Print this page
Tuesday, 08 October 2019 09:51

‹‹በሰዎች ደግነት ላይ ፅኑ እምነት አለኝ››

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አዜብ ወርቁ - ደራሲ፣ ተዋናይትና አዘጋጅ

             በጥበቡ ዓለም የምፈልገውን ዓይነት ሕይወት መምራት የቻልኩት፣ በእጄ የሚገቡትን ዕድሎች ሁሉ በቅጡ በመጠቀሜ ነው ብዬ አስባለሁ:: ተስፋ አለመቁረጤና ቀና ከሆኑ ሰዎች ድጋፍ ማግኘቴም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በዚያ ላይ እድለኛም ነበርኩ። የራሴን የመጀመሪያ ትያትር ለመሥራት ስነሳ በፍርሃትና በጥርጣሬ ተሞልቼ፣ ስንዝር እንኳ መራመድ አቅቶኝ ነበር:: ነገር ግን በሥራዬ የሚያግዙኝና የሚደግፉኝ ሰዎች ከተፍ አሉልኝ። ለዚህ ነው በሰዎች ደግነት ላይ ጽኑ እምነት ያለኝ፡፡  
የተወለድኩትና ያደግሁት በአዲስ አበባ፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በሚባለው አካባቢ ነው:: በወቅቱ የከተማዋ ዳርቻ ቢሆንም የበርካታ ከያኒያን፣ ሙዚቀኞች፣ ጸሀፍትና ተዋንያን የትውልድ ስፍራ ነው። ከእነዚህ ከያኒያን መካከል አንዳንዶቹን አውቃቸው ነበር:: የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድራማዎችን መስማትና መመልከት ነፍሴ ነበር፡፡ ማትሪክ ከተፈተንኩ በኋላ ተዋናይ የመሆን ፍላጎት ስለጸናብኝ፣ ክረምት ላይ በተስፋዬ ሲማ የሚሰጠውን የአራት ወር ትምህርት ለመውሰድ አመለከትኩ:: ከተመዘገቡት 300 አመልካቾች መካከል ለሥልጠናው የሚቀበሉት ሰባ ያህሉን ብቻ ስለነበረ አይቀበሉኝም የሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር፡፡ ለኮርሱ እጩ ሆኜ ብመረጥ እንኳን ገና የትወና ፈተና እንደሚጠብቀኝ አውቃለሁ። አብዛኞቹ አመልካቾች ደግሞ ለትወና እንግዳ አልነበሩም። እኔ ግን ኃይለኛ አንባቢ እንጂ ከትወና ጋር ከነአካቴውም አልተዋወቅም ነበር፡፡ እናም በወቅቱ በማነበው መጽሐፍ ላይ ተመስርቼ ለፈተና የማቀርበውን ቃለ ተውኔት ለማዘጋጀት ወሰንኩ፡፡ መድረክ ላይ ስወጣ ግን ተረብሼ ስለነበር ምን አድርጌ እንደወረድኩ ፈጽሞ አላስታውስም፡፡ ያም ሆኖ ማለፊያ ድምጽና ትክክለኛውን ሥራ ሳላሳይ አልቀረሁም መሰል ተቀበሉኝ፡፡ በዚህም እድለኛ ነኝ እላለሁ:: ምክንያቱም ያንን ሥልጠና ባልወስድ ኖሮ ፈጽሞ ተዋናይ እንደማልሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡
ኮርሱን ከጨረስኩና ማትሪክ መውደቄን ከሰማሁ በኋላ፣ አባቴ ማታ ማታ፣ ትምህርቴን እንድቀጥል ይፈልግ ነበር፡፡ እኔ ግን ቀልቤ ሁሉ ትወና ላይ ነበር፤ አትኩሮቴን ሌላ ምንም ነገር ላይ ማድረግ አልቻልኩም፡፡ አባቴ በዚህ መከፋቱ አልቀረም፡፡ ለትወና ያለኝን ፍቅር ያውቅ ስለነበር ግን ከትያትር እንድለያይ  አላስገደደኝም፡፡
የመጀመርያ ትወናዬን አሀዱ ያልኩት ከአፍለኛው የትያትር ክለብ በቀረበልኝ ግብዣ ሲሆን ‹‹ከዳንኪራው በስተጀርባ›› በተሰኘው ትያትር ላይም መሥራት ጀመርኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በብሔራዊ ትያትር የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ሥራ በሆነው ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› ትያትር ላይ በተጋባዥ ተዋናይነት ለመሥራት ተመረጥኩኝ፡፡ በጥበቡ ዘርፍ እንደ ታቦት ከሚታይ ታላቅ ባለሙያ ጋር በመሥራቴ፣ ራሴን እንደ እድለኛ እቆጥራለሁ። በዚህ አጋጣሚም የቻልኩትን ያህል ለመማር ሞክሬአለሁ:: በማከታተልም በትያትሮች፣ በቴሌቪዥን ድራማዎች እንዲሁም በፊልሞች ላይ መተወኔን ገፋሁበት፡፡ ከትወና በተጨማሪ ከሴት የሙያ ጓደኞቼ ጋር በመሆን ትያትር ጻፍን፡፡ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ስኬታማ የትያትር ጸሐፊዎች ግን የጻፍነው ትያትር ቀሽም መሆኑን አረዱን፡፡ በውስጤ ከፍተኛ የመጻፍ ስሜት ቢታገለኝም ለጊዜው ራሴን ከመጻፍ  ገታሁ፡፡
መጻፍ ባቆምም ፊልምና ትያትሮች ላይ መተወንና መመልከቱን ቀጠልኩበት፡፡ ለባለቤቴ ምስጋና ይግባውና፣ የፈረንሳይ ፊልሞች ቀንደኛ ተመልካችና አድናቂ ሆንኩ፡፡ በ1997 ዓ.ም ወደ አማርኛ ቢተረጎም ግሩም ትያትር እንደሚወጣው ያሰብኩትን አንድ የፈረንሳይ ፊልም ተመለከትኩ፡፡ ወዲያውኑ ባለቤቴ እያገዘኝ ፊልሙን ወደ አማርኛ መተርጎም ብጀምርም፣ ትርጉሙን የማጠናቀቅ ድፍረትና ብርታት አልነበረኝም፡፡ ሁለት ጓደኞቼ ግን በሥራው እንድቀጥል ገፋፉኝ፡፡ እነዚህ ጓደኞቼ ሥራውን ለመድረክ የምናበቃበትን ሁኔታም ጭምር እንዳስብ አግዘውኛል፡፡  የማታ ማታም፣ እነሱ ብርታት ሆነውኝ ተውኔቱን ጽፌ ለማጠናቀቅ በቃሁ፡፡ ታላላቅና ታዋቂ ሰዎች ባደረጉልኝ ድጋፍና እገዛም ‹‹ስምንቱ ሴቶች›› የተባለው ትያትር ጥቅምት 3 ቀን 1998 ዓ.ም በብሔራዊ ትያትር ተመረቀ፡፡
‹‹ስምንቱ ሴቶች›› በኢትዮጵያ በሴቶች ብቻ ተዘጋጅቶ የቀረበ የመጀመርያው ትያትር ሲሆን ተዋናዮቹ፣ አቀናባሪዎቹና አዘጋጆቹ ሁሉ ሴቶች ነበሩ፡፡ እኔ በጸሀፊነት፣ በአዘጋጅነትና በትወና፤ ሐረገወይን አሰፋ ደግሞ በረዳት አዘጋጅነትና ተዋናይነት የሰራን ሲሆን ድርብወርቅ ሰይፉ፣ ፍሬሕይወት መለሰ፣ ቤተልሄም ታዬ፣ አስቴር ደስታ፣ ህሊና ሲሳይና ፍቅርተ ደሳለኝ በተዋናይነት ተሳትፈዋል፡፡ ይሄን ትያትር ለመድረክ ለማብቃት ስንለፋ ትልቅ እገዛ ካደረጉልን እውቅ የትያትር ባለሙያዎች መካከል በተለይ ጌትነት እንየው፣ ሱራፌል ወንድሙ፣ አለሙ ገብረአብና ግሩም ዘነበ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አቅም ባጎለበቱ ሴቶች ዙርያ የሚያጠነጥን ትያትር ለመደገፍ የሚፈልጉ ኩባንያዎችና ድርጅቶችም የበኩላቸውን እገዛ አድርገውልናል፡፡ ‹‹ስምንቱ ሴቶች›› ሁለት ዓመት ሙሉ ከመድረክ ሳይወርድ የቆየ ሲሆን ለ18 ወራት በብሔራዊ ትያትር፣ ለስድስት ወራት ደግሞ በቢጂአይ ኢትዮጵያ ስፖንሰር አድራጊነት፣ በክልል ትያትር ቤቶች ታይቷል:: ሙሉ ልብና አትኩሮታችንን ሥራችን ላይ ስናደርግ፣ የሚያግዙን ሰዎች ከተፍ እንደሚሉ አምናለሁ፡፡ ‹‹በስምንቱ ሴቶች›› ትያትር ዝግጅት የተረዳሁትም ይሄንኑ ነው፡፡
ከዚህ ትያትር በኋላ ብዙ እድሎች ተከታትለው መጡ፡፡ እኔን የረዳኝ እያንዳንዷን ዕድል በወጉ መጠቀሜና ይዞልኝ የመጣውን የመማርና ትስስር የመፍጠር አጋጣሚ በፀጋ መቀበሌ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ በአፔክሳርት አማካኝነት ግሩም የሆነ የአንድ ወር የሥነ ጥበብ ትምህርት በኒውዮርክ ከተማ የመካፈል፣ በስዊድንና በኬንያም በታሪክ አጻጻፍ ፌስቲቫል ላይ የመሳተፍ፣ ከዚያም ቴዎድሮስ ለገሰ ከተባለ የፊልም ባለሙያ ጋር በመተባበር ‹‹ዳያስፖራ›› የተሰኘ ትያትር የመጻፍና የማዘጋጀትን ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ይሄን ትያትር የአገር ውስጥና የዳያስፖራ ተዋናዮችን በመጠቀም የሰራነው ሲሆን በአዲስ አበባ ሦስት ትያትር ቤቶችና በክልሎች 38 መድረኮች ላይ በአስገራሚ ጥድፍያ፣ አንዳንዴ በቀን ሦስቴ እያቀረብን አሳይተናል፡፡ ሌላው ከፈረንሳይኛ የተተረጎመውና ራሴ ያዘጋጀሁት ‹‹የሚስት ያለህ›› ትያትር ደግሞ መጋቢት 29 ቀን 2003 ዓ.