Saturday, 05 October 2019 00:00

በዓመት 18.5 ቢሊዮን ብር (620 ሚ.ዶላር) ወለድ፣ የኢትዮጵያን ፈተና ያሳያል

Written by  ዮሃንስ. ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 የውጭ እዳና ወለድ - በ2001 እና በ2011 ዓ.ም
የመንግሥት የውጭ እዳ (በዶላር)
በ2001 ዓ.ም … 4.4 ቢሊዮን ዶላር
በ2011 ዓ.ም … 27 ቢሊዮን ዶላር
ለውጭ እዳ ከነወለዱ የተከፈለ (በዶላር)
በ2001 ዓ.ም … 80 ሚሊዮን ዶላር
በ2011 ዓ.ም …. 2,000 ሚሊዮን ዶላር (2 ቢሊዮን)
ለወለድ የተከፈለ (በዶላር)
በ2001 ዓ.ም … 30 ሚሊዮን ዶላር
በ2011 ዓ.ም … 620 ሚሊዮን ዶላር (18.6 ቢሊዮን ብር)
የመንግስት የውጭ እዳ፣ እንደ ሌሎቹ የአገራችን ችግሮች፣ በላይ በላዩ እየተከመረ፣ በአንድ ዓመት፣ ለወለድ ክፍያ ብቻ፣ 620 ሚ.ዶላር እስከ መክፈል መደረሱ ያስደነግጣል››:: ያስፈራል ቢባል ይሻላል፡፡ ድንገት ደራሽ አደጋ አይደለምና፡፡ የአስር አመታት የስህተት መዘዝ ነው፡፡ ክፋቱ ደግሞ፣ ከዚህ የማይተናነስ ሌላ ችግር አለ፡፡
የእዳ እና የወለድ ሸክም እንደ ሐምሌ ዝናብ እያከበደ፣ ለእዳ ክፍያ ብዙ ዶላር ማፍሰስ የግድ ሀኗል፡፡ ከኤክስፖርት የሚገኘው ዶላር ግን፣ በካፊያ ብቻ ቀርቷል፡፡
በ2001 ዓ.ም፣ ከኤክስፖርት የሚመጣው ዶላር፣ እዳና ወለድ ለመክፈል ብቻ ሳይሆን፣ ነዳጅ ለመግዛትም ጭምር ይበቃ ነበር፡፡ አሁን ግን በእዳና በወለድ እያለቀ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ለነዳጅ ብቻ፡፡
በአስር ዓመት ልዩነት፣ ለእዳና ለወለድ የሚገፈገፈው ዶላር ከ20 እጥፍ በላይ ጨምሯል::
ከ100 ሚሊዮን በታች የነበረው የእዳና የወለድ ሸክም፣ አሁን በዓመት 2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ የኤክስፖርት ገቢ በተቃራኒው፣ እያሽቆለቆለ ነው፡፡
በሌላ አነጋገር፣ የኤክስፖርት ድንዛዜ፣ ከእዳና ከወለድ ሸክም የማይተናነስ፣ ሌላ ከባድ ችግር ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የወለድ ሸክምና የኤክስፖርት ድንዛዜ፣ ለብቻቸው የተፈጠሩ መንትያ ችግሮች አይደሉም፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያዛባና የዜጐችን ኑሮ የሚያናጋ የዋጋ ንረት፣ ከሁለቱ ችግሮች ጋር ይዛመዳል፡፡ መፍትሔያቸውም እንዲሁ፡፡
    የውጭ እዳ - በቢሊዮን ዶላር
2000    2.8
2001    4.4
2002    5.6
2003    7.8
2004    8.9
2005    11.2
2006    14.0
2007    18.6
2008    21.3
2009    23.3
2010    25.8
2011    27.0


    የእዳ ክፍያ - በሚሊዮን ዶላር
2000    89
2001    77
2002    111
2003    242
2004    412
2005    567
2006    667
2007    993
2008    1,130
2009    1,288
2010    1,603
2011    1,996


    የወለድ ክፍያ - በሚሊዮን ዶላር
2000    32
2001    28
2002    42
2003    62
2004    103
2005    138
2006    160
2007    259
2008    358
2009    433
2010    446
2011    620

የአንዱ በሽታ መድሃኒት ለሌሎቹ ማገገሚያ ይሆናል፡፡
የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር፣ ኑሮ እንዳይናጋ፣ ኢኮኖሚውም እንዳይዛባ፣ ቀጥተኛና ግልፅ መፍትሄ አለ።
ለመንግስት በጀት ልጓም፣ ለብድሩ ለከት፣ ለብር ሕትመትም ፍሬን ማበጀት ነው - መፍትሄው። ይሄ በራሱ ትልቅ ቁም ነገር ነው። ግን፣ ምርቃት (‹‹ቦነስ››) አለው፡፡ የገንዘብ ሕትመት መረን ካልተለቀቀ፣ የብር ዋጋ ካልረከሰ፣ የዶላር ምንዛሬ እንዳይዛባ መከላከል አይከብድም።
ቆሌው እስኪገፈፍ ድረስ፣ የገንዘብ ኖት በገፍ እየታተመ፣ የብር ዋጋ እየከሳ የሚረክስ ከሆነ ግን፣ የዶላር ምንዛሬ በጥቂት ወራት ውስጥ ሚዛኑን ይስታል፡፡ በየዓመቱም እየባሰበት ይዛባል፡፡ እዚያው በነበረበት አይቆይም።
አዎ፣ የዶላር ምንዛሬ እንዳይንር፣ እዚያው በነበረበት ለማቆየት፣ እንዳይነቃነቅ ደፍጥጦ ለመያዝ፣ መንግስት ሁሌም ሲሞክር ይታያል። የምንዛሬ ተመን የሚወሰነው በብሔራዊ ባንክ ነው ተብሎ ክትትልና ቁጥጥር ይካሄዳል፡፡ በእርግጥም፣ ለስም ያህል፣ “አንድ ዶላር በ30 ብር ይመነዘራል” ይላል - የመንግስት ተመን።
በተግባር ግን፣ ተመኑ ለመንግስት ከተመቸ ብቻ እንጂ፣ ለሌላ አይሰራም። መንግስት፣ ከዜጎች ዶላር እየወሰደ፣ በብር መንዝሮ ይሰጣል - በ30 ብር ሂሳብ። ብር ይዘው ቢጠይቁት ግን፣ በዶላር መንዝሮ አይሰጥም። አያዋጣውም። በኮታ፣ በወረፋ፣ በቁጥ-ቁጥ፣ እፍኝ ዶላር መንዝሮ ከሰጠ፣ “ብርቅ” ስለሆነ፣ እንደ ትልቅ ደግነት ወይም እንደ ከባድ ውለታ ነው የሚቆጠርለት። በአብዛኛው፣ ጨርሶ ዶላር አይሰጥም።
በአጭሩ፣ መንግስት፣ ራሱ ባወጣው የምንዛሬ ተመን፣ ዶላር ለመሸጥ አይፈልግም።
ቢፈልግ እንኳ አይችልም። ዶላር ከየት ይመጣል? ለራሱም አልበቃውም። “ብር ይዞ ለሚመጣ ሁሉ፣ በ30 ብር ሂሳብ፣… ከምር፣ ዶላር እሸጣለሁ” ቢል፣ በአንድ ቀን ውስጥ ባዶ እጁን ይቀራል። እናም፣ ለመንግስት ሲመቸው ብቻ እንጂ፣ “የምንዛሬ ተመን”፣ ለስም ያህል ብቻ ነው። በተግባር፣ አንድ ዶላር በ40 ብርና ከዚያም በላይ ነው የሚመነዘረው - በተባራሪ ገበያ። ለምን?
የገንዘብ ኖት አለቅጥ ከታተመ፣ ብር መርከሱ፣ እንደሌላው ሸቀጥ፣ የዶላር ዋጋም ሽቅብ መናሩ፣ ውጤትና መዘዙ አይቀሬ ነው። “የምንዛሬ ዋጋ እቆጣጠራሉ” በማለት መዘዙን ለማስቀረት መሞከር፣ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሌላ የራሱን መዘዝ ያመጣል - እንደምናየው ይሆናል፤ ምንዛሬ ይዛባል። “የዶላር የምንዛሬ ተመን” እና “የዶላር የገበያ ዋጋ” ይለያያሉ። ከመለያየትም ይራራቃሉ። አሁን፣ ልዩነታቸው ሰፍቶ፤ ከመዛባትም አልፏል።
 በአንድ ወር ወይም በአንድ ዓመት ውስጥ የታተመ የገንዘብ ብዛት አይደለም፣ የችግሩ ሰበብ። ለበርካታ ዓመታት ስድ የተለቀቀ የሕትመት አመል ሲደራረብ ነው፣ የዚያኑ ያህል “ብር” የቀለለው፤ ዶላር የከበደው። ምንዛሬ የተዛባው። ለአመታት የተዛባውን ምንዛሬ፣ በአንዴ ላስተካክልህ ቢሉት፣ ቀላል አይሆንም። የተዛባውን ይዤ ልቀጥል ቢሉም፤ “እሺ” አይልም። ለምን?
