Print this page
Saturday, 05 October 2019 00:00

“ኢሬቻ - የይቅርታ የእርቅና የምስጋና በዓል”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬና አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ፈጣሪ አገራችንን ሰላም ያድርግልን፤ ህፃናት ይደጉ፣
አዛውንቶች ይጦሩ፤ የዘራነውን የምንሰበስብ ያድርገን፤
ሰላም አውሎ ሰላም ያሳድረን፤
ያጣነውን እናግኝ፤
ያገኘነውን አንጣ
የአገራችንን አንድነት ይጠብቅልን፤
ከ4-6 ሚሊዮን ዜጐች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ደምቆ ይከበራል፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ “ሆረ ፊንፊኔ” ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከበረው የኢሬቻ በአል ላይ ከኦሮሞ ህዝብ በተጨማሪ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የበዓሉ ተሳታፊዎች የሚገኙበት ሲሆን ዝግጅቱ በተለያዩ ትርኢቶች ይደምቃል ተብሏል፡፡ ለዚሁ በዓል ማክበሪያ መስቀል አደባባይ ሁለት ገንዳዎች በውሃ ተሞልተው የተዘጋጁ ሲሆን፤ ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጀርባ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፓርክ ውስጥ የሚገኙ 3 የውሃ ገንዳዎች በውሃ ተሞልተዋል፡፡
ዋናው የኢሬቻ ስነስርዓትም በአባ ገዳዎች እየተመራ ለዚሁ ስነስርአት በተዘጋጀውና መስቀል አደባባይ አካባቢ በሚገኘው መናፈሻ ውስጥ ይከናወናል ተብሏል፡፡
 በኦሮሞ ባህል ማዕከል ውስጥ 4ሺህ ሜትር የሚደርስ የኦሮሞ ባህላዊ ምግብ የሆነው ጩኮ፤ ሀጂ ደንቡ አብደላ በተባሉ ግለሰብ ተዘጋጅቶ፣ ከዋዜማው ጀምሮ ለታዳሚያን ይቀርባል፡፡ ጩኮው ከእጅ ንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ መሰረቱንና 29 ቀናትን መፍጀቱ ተገልጿል፡፡ የአልባሳትና የጥበባት ትርኢትም እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
በአሉ ከምንጊዜውም በላይ የኦሮሞ ህዝብን እሴትና ባህል በሚያንፀባርቅ መልኩ እንደሚከበር የገለፁት አቶ ግርማ፤ በዘንድሮ በአል የህዝቦችን ትስስር ለማጐልበት ይቻል ዘንድ መላው የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችን እንዲያሳትፍ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በዚህም ከሀረር፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር ክልል የሚመጡ እንግዶች አዳማ ላይ ሰፊ አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ከጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከወለጋ መስመር የሚመጡ ለገጣፎ ላይ ደማቅ አቀባበል እንደሚጠብቃቸው ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ ነገ እሁድ በቢሾፍቱ ሆራን አርስዲ በአሉ ቀጥሎ እንደሚከበርም ታውቋል፡፡
የኢሬቻ በዓልን አስመልክቶ ዘለግ ያለ መልዕክት ያስተላለፉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ “ኢሬቻ በገዳ ስርአታችን እሴቶች የሰላምና የአንድነት ተምሣሌት ነው” ብለዋል፡፡
ኢሬቻ የምስጋና፣ የፍቅር፣ የሠላም፣ የእርቅና የይቅርታ በዓል ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የኢሬቻን ዋነኛ እሴቶችም በምልአት ዘርዝረዋል፡፡ መላው የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ኢሬቻን በፍቅር፣ በይቅርታና በሠላም ተያይዘው ወደፊት ለመሻገር በጋራ ሊያከብሩትና መልካም እሴቶቹን ሊቋደሱ እንደሚገባም ጠ/ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል - በመልዕክታቸው፡፡
“ኢሬቻ አገር የመገንባትና የማልማት ኃላፊነትን በትጋትና በነባር ኦሮማማ እሴቶቻችን ወደ ላቀ ድል የምንሸጋገርበት የቃል ኪዳን በአላችን ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ኢሬቻ የገዳ ፍልስፍናን፣ እሴቶችንና አስተምህሮዎችን ለአገር ግንባታ ለማዋል ቃል የምንገባበት በዓል ይሆናል ብለዋል፡፡
ኢሬቻ በአገር አቀፍ ደረጃ የመላ ኢትዮጵያውያን የጋራ የምስጋና በዓል ነው ብዬ አምናለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሉ ለኢትዮጵያውያን የበለጠ ትስስርና መግባባትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡   
የባሌው አባገዳ አሊ መሐመድ ስለ እሬቻ እንዲህ ያብራራሉ፡-
“የእሬቻ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት ባህል ነው፡፡ ሁሉም ሰው በየቤቱ ተቀያይሞ የነበረውን ይቅር የሚባባልበት ጊዜ ነው፡፡ እሬቻ ማለት ይቅርታ ማለት ነው፡፡ ዝናባማና ደመናማ ከሆነው ጊዜ ወደ ብራ፣ ወደ ፀሐይ የወጣንበት ጊዜ ስለሆነና የዘራነው እህል በዝናቡ ጥሩ ሆኖ ስለደረሰልን ፈጣሪን የምናመሰግንበት ፕሮግራም ነው፡፡ እሬቻ ምስጋና ነው፡፡ እሬቻ አንድነትን የሚያጠናክር፣ ሰላምን የሚሰብክ፣ ፍቅር ያለበት የአንድነት በዓል ስለሆነ ሁላችንም በጋራ ልናከብረው ይገባል፡፡ አሁን እኛ እንደ ኢትዮጵያዊ የምንፈልገው ሠላም ነው፡፡ እሬቻ ደግሞ የሰላም በዓል ነው፤ ሁላችንንም የሚያሳትፍ፣ ማንንም የማይገድብና ይቅር የምንባባልበት ጊዜ ስለሆነ ሁሉም ሰው በዚህ በምስጋናና በይቅርታ በዓል ላይ ተገኝቶ ይቅር ሊባባል ይገባል፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያዋጣን አንድነት ነው፡፡ ጣሊያን በወረረን ጊዜ አንድ ሆነን እንደመከትነው ሁሉ አሁንም የሚያስፈልገን አንድነትና ህብረት ነው፡፡ ይሄ የሚወራውን ትናንሽ ነገር በጆሮአችን መስማት፣ በልባችን መቀበሉን ትተን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጐሳ ሳንከፋፈል አንድ መሆን ነው የሚያስፈልገን፡፡
‹‹ስለዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ከኦሮሞ ወንድሞቹ ጋር ተደስቶ በዓሉን አብሮን ሊያከብር ይገባል፡፡ ወንድሞቻችን ደቡብ ላይ ጨምበላላን ሲያከብሩ ቦታው ድረስ ሄደን አብረን አክብረናል፣ የአማራና የትግራይ ወንድም እህቶቻችን ሻደይና አሸንዳን ሲያከብሩ እዚያው አብረናቸው አክብረናል፡፡ አሁን ደግሞ እኛ፤ እሬቻን አብረውን እንዲያከብሩ እንፈልጋለን፡፡”
ጐተራችን ሙሉ ይሁን!
ጢቃን ኬ ሲ ያ ጉደቱ
ጉዳን ኬ ሲ ያቡሉ
ዋን ከሌ ደብዴ አርገዱ
ቢዬ ኢትዮጵያ’ረት ጅባዳ ጅራዱ
ገለቶሚ!   

Read 5246 times