Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Print this page
Tuesday, 08 October 2019 10:01

ዱባይን በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ዱባይን አየነው ከእግር እስከራሱ
አንድ ቀን አይኖር ገንዘብ ከጨረሱ
በጣም ደስ ያሰኛል ከሀገር ሲመለሱ፡፡
ዱባይ የበረሃ ገነት ናት፡፡ በስርአት በታነጹና ባማሩ ህንጻዎች የተንቆጠቆጠች ማራኪ  ከተማ ናት፡፡ ዱባይ ከዓለማችን ምርጥና ዘመናዊ ከተሞች አንዷ ለመሆን የቻለችው ደግሞ ባለፉት 20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ መሆኑ አጃኢብ ያሰኛል፡፡ አፈር ከሰው ሀገር አምጥተው የሰሩት የአበባ ምንጣፍ የመሰለ የመናፈሻ ሥፍራቸው ታይቶ አይጠገብም፡፡ ተአምር ነው፡፡
እኛም የነሱን ተሞክሮ ብንወስድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራችንን መቀየር ማዘመን እንችላለን፡፡ አገራችን እንደ ዱባይ አፈርም ሆነ ሌላ የተፈጥሮ ሀብት ከሌላ አገር ማምጣትም ሆነ መዋስ አያስፈልጋትም፡፡ በሁሉም የተፈጥሮ ጸጋ የታደለች ናት፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ተባብሮ በትጋት መስራት ብቻ ይመስለኛል፡፡
አንዳንድ ያስገረሙኝና የታዘብኳቸው ነገሮች
1. ዱባይ የትራፊክ ፖሊስ እምብዛም የማይታይባት ከተማ ብትሆንም፣ ሁሉም ተሽከርካሪ ያለ ችግር ነው የሚተላለፈው፡፡ የትራፊክ ስርአቱን በሳተላይትና በካሜራ ነው የሚቆጣጠሩት፤
2.  የህንድና የፓኪስታን ዜጎች የሚበዙ ቢሆንም፣ ዱባይ  የአለም ህዝቦች ደሴት ናት ማለት ይቻላል፤
3. ከተማዋ ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላት በመሆኑ ሙቀቱ ሲጠናባችሁ ወደ ቤት ሮጣችሁ መግባት ነው፡፡ ሁሉም ቤቶች፣ መፀዳጃ ቤቱም ጭምር አየር ማቀዝቀዣ (ኤር ኮንዲሽኒንግ) ስለተገጠመላቸው ይቀዘቅዛሉ፤
4. የገበያ ስርአታቸው አስደናቂ ነው፡፡ “1-10” እና “1-20” የሚባሉ ትላልቅ የገበያ መደብሮች አላቸው፡፡ በእነዚህ መደብሮች ውስጥ የሚገኝ የማንኛውም (ነጠላ) እቃ ዋጋ ከአስርና ከሀያ ዱርሀም አይበልጥም፡፡
ጫማና ልብስ ስትሸምቱ እንደ ሁኔታው፣ ቲ-ሸርት ወይም ሽቶ አሊያም ሌላ ዕቃ  በነጻ ሊሰጣችሁ ወይም ሊመረቅላችሁ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ አራት ቢራ ከጠጣችሁ፣ አንድ ቢራ በነፃ ይጨመርላችኋል፡፡ (እኛ አገር ግን ሳጥን ብትጠጡም--)
5. የምድር ውስጥ (ሜትሮ) ባቡራቸው ብዛትና ፍጥነት በጣም አስገራሚ ነው፡፡  ሴትና ወንድ ታዲያ በአንድ ባቡር  አይሳፈሩም፤ ለየብቻቸው ነው፡፡
6. በዱባይ ከሰው ጋር ከተጣላችሁ (ጠበኛው ማንም ይሁን) ሁለታችሁም ናችሁ የምትታሰሩት፤ ስለዚህ ሰው ነገር ከፈለጋችሁ፣ ትቶ  መሮጥ ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡
7.  ዱባይ በማሳጅ ሰበብ ወሲብ የሚፈጸምበት ከተማ ናት፤ ወሲብ ቀስቃሽ የሴቶች ምስል የታተመበት ቢዝነስ ካርድ በዱባይ መንገዶችና በቆሙ መኪኖች ላይ አይጠፋም፡፡ የሀገሪቱ ማዘጋጃ ቤት በየሌሊቱ ለቅሞ ለመጣል ቢሞክርም በማግስቱ ግን ያው ነው፡፡ ወደ ማሳጅ ቤቶቹ ሲኬድ ሴቶቹ መጀመሪያ የሚያቀርቡት ጥያቄ ‹‹ወሲብ ትፈልጋለህ?›› የሚል ነው፡፡
8. ዱባይ በሁሉም ነገር ለዜጎቿ ቅድሚያ ትሰጣለች፤ የማሳጅ ቤት አገልግሎትን ጨምሮ ማለት ነው፡፡
9. በዱባይ በሚገኘው የዓለም ረዥሙ ህንጻ (በርጂ ከሊፋ) ስር በምሽት የሚታየው የውሃ ላይ ዳንስ፤ ርችትና ሙዚቃ በቃላት ለመግለጽ ያዳግታል፤ እንደው በደፈናው ነፍስን በሃሴት ጮቤ ያስረግጣል ቢባል ይቀላል፡፡
10. ከንጹህ ወርቅ ብቻ የተሰራ ረዥም ካፖርት (የሚለበስ ነው) በዱባይ የወርቅ መሸጫ መደብር ውስጥ ተመልክቻለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ካፖርቱ አጠገብ በመቆም ፎቶ ይነሳሉ፡፡
11. በዱባይ በወርቅ ተንቆጥቁጠው ዘመናዊ መኪና የሚያሽከረክሩ፤ አስገራሚ የግል ሱቆችና  መኖሪያ ቤት ያላቸው ኢትዮጵያውያን  እንስቶች የመኖራቸውን ያህል፣ ስጋቸውን የሚቸረችሩና አልባሌ ህይወት የሚመሩ እንዳሉም ተረድቼአለሁ፡፡
12. በዱባይ የሀገራችን ዘፈኖች የሚቀነቀኑባቸው ውብ ናይት ክለቦች ሞልተዋል:: ነገር ግን እኔን ያስገረመኝ በኢምሬት ሌላዋ ከተማ በአጅማን ያየሁት ነው፡፡ በዚህች ከተማ የሁሉም አገራት ናይት ክለቦች ከሞላ ጎደል በአንድ ቦታ ላይ ተሰባስበዋል፡፡ ከናይጄሪያ ናይት ክለብ ትይዩ የኢትዮጵያ ናይት ክለብ ይገኛል፡፡ ናይት ክለቦቹ እንደ ሀገራችን የሀረር ጀጎል ግንብ በታጠረ ግንብ ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡
በኢትዮጵያውያን ናይት ክለብ ጎራ ባልኩበት ሰዓት፣ በጣም የተዋቡና የሚያማምሩ የሀገሬ ልጆች፣ በሚያስገርም የአዘፋፈን ስልትና ውዝዋዜ የሚያቀርቡት ኢትዮጵያዊ ዘፈኖች በእጅጉ መስጦኛል፤ የአገር ቤት ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ ታዲያ ዘፋኞቹንም ሆነ ተወዛዋዦቹን ገንዘብ መሸለም የተከለከለ ነው፤ መሸለም የሚቻለው ከናይት ክለቡ የሚገዛውን የአበባ ጉንጉን  ብቻ ነው፡፡ የአበባ ጉንጉን አንገታቸው ላይ በማጥለቅ መሸለም ይቻላል፡፡ ናይት ክለቡን ኢትዮጵያውያን፤ ሱዳኖችና የዱባይ ጥቁር አረቦች በብዛት እንደሚጎበኙት ለመረዳት ችያለሁ፡፡
13. ሌላው ያስተዋልኩት በዱባይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ጉዳይ በጥብቅ የሚከታተሉ መሆናቸውን ነው፡፡ በዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን መምጣት መደሰታቸውን ሳይጠየቁ ነው የሚናገሩት፡፡
አስፋው መኮንን
(‹‹የሀበሻ ቀልዶች›› መጽሐፍ ደራሲ)


Read 1303 times