትህነግ ተላላኪዎች ናቸው” ሲሉ የአቶ አገኘውን መረጃ አጠናክረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የህወኃት ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ክሱ መሰረተ ቢስ ነው ይላሉ፡፡ “በግጭቱ ህወኃት እጁ የለበትም፤ ህወኃት እጁ እንደሌለበትም የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ያውቃል፤ የቅማንትም የአማራም ሕዝብ ያውቃሉ” ብለዋል፤ አቶ ጌታቸው፡፡ “ህወኃት ላይ ጉዳዩን ማላከክ የአማራ ክልልን የማይመጥን አካሄድ ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፤”ህውኃት በግጭቱ እጁ እንዳለበት ማስረጃ ማቅረብም አይችሉም፤ ማስረጃም የላቸውም” ብለዋል፡፡
“የቅማንት ሕዝብ ሕጋዊ ጥያቄን እንደግፋለን፤ጥያቄውን በአግባቡ መመለስ ያስፈልጋል፤ የፌዴራል መንግስትም ጉዳዩን በቸልታ መመልከት የለበትም፤ትኩረት ተሰጥቶ በቅማንት ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ሊቆም ይገባል” ሲሉም አክለዋል፤ አቶ ጌታቸው፡፡  
‹‹እንደውም የቅማንትን ሕዝብ ግፍ በአደባባይ ወጥተን አለማውገዛችን ያሳፍረናል ያሳዝናል፤ በቅማንት ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ ሁሉም ክልሎች ሊያወግዙት ይገባል” ሲሉ አቶ ጌታቸው ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል፡፡
“የአማራ ብሎም የአገራችን ሕዝቦች የለውጥና የአንድነት ጉዞ በአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች ከቶውንም አይደናቀፍም›› በሚል ርዕስ ከሰሞኑ በጎንደርና አካባቢው ተከስቶ በነበረው ግጭትና አለመረጋጋት ዙሪያ ዝርዝር  መግለጫ ያወጣው የአማራ ክልላዊ መንግስት፤”በከሰሩ የፖለቲካ ቁማርተኞች የእጅ አዙር ትንኮሳ ተካሂዶብኛል” ብሏል፡፡
“የፖለቲካ ሴራው ቅማንትንና አማራን በመለያየት፣ የአማራን ሕዝብ የማዳከም ጥረት ነው” ያለው መግለጫው፤ ‹‹ከዚህ ሴራ ጀርባ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ለፍተው ያለሙትን አዝመራ እንዳይሰበስቡ በማድረግ፣ ክልሉን በኢኮኖሚ ለማዳከም እንዲሁም የታላቋ አገራችን ኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ የጥፋት ሃይሎች የአማራን ሕዝብ ማዳከም የስትራቴጂያቸው አካል በማድረግ፣ ከመሰሎቻቸው ጋር ሆነው የሽብር ድርጊት እያካሄዱ ነው” ብሏል፡፡
“ይህ እቅድም የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ፣ በፋይናንስና ሆን ተብለው ለጥፋት በተከፈቱ ሚዲያዎች አማካኝነት በተቀናጀ መልኩ እየተፈፀመ የሚገኝ ነው” ያለው የክልሉ መንግስት መግለጫ፤መንግስት በእነዚህ ሚዲያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡  “ግጭቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም የአማራ ክልል ራሱን ለመከላከል ይገደዳል” ብሏል- ክልሉ በመግለጫው፡፡    
 ከግጭቱ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ መንግስት ሰሞኑን ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ፤ በጎንደር ከተማና በአካባቢው የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ፣ መንገዶች መዘጋጋታቸውንና ንብረት መውደሙንም ጠቅሶ፣ ዜጎቹ  ለጊዜው ወደ አካባቢው እንዳይጓዙ እገዳ ጥሏል፡፡   
 ከረቡዕ ጀምሮ ጎንደርና አካባቢው መረጋጋቱን የገለፁት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በበኩላቸው፤‹‹የሚወራውና መሬት ላይ ያለው ሀቅ ፈጽሞ የተለያየ ነው፤ ቱሪስቶች እንዳሻቸው እየተንቀሳቀሱ ነው” ሲሉ የጉዞ ማስጠንቀቂያው አስፈላጊ እንዳልሆነ ተናግረዋል፤ለመገናኛ ብዝኃን በሰጡት ቃል፡፡


Read 5602 times