Tuesday, 08 October 2019 09:21

የእንስሳት ሀብት ተዋጽኦ ኤግዚቢሽን ሊካሄድ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)


                ኢትዮጵያ ከ124 ሚ. በላይ የዳልጋ ከብት ቢኖራትም፣ በዓመት ወደ ውጪ የምትልከው 2 ሚ. ያህሉን ብቻ ነው

          ከ10 አገራት የተውጣጡ ከአንድ መቶ በላይ ተሳታፊዎች የሚገኙበት የኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ተዋፅኦ ኤግዚቢሽን ከጥቅምት 6 – 8, 2012 ዓ.ም ድረስ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ የሥጋ፣ የአሳ፣ የዶሮ፣ የንብና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ኤግዚቢሽኑ በእንስሳት ሀብት የገበያ ሰንሰለቶች ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኤግዚቢሽኑ አዘጋጅ የፕራና ኢቨንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነቢዩ ለማ ተናግረዋል፡፡
ይኸው አመታዊ የእንስሳት ሀብት የንግድ ትርዒት፣ ከቀደምቶቹ የሚለይበት ዋነኛው ምክንያት፣ የአሳና የማር ዘርፎችን ማካተቱ እንደሆነ የገለፁት አዘጋጆቹ፤ ኤግዚቢሽኑ በእንስሳት ጤና፣ በእንስሳት መኖ፣ የወተትና ሥጋ ዘርፍን በዘመናዊ መልክ በማሳደግ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአሳ ሀብት ቀደም ሲል በአውደ ርዕዩ ላይ ተሳታፊ እንዳልነበር የገለፁት አቶ ነብዩ፤ አገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የአሳ ምርት በመቀላቀል፣ ለምግብ ዋስትናችን አንዱ አማራጭ እንዲሆን ዘርፉን የማስተዋወቅ ሥራ ለመስራት ኤግዚቢሽኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የኤግዚቢሽኑ አዘጋጆች ሰሞኑን ባዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የየዘርፉ ማህበራት የሥራ ኃላፊዎች፤ ኤግዚቢሽኑ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ሀብት ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና በዘርፉ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ ያግዛል ብለዋል:: ኤግዚቢሽኑ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሰዎችና ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው ስለ ስራ ዕድሎቻቸውና ስለሚገጥሟቸው ችግሮች  የሚወያዩበትና መፍትሄ የሚሹበት ዕድልንም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
የፋኦ 2016 መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ የዶሮ ስጋ 0.66 ኪ.ግ፣ እንቁላል 0.36 ኪ.ግ፣ የበግና የፍየል ስጋ 1.4 ኪ.ግ ብቻ ሲሆን ይህም የአለም ዝቅተኛው ፍጆታ ነው ተብሏል፡፡


Read 2275 times