Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Print this page
Tuesday, 08 October 2019 09:31

“ይሁዲ ነኝን?” (ይሁዲ መሆን ምን ማለት ነው?)

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

በርካታ አይሁዳዊያን ህዝቦች አንድም በኦርቶዶክስነት ወይም በኢ-አማኒነት ቅርቃር መሀል ተቀይደው ይታሰባሉ፡፡ ሮሽ ሀሻናህ (Rosh Hashanah) የአይሁዳዊያን አዲስ አመት ወይም ደግሞ ዮም ኪፑር ሲቃረብ፣ ምናልባት አብዛኛዎቹ አይሁዳዊያን ከእምነትና ማንነት ጥያቄ ጋር ፊት ለፊት ይፋጠጣሉ:: የሬዲዮ ጋዜጠኛው ሚሼል ማርቲን “Am I A Jew?” (‹‹ይሁዲ ነኝን?››) በሚል ርዕስ የህይወት ታሪኩን/የራስ ምስሉን (Self portrait/Memoir) ያሳተመው ቴኦዶር ሮስን ኒው ዮርክ በሚገኘው ስቱዲዮው በእንግድነት ጋብዞት፣ በመጽሐፉና በጥያቄዎቹ ሀሰሳው ዙሪያ ቃለ መጠይቅ አድርጎለት ነበር፡፡ (ደራሲው በውይይቱ ማገባደጃ ከጋዜጠኛው ለሚሰነዘርለት መቋጫ ሃሳብ ኢትዮጵያን በድንቅ ማስረጃነት ይጠቅሳል፡፡) ከራዲዮ ፕሮግራሙ ‹‹በግርድፉ›› ተተርጉሞ እንዲህ ቀርቧል . . .
ማርቲን- እሺ እንግዲህ አሁን ደሞ ወደ እምነት ጉዳዮች እናመራለን፡፡ ስለ እምነት፣ ኃይማኖትና መንፈሳዊ ሃሳቦች የምንዳስስበት የፕሮግራማችን አንዱ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ ይህ ምሽት ደግሞ የሮሽ ሀሻናህ የመጀመሪያ ምሽት ነው፤ የአይሁዳዊያን አዲስ አመት ማብሰሪያ፤ ከቅዱሳኑ እለታት ሁሉ ላቅ ያለው ተብሎ የሚታወቀው እለት፤ አውደ አመቱ በናፍቆት የሚጠበቀው በአመቱ ውስጥ ለሚከበሩት ኃይማኖታዊ  ክብረ እለታት ሁሉ ማስጀመሪያ የአመቱ እጅግ እፁብ ድንቅ አሀዱ እለት በመሆኑ ነው፡፡
የዛሬው እንግዳችን ግን ከኃይማኖታዊ ክብረ እለታቱ ጋር በብዙዎች ዘንድ አሁንም ድረስ ያልተቋረጠውን ‹‹ይሁዲ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?›› የሚለውን እንቆቅልሽ እንደሚያነሱ ያስታውሰናል፡፡ እንግዳችን ቴኦዶር ሮስ ይባላል፡፡ “Am I a Jew? Lost Tribes, Lapsed Jews and One Man’s Search for Himself.” (‹‹ይሁዲ ነኝን? የጠፉት ነገዶች፣ የተረሱት አይሁዶችና ራሱን የሚፈልገው ሰው፡፡›› የሚል መጽሐፍ ጽፏል፡፡ እንኳን ደህና መጣህ፤ ግብዣችንን ተቀብለህ ስለተገኘህ በጣም እናመሰግናለን፡፡
ቴኦዶር ሮስ - እኔም አመሰግናለሁ ሚሼል፤ ስለጋበዝከኝ ደስ ብሎኛል፡፡  
ማርቲን - እሺ፤ በመጽሀፍህ አንደኛ መስመር የህይወት ታሪክህን መተረክ ስትጀምር ምን ብለህ እንደነግረኸን ታውቀዋለህ መቸም፤ እና ለምን ይሆን እኛን አንባቢዎችህን ይህን በመሰለ ስሜትን ሰቅዞ በሚይዝ እንቆቅልሽ ትረካ ያስጀመርከን? የዘጠኝ አመት እድሜ ታዳጊ ወጣት ሳለህ፣ ወላጅ እናትህ ወደ ክርስቲያንነት እንድትለወጥ አስገድደውህ እንደነበር ነው ገና በመክፈቻ ዓረፍተ ነገርህ ላይ የጻፍከው፡፡ በዚያን ወቅት የሆነው ምን ነበር?
