Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Print this page
Saturday, 05 October 2019 00:00

ከእስር ቤት መልስ - ወደ በጎ አድራጎት የገባችው የቀድሞዋ ፖለቲከኛ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 - ‹‹እናት ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት›› የተባለ ድርጅት አቋቁማለች
                 - በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይሰራል

           የቀድሞ ‹‹አንድነት ለፍትህ ፓርቲ››ን ገና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆና በመቀላቀል የፓርቲው ብሔራዊ ም/ቤት አባልና የሰሜን ጎንደር ዞን የፓርቲው አደረጃጀት ዘርፍ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሳለች በ‹‹አሸባሪነት›› ተከሳ ለእስር ተዳረገች፡፡ ለ3 አመታትም በአሰቃቂ እስር ላይ ቆይታለች፡፡ በእስር ቤት እያለች ወላጅ እናቷን በሞት አጥታለች፡፡ የወላጅ እናቷን ሞት በጊዜው እንዳትረዳ ተደርጋ በመቆየቷም ለከፍተኛ የስነ ልቦና ስብራት ተዳርጋ እንደነበር ከእስር ቤት በወጣችበት ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ መግለጿ አይዘነጋም:: ይህ የስነ ልቦና ስብራትም ለጭንቀትና ለከፍተኛ የልብ ህመም ዳርጓት፣ ከእስር ቤት መልስ በየሆስፒታሉ ተንከራታለች፡፡ ‹‹ዛሬ ግን ፈጣሪ ይመስገን ጤንነቴ ተመልሷል›› ትላለች - የቀድሞዋ ፖለቲከኛ አስቴር (ቀለብ) ስዩም፡፡
ከፖለቲካው ራሷን ማግለሏን የምትናገረው ወ/ሮ አስቴር፤ ከእስር ቤት ተሞክሮዋና በአገሪቱ ከተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውሶች ተነስታ፣ በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የሚሰራ ‹‹እናት ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት›› የተሰኘ ድርጅት መስርታለች፡፡
ይህን ድርጅት እንዴት ልትመሰርት አሰበች? የድርጅቱ አላማና ግብ ምንድነው? በምን ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይሰራል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መስራቿን ወ/ሮ አስቴር ስዩምን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯታል፡፡


             ከእስር ቤት መልስ ሕይወት ምን ይመስላል?
ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ብዙ ነገር አጋጥሞኛል፡፡ እስር ቤት እያለሁ በብዙ ሕመም ስሰቃይ ነበር፡፡ ከወጣሁ በኋላ ህመሙን ለመታከም ከ4 በላይ ሆስፒታሎች ገብቻለሁ:: ህመሙ ከከፍተኛ ጭንቀት የሚመጣ የልብ ቧንቧ ጥበት ነው ተብዬ መድኃኒት ስወስድ ቆይቻለሁ፡፡ ከዚያ ጎን ለጎን ግን ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ አንዲት ሴት ልጅ ወልጃለሁ:: የሚገርመው ደግሞ በእስር ቤት እያለሁ በሞት ያጣኋትንና ለመቅበር እንኳ እድል ያላገኘሁላትን እናቴን ራሷን ነው የወለድኳት፡፡ በመልክ እናቴን ራሷን ነው የምትመስለው፡፡ ይሄ ለኔ ብዙ ትርጉም አለው፡፡ ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት በግል ሕይወቴ እነዚህ ሁነቶች አልፈዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ወደ ተወለድኩበት ታች አርማጭሆ ጎንደር ሄጄ የእናቴን ለቅሶ እርም አውጥቻለሁ፡፡ በሄድኩበት ወቅት እናቴ ካለፈች ሁለት አመት አካባቢ ነበር:: ነገር ግን ወንድሞቼ እሷ ከእስር ካልተፈታች ተዝካር አናወጣም ብለው ቆይተው፣ እኔ እርሜን ለማውጣት በሄድኩበት ወቅት ነው የመጀመሪያ ተዝካርም የተደረገው። ወንድሞቼ እኔ እስከምፈታ ጠብቀው ይሄን ማድረጋቸው በወቅቱ ለኔ አስደንቆኝ ነበር፡፡ ሕዝቡም እንደ አዲስ ነበር ለለቅሶ የተሰበሰበው፡፡ ለሁለት ወር ያህል ህዝቡ ተሰብስቦ እናቴን ሲያስብ ነው የቆየው። ከዚያ ከተመለስኩ በኋላ ማስተርስ የሰራሁበትን የኢኖርጋኒክ ኬምስትሪ ሰርተፊኬት ከዩኒቨርሲቲ ለመውሰድ ስሞክር ‹‹አይቻልም በመጀመሪያ እንደገና የጥናት ጽሑፍ አቅርቢ›› ተብዬ ድጋሚ የጥናት ጽሑፉን ሰርቼ የማስተርስ ዲግሪ ሰርተፊኬቴን ወስጃለሁ፡፡
በሌላ በኩል፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመጎብኘት ዛሬ እስር ቤት ከሚገኘው ስንታየሁ ቸኮልና ሌሎች ወዳጆቼ ጋር ወደ ቦታው ሄደን እርዳታ አሰባስበን ድጋፍ ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ በወቅቱ የተፈናቀሉ ዜጎቻችን ባየሁ ጊዜ በጣም ስሜቴ ተነስቶ ነበር:: እንዴት በዘላቂነት ማገዝ እንደሚቻል ሳስብ ሳሰላስል ነበር የቆየሁት፡፡ እርዳታ ይሰጣሉ ላልኳቸው ሰዎች ፎቶ ግራፎችን፣ ቪዲዮዎችን እየላኩላቸው እርዳታ እንዲሰጡ እጎተጉት ነበር:: በዚህም ቀና ምላሽ ማግኘት ችያለሁ፡፡
አሁን የጤንነትሽ ጉዳይ እንዴት ነው?
አሁን ደህና ነኝ፤ የሥነ ልቦና ሕክምናም አግኝቻለሁ፡፡ በጥሩ ስነ ልቦናና የሥራ መነቃቃት ውስጥ ነው የምገኘው ማለት እችላለሁ፡፡
ቀደም ብሎ መምህር ነበርሽ፤ ጎን ለጎንም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራርም ነበርሽ፡፡ ወደ እነዚህ ሥራዎችና እንቅስቃሴዎችሽ መመለስ አልቻልሽም?
ወደ ምወደው መምህርነት ለመመለስ ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ነገር ግን አልተሳካልኝም:: ለረዥም ጊዜ የመምህርነት ስራ ማስታወቂያዎችን እየተከታተልኩ አመለክት ነበር፤  ሆኖም የሚቀጥረኝ አላገኘሁም፡፡ በዚህ ምክንያት ወደምወደው ሙያዬ መመለስ አልቻልኩም፡፡
በፖለቲካ በኩል ግን እኔ የምችለውን ሁሉ ትግል ለሀገሬ የዲሞክራሲ እመርታ አድርጌያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ እንግዲህ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከመጡ በኋላ በርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ተፈተዋል፤ አንፃራዊ የሃሳብን በነፃነት መግለጽ መብት መጥቷል ተብሎ ይታመናል፤ ነገር ግን በቀጣይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወዴት ሊደርስ ይችላል? ግቡ ምንድን ነው? ሀገር  ወዴት እየሄደች ነው? የሚለው የሚያሳስበኝ ቢሆንም፣ አሁን በዚህኛው ወይም በዚያኛው የፖለቲካ ጐራ ተሰልፌ የበኩሌን አደርጋለሁ ብዬ ለመወሰን አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ ሀገራችን በጭንቅና በተስፋ ውስጥ ያለች ሀገር ነች፡፡ ስለዚህ አሁን መሃል ላይ ቆሜ ነገሩን ብመለከት ይሻላል በሚል ከፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ራሴን አግልያለሁ፡፡ አሁን የራሴን አስተዋጽኦ አበረክትበታለሁ ብዬ ያሰብኩትን አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አቋቁሜያለሁ፡፡