ም ተመርቆ፣ በአዲስ አበባና በመላው አገሪቱ በሚገኙ የክልል ትያትር ቤቶች ለእይታ በቅቷል:: የቴሌቪዥን ድራማ ላይ እንድሳተፍ ተጋብዤም የ‹‹ገመና›› ድራማን የመጨረሻ 20 ክፍሎች የጻፍኩ ሲሆን በሂደቱም የቴሌቪዥን ድራማ እንዴት እንደሚጻፍ ተምሬበታለሁ፡፡ ከዚያም ‹‹ኮንዶሚኒየሙ›› የተሰኘ የፊልም ስክሪፕት ጽፌ ፊልም ተሰርቶበታል፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲተላለፍ የነበረውን ‹‹ዳና›› የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማም ጽፌአለሁ፡፡ ወደፊት ለዓለም አቀፍ ተመልካቾች የሚሆኑ ትላልቅ ፊልሞችን የመሥራት እቅድ አለኝ፡፡ ፊልሞቹም ዘላቂ ተወዳጅነት ያላቸውና የመጪውን ትውልድ ቀልብ የሚስቡ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ። ከልምድ የቀሰምኩትን ትምህርት ለማዳበር ወደ ት/ቤት የመመለስ ከፍተኛ ጉጉትም አለኝ፡፡   
የትያትር ጥበባት ሥራዬን በፍቅር እወደዋለሁ፡፡ ስኬቴ ትልቅ ደስታ ይሰጠኛል:: የላቀ እርካታ የሚያጎናጽፈኝ ግን በወረቀት የጻፍኳቸውን ሥራዎች ወደ መድረክ ወይም ወደ ፊልም በማምጣት ሕይወት ስዘራባቸው ነው፡፡ እነዚህ ብዙ እድሎች ወደ እኔ የመጡት በአጋጣሚ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ምናልባት በትጋት ስለምሰራም ይሆናል፤ ለሁሉም እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፡፡
ሁለት ልጆች ስላሉኝ በጣም እድለኛ ነኝ:: እነዚህ የፈጣሪ ስጦታ የሆኑ ወንድና ሴት ልጆቼ፣ የደስታዬ ምንጮች ናቸው፡፡ ሕይወት በፈተና የተሞላች ብትሆንም፣ ከሁሉም በእጅጉ የፈተነኝ ግን ፋታ የማይሰጥ ሥራዬንና ቤተሰባዊ ኃላፊነቴን አመጣጥኜ መጓዝ ነው፡፡ በሥራ መወጠሬ የጥፋተኝነት ስሜት እየፈጠረብኝ የምናደድበት ጊዜ አለ፡፡ የምፈልገውን ዓይነት እናት አልሆንኩም ብዬም እጨነቃለሁ፡፡ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ግን በቤት ውስጥ የሚያግዘኝ ግሩም የሆነ ደጋፊ ባል ሰጥቶኛል፡፡
የመጪው ትውልድ ሴቶች ልበ ሙሉ፣ ራሳቸውን ችለው የሚቆሙ፣ በቅጡ የተማሩና አስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላቸው እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አገራችን አስተማማኝና ንፁህ መሠረተ ልማት ስትገነባ የማየት ከፍተኛ ጉጉት አለኝ፡፡ ለምሳሌ ምርጥ ፓርኮችና ጥሩ መንገዶችን ጨምሮ ሌሎች ነገሮች እንዲሟሉ እመኛለሁ፡፡ ይህቺ ታላቅ አገር በመንፈስ አነቃቂነቷ ትቀጥል ዘንድ ንፁህና አረንጓዴ አካባቢ ለመፍጠር፣ ጊዜና ገንዘባችንን ማፍሰስ ይኖርብናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገራችን የእድገት ሂደት ውስጥ የጥበባችን ምንጭ የሆነውን የዳበረ ባህላችንን እንደምንጠብቅ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ምንጭ፡- (“ተምሳሌት፤ ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች”፤ 2007 ዓ.ም)

Read 1281 times
Administrator

Latest from Administrator