ሮስ - መልካም፤ ወቅቱ ከምንኖርበት ከኒው ዮርክ ከተማ ለቅቀን ወደ ገልፍ ኮስት ሚሲሲፒ የመጣንበት ጊዜ ነበር፤ ከተማ ቀይረን ወደ ሚሲሲፒ ስንመጣ፤ እናቴ ከእንግዲህ ለማንም ቢሆን አይሁድ መሆናችንን ከመንገር መቆጠብ እንዳለብን ወስና ነበር፡፡  እኔም ኳየር ወደምዘምርበትና ቅዱስ ቁርባንም መውሰድ ወደ ጀመርኩበት ወደ ክርስቲያን Episcopal ትምህርት ቤት ተላክሁ፡፡ እናም ማንም ሲጠይቀኝ፣ በአንድ አምላክ ብቻ እንጂ በስላሤዎች የማላምን Unitarian ነበርኩኝ እላለሁ፡፡
ማርቲን - ግን ደሞ በመጽሐፉ ውስጥ የከተብከውን ገራሚ ሀሳብ ታውቀዋለህ፤ በእርግጥም ይህን መሰል ጥያቄ ለማጠየቅ ተገቢ የሆነ አንዳች ሂብሩአዊ ልህቀት በሚስተዋልበት ላህይ ያቀረብከው የማንነት/መሆን ጥያቄህ ‹‹እኔ ይሁዲ ነኝን?›› የሚል ነው፤ እናም እንዲህ ትላለህ፡- በሌላው እምነት ይህን ከዘር የተወረሰ የእምነት ፋይዳ ለመቀበል የሚፈጠረው ጥርጣሬና ገንጋኝነት፣ የራሱ የኃይማኖቱ መሰረታዊ መገለጫ ባህርይው ነው፡፡ ለምን እንዲህ አልክ?
ሮስ - መልካም፤ እንግዲህ እኔ ሌሎች ኃይማኖቶችን ወክዬ መናገር አልሻም፡፡ በበኩሌ እንደማምነው፤ በአይሁዳዊያን ህዝቦች ሁሉ መካከል አንድ አይነተኛ የወል የማንነት መገለጫ ታገኛለህ፤ ግን ደሞ ኃይማኖቱ ወይም እምነቱን ‹እንዲህ ነው ብሎ ለማለት› በቀላሉ ማብራራት ይከብዳል ነውና ነው፡፡ ወይም የሀሳብ መዐት በመደርደር ዘርዝረህ ልታስረዳው የምትችለው አይደለም፤ ምክንያቱም ለተለያዩ ሰዎች በጣም የተለያየ ነውና፡፡ ምናልባትም ሌሎች ለመቀበል የሚቸገሩትም ለዚያ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ እንደማስበው ካቶሊኮች ስለ ራሳቸው ያውቃሉ፤ የእነሱ ካልሆነው ጋር ያላቸውንም ልዩነት እንዲሁ፡፡ በአይሁድ ብዙ የተለያዩ ጉዳዮች ሁሉንም በአንድ ጊዜ መሆን ይችላሉ፡፡
ማርቲን - ጥሩ፤ መቸም በዚህ ዙሪያ የወጣውን የጥናት ውጤት ታውቀው ይሆናል:: እናም በዚህ Cohen Center for Modern Jewish Studies ባደረገው ጥናት መሰረት፤ በአሜሪካ ከሚኖሩ አስር ይሁዲዎች ስድስቱ ራሳቸውን እንደ ማንኛውም ሰው የሚቆጥሩ ወይም በቃ ትውልደ ይሁዲ ብቻ ነን (“just Jewish,”) ሌላ ትርፍ ነገር የለም የሚሉ አይነት መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡ እሳቤው በራሱ አጀብ የሚሰኝ ነው፡ እናም  ይኼ ደሞ በተለይ አንተ ወዳነሳኸው ነጥብ የሚቃረብ መልክ አለው፡፡
አንተ እውነቱን ፍለጋ ለመኳተን ያነሳሳህና በስፋት ያጠነጠንክበት አንኳር ተጠየቅም፤ አያት ቅድማያትህ አይሁድ መሆናቸውን እያወቅክ፣ በዘር የአይሁድ ማንነት እንዳለህ እምታውቅ ሆነህ፣ ነገር ግን ያው አንተው ራስህ እንደገለጽከውም፤ ከልጅነትህ ጀምሮ በኃይማኖቱ ውስጥ ሳትመላለስ፣ እምነቱን ሳትኖረው አድገህ “ራሴን በትክክል ይሁዲ ነኝ ብዬ ለመጥራት እችላለሁን ወይስ...?” የሚል ነው፡፡ እና ይህን መነሻ አድርገህም ነው፤ ይሁዲነት ፍንትው ያለ እንዲህ ነው የሚሉት ፍቺ የለውም ያልከው፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥቂት ማለት ትችላለህን?