የተቋቋመው ድርጅት አላማ ምንድን ነው? ድርጅቱን ለማቋቋም ያነሳሳሽ ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ ውስጥ እንግዲህ እንደምናውቀው ብዙ ዜጐች የማይገባቸውን ዋጋ ከፍለዋል:: ሊወነጅሉ በማይገባቸው ጉዳይ እየተወነጀሉ በመታሠር፣ ግማሹ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ግማሹ በግፍ እየተገደለ ዜጐች ብዙ ዋጋ የሚከፍሉባትና የከፈሉባት ሀገር ነች ያለችን፡፡ ለሀገር ዋጋ ከከፈለ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ደግሞ አንዱ የኔ ቤተሰብ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እጅግ የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ከተደረገባቸው ኢትዮጵያውያን ውስጥም የኛ ቤተሰብ አንዱ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሣሌ በኔ መታሰር ስትብሰከሰክ ህመምተኛ የሆነችውን እናቴን አጥቻለሁ፡፡ የእናቴን ማለፍ እንኳ በወቅቱና በአግባቡ ተረድቼ እርሜን እንዳላወጣ ተደርጌያለሁ፡፡ የጤና ባለሙያ የሆነው የባለቤቴ ወንድም ፋሲል ጌትነት እኔ ከታሠርኩ ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ የት እንደጠፋ እንኳ እስካሁን ማወቅ አልቻልንም፡፡ ከ5 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ የት እንደደረሰ እንኳ ማወቅ ሳንችል ዛሬ ነገ ይመጣ ይሆን? ሞቶ ይሆን? በሚሉ ሃሳቦች ቤተሰብ እየተብከነከነ ነው ያለው፡፡ ባለቤቴ ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ነፃ ሆኖ እያለ፣ በኔ ምክንያት በሙያው ሰርቶ እንዳያድር ተደርጐ ቆይቷል፡፡
በኔ ምክንያት የኔ ቤተሰብ እንደከፈለው ዋጋ ሁሉ በርካቶች ከዚህም በላይ ከፍለዋል:: በዚህ መነሻ ነው እንግዲህ በዋናነት ሰብአዊ መብት ላይ የሚሠራና የእስረኞችንና ታሣሪ ቤተሰቦችን ሁኔታ የሚከታተል ተቋም ለመመስረት የቻልኩት፡፡ የፖለቲካ እስረኞች ብዙ ግፍ ሲፈፀምባቸው ተመልክቻለሁ፡፡ ሰው መብቱ ሲገፈፍ፣ በህይወት የመኖር መብቱን በግፍ ሲነጠቅ አይቻለሁ፡፡ ይሄን አሰቃቂ ድርጊት እንዴት ነው ማስቆም የሚቻለው? የታሣሪ ቤተሰቦች ከስነልቦና ስብራት እንዴት ነው የሚጠገኑት? የሚለውን ነገር እስር ቤት እያለሁም አስበው ነበር፡፡ እናም በእነዚህ መነሻ ነው ይሄን ድርጅት ያቋቋምኩት፡፡ ይህ ተቋም በሰብአዊ መብት ረገድ ሌላው አትኩሮት ሰጥቶ የሚሠራበት የተፈናቃዮች ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ሲፈናቀሉ የሚያጡት ማህበራዊ ህይወት፣ የኢኮኖሚ ምስቅልቅልና የስነ ልቦና ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ይሄን እኔ በተግባር አይቸዋለሁ:: እናቶች ሕጻናት ልጆቻቸውን እያዩ ሲያነቡ፣ ተስፋ ሲያጡ አለም ሲጨልምባቸው፣ ብቸኝነትና ባዶነት ሲሰማቸው በቅርበት አስተውያለሁ፡፡
ተቋሙ ስያሜው ‹‹እናት ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት›› ድርጅት ነው የሚባለው፤ ስለዚህ እነዚህን ወገኖች እንደ እናት አለሁ ሊላቸው ይፈልጋል፡፡ እዚህ ላይም አተኩሮ ይሰራል፡፡ እናት ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜም ወላጆቻቸውን ያጡ ብቸኝነት የተሰማቸው ዜጎች ኢትዮጵያ እናታቸው እንደሆነች ለማመላከት ነው፡፡ ዜጎች በአገራቸው ሊንገላቱ አይገባም፤ እናት ኢትዮጵያ አቅፋ ይዛ ልትደግፋቸው ልትንከባከባቸው አለኝታ ልትሆናቸው ይገባል ከሚል መነሻ ነው፣ እናት ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜም የተሰጠው፡፡
ድርጅቱ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ሲሰራ በምን መልኩ ነው?