• ለመንግስት ካላዋጣ ለሌላው እንዴት ያዋጣል?
መንግስት፣ ራሱ ባወጣው ተመን፣ 30 ብር እየሰጠ ዶላር መግዛትን ይፈልጋል እንጂ፣  30 ብር እየተቀበለ ዶላር መሸጥን አይፈልግም። አያዋጣውም። ከሞከረም፣ ውሎ ሳያድር ዶላሩ ይሟጠጣል። ግን ሌላውም ሰው አያዋጣውም።
በ30 ብር የምንዛሬ ተመን፣ ዶላር ለመግዛት እንጂ፣ ዶላር ለመሸጥ የሚሽቀዳደም ጤነኛ ሰው አይኖርም። የሚኖር ከሆነም፣ ገና በጥዋቱ፣ በፈጣን ኪሳራ፣ በባዶ ኪስ ከገበያው ይሰናበታል። ከጥቁር ገበያ በ40 ብር ሂሳብ ዶላር እየገዛ፣ ለመንግስት በ30 ብር ሂሳብ ለመሸጥ የሚሮጥ ሰውስ፣ በስንት ደቂቃ ይራቆታል?
በመንግስት የምንዛሬ ተመን ዶላር ለመሸጥ የሚሮጥ ሳይሆን፣ ዶላሩን ከመንግስት ለመሸሸግ፣ ከመንግስት ተመን ለመሸሽ የሚሮጥ ነው የሚበዛው። በድንበር በኩል በድብቅ ወደ ውጭ ወርቅ ለመውሰድና ለመሸጥ፣ በርካታ ሰዎች መከራቸውን የሚያዩት ለምን ሆነና?
የመንግስት እዳ፣ የተዛባ ምንዛሬና የወርቅ ኮንትሮባንድ፡፡
በረሃ ላይ በድንኳን እያደሩ፣ ከንጋት እስከ ምሽት አፈር ሲምሱ፣ ድንጋይ ሲፈነቅሉ፣ ጉድጓድ ውስጥ ውለው፣ በባትሪ ጭምር ሲቆፍሩ ሌቱን የሚያጋምሱ፣…. ከቆፈሩት ክምር አፈር፣ ብናኝ ወርቅ ለማግኘት፣ ወንዝ ውስጥ ተነክረው፣ አፈር አበጥረው፣ አፈር አጥበው፣…. ቅንጣት ታህሏን ለማጠራቀም፣ ቁም ስቅል የሚያዩ ሰራተኞች፣ ወርቅ ሸጠው ጥሩ ዋጋ ለማግኘት ቢመኙ እንዴት ይገርማል?
በእርግጥ፣ ቡና አብቃይና የሰሊጥ ገበሬም፣ ምርቱን በጥሩ ዋጋ ለመሸጥ ይመኛል። ወርቅ፣ ቡና፣ ሰሊጥ፣…. በአለም ገበያ ተፈላጊ ናቸው - በዶላር። ነገር ግን፣ በመደበኛው መስመር ከተሸጠ፣ ዶላሩ ወደ መንግስት እጅ ይገባል - በ30 ብር ሂሳብ መንዝሮ ይሰጣቸዋል። በድንበር በኩል፣ ከመንግስት ተደብቀው፣ በራሳቸው መስመር በዶላር ከሸጡ ግን፣ የሚያገኙትን ዶላር በ40 ብር ሂሳብ መመንዘር ይችላሉ።
ነገር ግን፣ ወርቅና ቡና እኩል አይደለም። መቶ ኩንታል ቡና በድብቅ ማጓጓዝና፣ አንድ ኪሎ ወርቅ አሳቻ ቦታ ሸጉጦ ማሳለፍ፣ ይለያያሉ። ከቡና ይልቅ፣ ወርቅ ለኮንትሮባንድ ይመቻል። ታዲያ፣ ከቡና ጋር ሲነፃፀር ነው እንጂ፣ የወርቅ ኮንትሮባንድ፣ “ከምር ይመቻል” ማለት ግን አይደለም። አይመችም።
ኮንትሮባንድ፣ አመቺ ሆኖ አያውቅም። በአቀባባይና በአስተላላፊ ብዛት፣ የንግድ ሰንሰለቱ ተንዛዝቶ ወጪው ይበዛል። እስከ ድንበር ድረስ ረዥም ርቀትን ማቋረጥ፣ ባልተለመዱ አቅጣጫዎች ከመደበኛው መንገድ ውጭ አስቸጋሪ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ቀላል አይደለም። በዚያ ላይ፤ አደጋው ብዙ ነው - ሕይወትን፣ አካልንና ንብረትን ሁሉ በሚያሳጣ አደጋ የተከበበ ነው - ኮንትሮባንድና ጥቁር ገበያ። የቀጥተኛ ንግድ ያህል አይመችም። የነፃ ንግድ ያህል አትራፊ አይደለም።
ችግሩ ምንድነው? ቀጥተኛው የንግድ መስመር፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚካሄድ እንጂ፣ ነፃ ንግድ ያልሆነ ጊዜ ነው ችግሩ። በቀጥተኛው የንግድ መስመር፣ 3 ሚሊዮን ብር ማግኘት ይሻላል? ወይስ፣ አቀባባይ በበዛበት፣ በአደገኛውና በአስቸጋሪው የኮንትሮባንድ መንገድ 4 ሚሊዮን ብር ለማግኘት መሞከር ይሻላል?