ሮስ - መልካም፤ እኔ ማለት የፈለግሁት እንኳ ይሁዲነት ግልጽ የሆነ ፍቺ የለውም አይደለም:: በርግጥ ላንዳንዶች ይሁዲነት እንደዛ ነው:: ለዚያም ነው በግሌ በጉዳዩ ላይ በትኩረት እንዳውጠነጥን የተገፋፋሁት፤ እናም እንደ ይሁዲ ነገሮችን በደርዝ ለመረዳት በሞከርኩ ቁጥር፤ የዚያኑ ያህል ለኔው ለራሴ ውስብስብ እየሆነብኝ መጣ፡፡ በተረፈ በዘርፈ ብዙ አሳማኝ መመዘኛዎች ምክንያት እኔ እንደ አንድ ይሁዲ እንድቆጠር ነው እምሻው፡፡ በትውልዴ በደም ይሁዲ ነኝ፡፡ ወላጅ እናቴ ይሁዲ ናት፡፡ ባጠቃላይ የቤተ ዘመዶቼ ሁሉ የዘር ግንድ ከአይሁድ የዘር ሀረግ የሚመዘዝ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ኃይማኖቱን አብጠርጥሮ ለመተንተን አያበቃም - ኃይማኖቱ ውስጥ በአንድ በኩል በሆነ የአውደ አመት ክብር ወቅት እንበልና ለዮም ኪፑር አንዳንድ አጥባቂ ኦርቶዶክስ ይሁዲዎች (ultra-orthodox Jews) ኃጢአታቸውን ለማሰረይ (ነባሩን የአምልኮ ስርአት ሳያስተጓጉሉ አክብረው ጠብቀው ለማስቀጠል) ዶሮ በአናታቸው ላይ እያዞሩ ጸሎት ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምናልባት በጣም ‹‹ነጻ›› የሆኑት ይሁዲዎች (very liberal Jews) ለምሳሌ ሞባይል ስልካቸውን የሚደብቁበት (Sabbath manifesto sleeping bag) ሻባት/ሰንበት ሰንዱቅ በ7.99 ዶላር በመግዛት፣ የሳምንቱን መጨረሻ ቀናት በቃ በአርምሞ ብቻ ያሳልፋሉ፡፡
ማርቲን - ጥሩ፤ ሌላው ያነሳኸው ነጥብም በጣም ልብ የሚነካ እንዲሁም ውኃ የሚያነሳ ነው፤ ምክንያቱም ሚሊዮኖች ህይወታቸውን የከፈሉበትን የእልቂት ኩነት የሚያስታውስ ይዘት አለውና… በዚሁ ባንተ ጥያቄ ጉዳይ፡፡
ሮስ - እውነት ነው፡፡ ማለት ሁልጊዜም  እንድናስታውሰው የሚያስገድደን የሆሎከስት ጠባሳ አለ፤ ይህን  እኔም በቅርብ የማውቀው ነው፤ በእናቴ የተነሳ፡፡ እና እነዚህ የእለት ተእለት መትከንከኖች በደመነፍስ የተሰነዘሩ ፖሊቲካዊ መልክ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ ወይም - በመጽሀፌ ውስጥ ለማካተት የሞከርኩት የሆሎከስት ትዝታዎችን የሚያሳዩ የእጅ ጽሑፎች የሚያመለክቱት ነገር ቢኖር፣ እንደማስበው የእናቴን ህይወት ያመሰቃቀሉ፤ በዚሁም