በአጠቃላይ እናት ኢትዮጵያ ይዞት የተነሳው የራሱ አላማና ግብ አለው፡፡ 15 ዋና ዋና አላማዎችን አስቀምጧል፡፡ አንዱ በሰብዓዊ መብት መከበርና የመልካም አስተዳደርን በማስፈን ከተቋማት ጋር ተባብሮ የሚሰራው ነው፡፡ ይሄን ስራ ሲሰራም በመላ ኢትዮጵያ ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተግባሩን የሚያከናውነው በአመዛኙ የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት ረገድ ነው:: ለምሳሌ ሴቶች በፖለቲካ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጎለብቱ፣ ለመብታቸውና ለኢኮኖሚ ዋስትናቸው እንዲታገሉ፣ መብትና ግዴታቸውን አውቀው እንዲንቀሳቀሱ የማንቃት ስራ ይሰራል፡፡ በአመዛኙ የአስተሳሰብና አመለካከት ቅየራ ላይ ነው የሚሰራው፡፡ አለፍ ሲልም ዜጎች የሰብዓዊ መብታቸውን አውቀው ተረድተው እንዲያስከብሩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ይሰጣል፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ለምሳሌ ሴቶች በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችል የማነቃቃት ተግባር ድርጅታችን ለመስራት ከወዲሁ አቅዷል፡፡ ይሄን ስልጠና ሲሰጥ ግን ‹‹እከሌን ምረጥ፤ እከሌን አትምረጥ›› በሚል ሳይሆን በምርጫ አስፈላጊነትና መብትነት ላይ ነው:: በተጨማሪም በአገሪቱ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በፍጥነት እንዲታረሙ የሚያደርጉ ሥራዎችን ይሰራል፡፡
የተፈናቀሉ ዜጎች ላይስ በተለየ ሁኔታ ድርጅቱ ሊሰራ ያሰበው ምንድን ነው?
