Tuesday, 08 October 2019 10:11

በአፍሪካ ረጅሙ ህንጻ ከሳምንታት በኋላ ስራ ይጀምራል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 234 ሜ. ቁመት ያለው ህንጻው 203 ሚ. ዶላር ፈጅቷል


          በአፍሪካ አህጉር እጅግ ረጅሙ ህንጻ እንደሆነ የተነገረለትና 234 ሜትር ቁመት እንዲሁም 55 ወለሎች ያለው የደቡብ አፍሪካው ሊዎናርዶ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ከሳምንታት በኋላ በይፋ ተመርቆ ስራ እንደሚጀምር ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሌጋሲ ግሩፕና ኔድባንክ የተባሉ ሁለት ኩባንያዎች በደቡብ አፍሪካዋ ጁሃንስበርግ ሳንድተን ሲቲ ውስጥ ከተማ በጋራ ያስገነቡትና ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎት የሚውለው ሊዎናርዶ 203 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደተደረገበት የጠቆመው ዘገባው፤ ህንጻው 254 አፓርትመንቶች፣ አምስት ወለል ቢሮዎችና ሱቆች፣ ሬስቶራንቶች፣ ጂም፣ ትምህርት ቤትና አረንጓዴ ስፍራ እንዳለውም አመልክቷል፡፡
ይህንን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ዲዛይን ያደረገው ኮአርክ ኢንተርናሽናል አርክቴክትስ የተባለ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ከኩባንያው 11 ባለሙያዎች መካከል ዘጠኙ ሴቶች መሆናቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
እስካሁን በአፍሪካ በቁመቱ ረጅም ተብሎ ሲጠቀስ የቆየው ህንጻ በዚያው በጆሃንስበርግ የሚገኘውና 222 ሜትር ቁመት ያለው ካርልተን ሴንተር እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ በአፍሪካ በቁመታቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ከያዙት ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች መካከል አራቱ በደቡብ አፍሪካዋ ጁሃንስበርግ፣ ሶስቱ በታንዛኒያዋ ዳሬ ሰላም፣ ሁለቱ በኬንያ መዲና ናይሮቢ አንዱ ደግሞ በናይጀሪያዋ ከተማ ሌጎስ እንደሚገኙ ገልጧል፡፡


Read 978 times