የተነሳ በተለያየ ሁኔታ ከኃይማኖቷ ጎትተው ያወጧትን መንስኤዎች ነው፡፡ እናም እሷ በቃ አሜሪካዊ ብቻ መሆንን ነበር እምትፈልገው፤ ይህን ስል ብዙም ደስ አይለኝም ግን ግልጽ ባለ መንገድ ለማስረዳት ስል ነው፡፡ እናም ለእናቴ በይሁዲነቷ በተለየ ነገድ ተቀንብባ መታየቷ፣ በተለይ ከሆሎከስት ጋር በተያያዘ፤ እሷ ለመሆን የምትፈልገውን አንዲት አሜሪካዊት ዜጋ የመባል መሻቷን ያሳጣት ጉዳይ ነው፡፡
ማርቲን - እንደው በመጽሀፍህ የተጠቀሰን አንድ ቃል እንድታብራራልኝ ከፈቀድክ.. ሌሎችንም ያካተተ ነው ብዬም አስባለሁ:: ገና በአርእስቱ ላይ ነው ያለው፡፡ “የተረሱ ይሁዲዎች” ነው የሚለው፡፡ አንተኑ ራስህንም እንዲሁ እንደ ተዘነጋ ይሁዲ አድርገህ ነው የምትገልጸው፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥቂት ልታወጋን ትችላለህ? ምን ማለት ነው?
ሮስ - መልካም፤ እንደሚመስለኝ ይህ ጉዳይ የሚመለከተው እኔን ብቻ አይደለም ብዬ አስባለሁ፤  ቅድም አንተም ጠቁመኸዋል፤ በአሜሪካዊያን ይሁዲዎች ላይ ስለተደረገው ጥናት፡፡ በአሜሪካ ከሚኖሩት አይሁዳዊያን 60 ከመቶው ራሳቸውን ‹‹ይሁዲ ብቻ›› ብለው ነው የሚቆጥሩት ብሏል፤ የጥናት ውጤቱ ነው ያልከው፡፡ እኔ እንደማስበው፣ ሌሎችም በጥናቱ ያልተካተቱ አይነተኛ መልካቸው ይፋ ሳይወጣ፣ እውነተኛ ማንነታቸው ተድበስብሶ የሚኖሩ በርካታ አይሁዳዊያንም አሉ፡፡ እነሱን ብዙ እየቆፈርን በሄድን ቁጥር በየማዕቀፉ ተኮድኩደው ሲኖሩ እናገኛቸው ይሆናል:: በእርግጥ በጥናቱ የተጠቀሱቱ የተባሉትም ቢሆኑ ራሳቸውን በዚህ መልኩ መግለጻቸው አሉታዊ ጎን አለው ብሎ ማሰቡም ያን ያህል አስፈላጊ ሆኖ አይታየኝም፡፡ ለኃይማኖቶችም በለውጥ ሂደት ተጽእኖ ውስጥ ማለፍ ግድ ይሆናል፡፡ በተለይ እንዲህ እንደ አሜሪካ ባለ የትየለሌ ያኗኗር ባህል ውስጥ ስንኖር ደግሞ ለራሳችን የተለያዩ የማንነት መገለጫዎችን ለመፍጠር የሚያስችለን አመቺ ሁኔታ ነው ያለው፡፡
ማርቲን - ይቅርታ የፕሮግራማችን ታዳሚያን፤ እያወጋን ያለነው ከ‹‹ይሁዲ ነኝን? የጠፉት ነገዶች፤ የተረሱት አይሁዶችና ራሱን የሚፈልገው ሰው›› መጽሐፍ ደራሲ ቴኦዶር ሮስ ጋር ነው፤ ውይይታችንን ስላናጠብኩ በድጋሚ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ ያም ሆኖ መጨረሻውን ለመናገር አልችልም፤ ምክንያቱም የመጽሐፉ ጭብጥ የሚያጠነጥነው ለጥያቄዎች ምላሽ ፍለጋ በተደረገ ያልተቋረጠ ሀሰሳ ላይ ነውና - ረዥም ጉዞ፡፡  . . . በረዥሙ ጉዞ መንገዶችህ መሀል ብዙ ወዲያ ወዲህ ተመላልሰህበታል፡፡ እናም ስለ ለዘብተኛ ይሁዲዎች (ultra-liberal Jews) እና ስለ ጽንፈኛ ኦርቶዶክስ ይሁዲዎች (ultra-orthodox Jews) እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጥጎች ድረስ ይከነዳልም ጉዞህ፡፡ ለመሆኑ ግን አንተው ራስህ...ይህን ጥያቄ በምን መልኩ ማቅረብ እንዳለብኝ አላውቅም ? ግን የግድ መጠየቅ ደሞ አለብኝ. . . እሺ አዎን፤ እናስ አንተ ራስህ ስለ ማንነትህ ለማወቅ በረዥሙ ስትቀዝፍ ከርመህ መልህቅ እሚያስጥል ወደብ ላይ ደረስህን? ማለት በመጨረሻ ጥያቄህን ምን በሚል ምላሽ ደመደምከው? ይቅርታ ይህን ለመጠየቅ እችላለሁ አይደል?
ሮስ - መልካም ነው፡፡ ግን ላንተ እምሰጠው አጥጋቢ ምላሽ ይኖረኝ እንደሁ አላውቅም፤ ከአክብሮት ጋር፡፡ለእኔ በበኩሌ ለራሴ የነገርኩት ምን ነበር--- በየሀገራቱ ስጓዝ፣ ለጥያቄዬ ምላሽ ፍለጋ እስራኤል ስደርስ፣ ምንጊዜም ለልቤ እማወጋው፤ “ቴኦዶር አንተ የታሪክ ተመራማሪ አይደለህም፤ አንተ ራባይ አይደለህም፤ አንተ ዘጋቢ አይደለህም፤ አንተ ዳኛ አይደለህም” እያልኩ ነበር፡፡ እናም ወደ አንድ ፍጻሜ የሚያደርስ ድምዳሜ ያለውም አይደለም፡፡ እሚሰማኝም ይህ ነው፡፡ መጽሐፉን እስከመጨረሻው ድረስ አንብበኸው ከሆነ መልሴን አስፍሬያለሁ:: ተጠይቆ ያልተሰለቀ አንድም የቀረ አሳብ ያለ አይመስለኝም በመጽሐፌ፤ሆኖም ግን ይሄ የእኔ የግል ጉዞ ነው፤ ግዘፍ በነሳ ጥያቄ፣ ብርሃንና ጥላ መካከል የተደረገ ሀሰሳ፡፡ እናም ጉዞው አንድ ቁርጥ ያለ እሚያበቃበት ነጥብ ይኖረው ይሆን? እንጃ ፡፡
ማርቲን - እሺ ምን ትመክራለህ? ወይም ምንድነው የምታስተላልፈው መልእክት… ለሌሎች አንተን አይነት ሰዎች እና አንተ ያነሳኻቸው መሰል ጥያቄዎች ላላቸው? ማለት እነዚህ ጥያቄዎች በምንኖርበት በአሜሪካ ውስጥም ያሉ ናቸውና፡፡  የምትለግሰው ምክር ቢጤ ይኖርህ ይሆን?     
ሮስ - ለሌሎች ምክር ለመስጠት እምበቃ ነኝ ብለህ ነው . . .
ማርቲን - አዎና!
ሮስ - በጁዳይዝም እምነታቸው ለሚንገጫገጩቱ ማለት ነው?
