Tuesday, 08 October 2019 10:04

እየተፍረከረኩ ያሉ ፓርቲዎች

Written by  (አ.አ)
Rate this item
(1 Vote)

  በኢሕአዴግ እንጀምር፤ የአራት የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ ግንባር ነው፡፡ ግንባሩ የተፈጠረ ሳይሆን የተሰራ ነው፡፡ የተሰራ ነው ስል የርዕየተ ዓለም፣ የአላማ፣ የግብ፣ ወዘተ ልዩነት ያላቸው፣ ራሳቸውን የቻሉ ነፃ ድርጅቶች ተገናኝተው፣ ተመካክረውና ተደራድረው፣ አንተ ይህን ታደርጋለህ፣ እኔ ደግሞ ይህን እፈጽማለሁ ብለው በአጭርም ይሁን በረጅም ጊዜ ከያዙት አንድ ግብ ለመድረስ ያቋቋሙት ግንባር ባለመሆኑ ነው፡፡
ድርጅቱ የጋራ ግንባር ሆኖ የተሰራ እንጂ የተፈጠረ አለመሆኑን የሚያረጋግጥልን በሰላሳ ዓመት እድሜው በአባል ድርጅቶች መካከል ክርክር ያስከፈተና ድርድር የጠየቀ አንድም ጉዳይ ሰምተን ስለማናውቅ ነው፡፡  
እንኳን በኢሕአዴግ በራሱ ውስጥ፤ አጋር እየተባሉ የሚጠሩት የአፋር፣ የቤንሻንጉል፣ የሐረሪ፣ የጋምቤላና የሶማሌ ክልል ገዥ ፓርቲዎች ጋር እንኳ አንድም ክርክር የከፈተ ነገር ገጥሞ አያውቅም። የክልል ገዥ ፓርቲዎች እራሳቸውን የሚገልጡበት ምንም ነገር ስላልነበራቸው በገዥው ፓርቲ በኢሕአዴግ ውስጥ ተውጠው እንደቀሩ መገንዘብ የሚያስቸግር አይደለም፡፡ ስለዚህም ነው በክልሎች ለተፈፀመ አንድ ግድያ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ተቀምጦ፣ ኢሕአዴግ እንዴት ዝም ይላል ብሎ ሕዝብ የሚያጉረመርመው፡፡
አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ይመሩት የነበረው የሶማሌ ክልል ገዥ ፓርቲ፣ የኢሕአዴግ አባል እንዲሆን የተጠየቀበትንና ሌሎች እየታዩ የታለፉበትን ዘመን ስናስታውስ፣ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን በያዙ ጊዜ ደግሞ አጋር የሚባል አሰራር አይኖርም ብለው፣ ለጊዜው የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ አባል አድርገዋቸዋል፡፡ የየክልሉ ገዥ ፓርቲዎች ሊቀ መናብርትና ምክትል ሊቀ መናብርቶች የጉባኤው ተሳታፊ መደረጋቸው ይጠቀሳል፡፡
ተፈጥሮአዊ የፖለቲካ ግንባር ባህሪ የማይታይበት ኢሕአዴግ፤በከረመበት መንገድ መቀጠሉ ጥሩ አለመሆኑን የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በአዲስ መልክ ለማደራጀት መታሰቡንና ጥናት መጀመሩን ከወራት በፊት ገልጠው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ጥናት ከጫፍ ደርሶ “የኢትዮጵያ  ብልጽግና ፓርቲ” የሚባል ስያሜ ይዞ እንደመጣ ቢዘገብም፣ ከኢሕአዴግ ጽ/ቤት አቶ ፈቃዱ ተሰማ የተባሉ ሰው ጥናቱ ላይ አባላት እየተወያዩበት መሆኑን ገልጠው፣ የአባላቱ ውይይት እንደተጠናቀቀ ለአጋር ድርጅቶችም እንዲደርሳቸው እንደሚደረግ አሳውቀዋል፡፡ አጋር ድርጅቶች ዛሬም ለኢሕአዴግ ደረጃ ሁለት የጎደለ መሙያ እንደሆኑ እንዲቀጥሉ መፈለጉ በግልጽ እየታየ ነው ማለት ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ አዲሱ ፓርቲ እንዴት እንደሚመሰረት የታወቀ ዝርዝር ነገር ባይኖርም፣ የተያዘው መንገድ ግን የክልል ገዥ ፓርቲዎች፣ በፌዴራል መንግሥቱ ወሳኝ የሥልጣን ቦታዎች ለምሳሌ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰው እንዲያወጡ ታስቦ እየተሰራ መሆኑን እያረጋገጠ ነው፡፡ ‹‹እኛም ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያምረናል›› የሚለው የአንድ ሶማሊ ምኞት አሁንም እውን አይሆንም ማለት ነው፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እንዴት እንደሚሳከለት ባይታወቅም፣ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ለመምጣት እየተንደፋደፈ ያለው በ2012 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው አገር አቀፍ ምርጫ ነው፡፡
ውል መቁረጥ አቅቷቸው እንደ ኢሕአዴግ የሚንደፋደፉ በአገር ውስጥ የነበሩ፣ ከውጭም የገቡ በርከት ያሉ ፓርቲዎች እንዳሉ መረሳት የለበትም፡፡ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ደግሞ ሁሉም አገር አቀፍ ሆነ የክልል ፓርቲ ላይ አዲስ መስራች አባል ሰብስበው፣ ጉባኤ አካሂደው እራሳቸውን ሕጋዊ ማድረግ እንዳለባቸው ግዴታ ጥሏል፡፡
በሌላው በኩል ደግሞ የ2012 አገር አቀፍ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ ካልተካሄደ አሁን ያለው የኢሕአዴግ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊነቱን ያጣል የሚሉ ወገኖች እየተደመጡ መሆናቸው መጠቀስ አለበት፡፡ ይህን መከራከሪያ ከሚያነሱት ውስጥ አንዳንዶቹ በተለይም ከውጪ የገቡት በራሳቸው ምክንያት ሕጋዊ መሆን ተቸግረው የሚገኙ መሆናቸውም ግልጽ ነው፡፡ ምርጫ ካልተካሄደ የኢሕአዴግ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊነቱን ያጣል የሚሉ ክፍሎችን፣ “በሕዝብ ነፃ ፍላጎት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለሥልጣን የበቃ መንግሥት ነው ብላችሁ ታምናላችሁ ወይ?” ተብለው ሊጠየቁ ይገባል፡፡
እነዚህም ቢሆኑ ሀሳባቸውን ማጣራት ያልቻሉ፣ ገና መስመር ለመለየት እየታገሉ ወይም እየተንደፋደፉ ያሉ ናቸው፡፡ አሁንም ኢሕአዴግም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎች ከነበሩበት ፈቀቅ እንዳላሉ ማስገንዘብ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ፓርቲዎች መቼ መንደፋደፋቸውን ጨርሰውና መቼ ለምርጫ እራሳቸውን አዘጋጅተው ይመጡ ይሆን? ለእኔ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡

Read 5682 times