እንዲህ አይነት ጥያቄ፣ ለአነስተኛ ወርቅ አምራቾች ምን ያህል ትርጉም እንዳለው ለመገመት፣ የየዓመቱን የወርቅ ኤክስፖርት መቃኘት ነው። ዛሬ ዛሬ፣ አነስተኛ የወርቅ አምራቾች፣ ቀጥተኛውን የንግድ መስመር እርግፍ አድርገው ትተውታል ቢባል ይሻላል። የወርቅ ኤክስፖርት ከ600 ሚሊዮን ዶላር ወደ 30ሚ ዶላር ወርዷል-በ7 ዓመታት ልዩነት፡፡
የዶላር ምንዛሬ እየተዛባ፣ “በመንግስት የምንዛሬ ተመን እና በገበያ የምንዛሬ ዋጋ” መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ በመጣ ቁጥር፣ የወርቅ ኮንትሮባንድ ቢጨምር አይገርምም። ኮንትሮባንድ እንዲቀንስ ስንመኝ ውለን ብናድር፣ በእልፍ ላይ እልፍ ተቆጣጣሪ ብናሰማራ፣ መፍትሄ አይሆንም።
የተዛባውን የዶላር ምንዛሬ፣ ደረጃ በደረጃ፣ በብልሃትና በጥበብ ማስተካከል ያስፈልጋል። ለዘለቄታውም፣ የዶላር ምንዛሬ እንዳይዛባ፣ ከልቅ የብር ሕትመት መታቀብ ነው ሁነኛው መፍትሄ። በእርግጥ፣ የመንግስት ወጪና እዳ መረን ከተለቀቀ፣ ዞሮ ዞሮ በገፍ ብር ለማተም መሮጦ አይቀርም። ይህ እንዳይሆን፣ ለመንግስት ወጪና በጀት፣ ለብድርም፣ ጠበቅ ያለ ደህና ልጓም ማበጀት ያስፈልጋል።
የተዛባው የዶላር ምንዛሬ ሲስተካከል፣ በኤክስፖርት የሚገኘው ዶላር ይጨምራል። ኤክስፖርት በቅጡ እንዲያድግ ከተፈለገ ግን፣ የዶላር ምንዛሬን ብቻ ሳይሆን፣ የተዛባውን አገር ለማስተካከል መጣር ይኖርብናል። ከሁሉም በፊት፣ ሰላምንና ፀጥታን ማስፈን ይቀድማል። ካልሆነማ፣ ሌላው ሌላው ነገር ሁሉ ከንቱ ይቀራል። የንብረት ባለቤትነት መብትን ማክበርና ማስከበር፣ ይህንን ለማከናወን የሚያስችል “ሕግና ስርዓት”ን ማደርጀት ይገባል።
የጠ/ሚ ዐቢይ አስተዳደር፣ የመንግስትን በጀትና የውጭ ብድር ላይ ትንሽ ረጋ ትንሽ ቆጠብ ለማለት እየሞከረ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅዶቹም፣ አደናቃፊና አሰናካይ ችግሮችን ለማቃለል፤ ለግል ጥረትና ኢንቨስትመንት ተገቢውን ጥበቃ የሚሰጥ ትክክለኛ ህግና ሥርዓት ለማጠናከር እንዳለመም መንግሥት ገልጿል፡፡ ቃሉን አክብሮ ቢተጋና ቢሳካለት ነው የሚሻለው፡፡
አለበለዚያ፣ በድህነት ላይ በዋጋ ንረት ኑሯችን እየተናጋ፣ በወለድ ሸክም ተጨምሮበት፣ መከራ ይበዛል፡፡

Read 4729 times