ማርቲን - እኒህን መሰል ጥያቄዎችን ለሚጠይቁ፡፡ አዎን፡፡
ሮስ - እኔ እምለው ከናንተ እሚጠበቀውን የየድርሻችሁን ተወጡ ነው፡፡ በግሌ በማንበብ ብዙ ጊዜዬን አሳልፋለሁ፡፡ አቅም በፈቀደው መጠን የተለያዩ የአይሁድ ማህበረሰብ አባላትን ተዘዋውሬ በማግኘት እወያያለሁ እናም ከእነሱ የተለያየና እጅግ የተራራቁ የህይወት ልምዳቸውን እቀስማለሁ፡፡ ስነሳም ጀምሮ የወሰንኩት ምንድነው… እኔ እማስበውን ወደ ጎን ትቼ የነሱን በጥሞና ለማስተዋል ነው፤ እና አሁንም ስለ 60 ከመቶዎቹ ‹‹ይሁዲ ብቻ›› ስለተባሉትም ሆነ ስለሌሎቹ ገና ያልደረስኩባቸው ሁሉ ጥግ ድረስ ለመሄድና ዘርፈ ብዙ እይታና ግንዛቤያቸውን ለመቅሰም ነው መሻቴ፡፡ እናም በራሴን ፍለጋ ጉዞዬ ውስጥ ለልቦናዬ የተገለጠልኝን፣ ስሜት የሰጡኝን፣ ወደ እውነታው የሚመሩኝ ያልኳቸውን ፍሬ ነገርና ፋይዳዎች ሳሰባስብ ሳደራጅና ሳሰናስል ነው የከረምኩት፡፡
ነጻ አሳቢ ነኝ እናም የሚሰማኝ አንተ “ultra-liberals” እንዳልካቸው እጅግ ሰላማዊ ሰዎች ነው፤ ልክ እስራኤል ውስጥ እንዳገኘሁዋቸው በድንቅ ፀጋና የእምነት መስተጋብር ተፀልለው የኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ይሁዲዎች ወይም  ደግሞ crypto Jews እንደሚባሉት በኒው ሜክሲኮ እንደሚኖሩቱ፡፡እነርሱ በህይወታቸው ይሁዲነትን የሚያጣጥሙበትና በውስጣቸው ያሰረፁበት ድንቅ ምልካቴና ገድል፣ እኛ እንዲህ በቀላሉ በየትኛውም ምኩራብ ሄደን እምናገኘው አይደለም፡፡
ማርቲን - እሺ.
ሮስ - እናም ምናልባት መደረግ ያለበት ምንድን ነው ያልከኝ… ይኸው ነው፤ ፍለጋ ከተነሳህ በጽኑ ትጋት መጓዝ መቻል… የምር ሀሰሳ ጁዳይዝም ካሻህ፡፡
ማርቲን -መልካም ሮሽ ሀሻናህ ልበልህ ወይስ ላሻና ቶቫህ?
ሮስ - እሺ፡፡ አዎን እንደዛ ነው እሚባለው. . .
ማርቲን - ይሄ የያዝከው ኮሸር ነው? (kosher በአይሁድ እምነት ያመጋገብ ስርአት መሰረት የሚዘጋጅ ምግብ ነው)
ሮስ - እውነት ነው፤ ኮሸር ነው፡፡ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ማርቲን - እሺ እስካሁን አብሮን የቆየው “Am I a Jew? Lost Tribes, Lapsed Jews and One Man’s Search for Himself.” በሚል ርዕስ የህይወት ታሪኩን ጽፎ ያሳተመው ደራሲ ቴኦዶር ሮስ ነበር፡፡ ቴኦዶር የ “Men’s Journal” መጽሄት ዋና አዘጋጅም ነው፡፡ እዚህ ኒው ዮርክ ከተማ የሚገኘው ስቱዲዮአችን ድረስ መጥቶ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ፈቃደኝነቱን ስለለገሰን እናመሰግናለን፡፡ ሻና ቶቫ ቴኦዶር ሮስ (መልካም አዲስ አመት)!
ሮስ - በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ለመላው የአይሁድ እምነት ተከታዮች፤ እንኳን ለሮሽ ሀሻናህ በሰላም አደረሳችሁ፡፡ መልካም አዲስ አመት!!

Read 1337 times