እንግዲህ መፈናቀሉ ያለው እዚሁ አገር ቤት ነው፡፡ የምናፈናቅለውም እኛው ነን፡፡ እንደውም በአገር ውስጥ መፈናቀል ከአለም አንደኛ ሆነን ነው በ2018/19 የተመዘገብነው፡፡ በጦርነት ከምትታመሰው ሶሪያም ልቀን ማለት ነው:: ‹‹እናት ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት›› በዚህ ጉዳይ ለመስራት ያሰበው፡- ፈጣን እርዳታ አስተባብሮ ለማቅረብ፣ ተፈናቃዮችን ቤተሰቦቻቸው ለስነ ልቦና ስብራት እንዳይዳረጉ የማረጋጋት ሥራ ማከናወን የመጀመሪያዎቹ ተግባራት ናቸው፡፡ ሥነ ልቦናው የተሰበረ ዜጋ በቀላሉ ሊጠገን ስለማይችል አለሁልህ ተብሎ በፍጥነት ከስብራት መታደግ ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ እኛም ይሄን መሰረት አድርገን ነው መፈናቀል ባጋጠማቸው ቦታዎች ሁሉ ለመስራት ያቀድነው፡፡ ዜጎች የተፈናቀሉበትን ምክንያትም በጥናት ለይቶ፣ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በወደፊት እጣ ፈንታቸው ላይም መክሮ ቀጣይ ሕይወታቸውን ለማስተካከል የድርሻውን ይወጣል፡፡ በመፈናቀል ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎች ካሉም ትምህርታቸውን ተፈናቅለው በተቀመጡበት አካባቢ (ደብተርና ሌሎች የሚያስፈልጋቸውን ቁሶች አሟልቶ) እንዲቀጥሉ ያደርጋል።  ለኛ አንድና ሁለት ቤተሰብ መንከባከብ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ሌላው የምንሰራው ተግባር የእስር ቤት ጉዳይ ነው፡፡ በእስር ቤት የሚፈፀሙ ጥሰቶችን እየተከታተለ ሪፖርት የማድረግ ሥራ ይሰራል፡፡ ያለፉ ጥፋቶችንም መርምሮ የማውጣትና ለመማሪያነት የማቅረብ አላማ አለው፡፡ እነዚህን መረጃዎች ከሰበሰበ በኋላ አገር ውስጥ ላሉና በውጭ ለሚገኙ ጉዳዩን በአንክሮ ለሚከታተሉ አካላት ጥቆማ ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንኳን በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ 230 ያህል እስረኞችን መረጃ አሰባስበን ይዘን ክትትል ማድረግ ጀምረናል፡፡ በእነዚህ ተግባራት ላይ አተኩረን እንሰራለን፡፡
የዚህ ድርጅት የመጨረሻ ግቡ ምንድነው?
አገራችን ውስጥ ሰላም እንዲረጋግጥ፣ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት እንዲኖሩ፣ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ ዜጎች ያለበቂ ማስረጃ የማይታሰሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማገዝ እንዲሁም በንግግርና በውይይት ብቻ የሚያምን ዜጋ መፍጠር ነው፡፡ ፍትህ የሰፈነባት አገር እንድትሆን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተፈተው ማየት ነው ራዕያችን፡፡
ሰፊ ፕሮጀክት ያቀደ ድርጅት እንደመሆኑ የፋይናንስ ምንጩ ከየት ነው?
በነገራችን ላይ ድርጅቱ አንደኛው ተግባሩ ለተጨማሪ ስራ የሚውሉ ገንዘብ የሚያስገኙ ፕሮጀክቶችን መተግበር ነው፡፡ ገንዘብ አስገኝተው ሌላውን ስራችንን ሊደግፉ የሚችሉ የተለያዩ የገንዘብ ማመንጫ ፐሮጀክቶችን እየነደፍን ነው፡፡ በቀጣይ ይፋ እናደርጋቸዋለን:: ከዚያ በመለስ ግን በአዲሱ የበጎ አድራጎት አዋጅ መሰረት፤ ስራችንን በተግባር እያሳየን አለማቀፍ እርዳታ ለማሰባሰብ እንጥራለን፡፡ ከወዲሁም እቅዳችንን አይተው ለመደገፍ ቃል የገቡልን አካላት አሉ፡፡
በቀጣይ ቅርንጫፎቻችን እናበራክታለን፡፡ ለጊዜው በባህርዳና ደቡብ ክልል ላይ የመጀመሪያዎቹ ቅርንጫፎች በቅርቡ ይከፈታሉ፡፡ በቀጣይ ስራችን እየሰፋ ሄዶ በመላ ኢትዮጵያ ነው ቅርንጫፍ መክፈት ያቀድነው፡፡

Read 1043 times