Tuesday, 08 October 2019 10:13

የፔሩ ም/ ፕሬዚዳንት 1 ቀን ሳይሞላቸው ስልጣን ለቀቁ

Written by 
Rate this item
(3 votes)


             የፔሩ ፕሬዚዳንት ማርቲን ቪዝካራ ባለፈው ሰኞ የአገሪቱን ምክር ቤት መበተናቸውን ተከትሎ፣ ላቲን አሜሪካዊቷን አገር በጊዜያዊነት እንዲያስተዳድሩ የተመረጡት ሜርሴድስ አራኦዝ ቃለ መሃላ ፈጽመው ስልጣን ከተረከቡ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን መልቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሜርሴድስ አራኦዝ ሰኞ የያዙትን የምክትል ፕሬዚዳንትነት ስልጣን፣ ማክሰኞ ለመልቀቅ የወሰኑት ሹመቱ የተከናወነው ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ በመሆኑ ህገ መንግስቱን የሚጥስ ነው የሚል ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ አራኦዝም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ፈርሷል የሚል አቋም በመያዛቸው ስልጣናቸውን በፈቃደኝነት መልቀቃቸውን በመግለጽ በአፋጣኝ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረባቸውን አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማርቲን ቪዝካራ ምክር ቤቱን የበተኑት ተቃዋሚዎች አብላጫ ወንበር የያዙበት ምክር ቤት በመሆኑና ምክር ቤቱ የጸረ ሙስና ጥረታቸውን እያደናቀፈባቸው ወራትን በመዝለቁ እንደሆነ ያስታወሰው ዘገባው፤ ተቃዋሚዎች ግን ወዲያውኑ ሜርሴድስ አራኦዝን በጊዜያዊነት አገሪቱን እንዲመሩ መሾሙን ጠቁሟል፡፡ አራኦዝ ከተሾሙ ከሰዓታት በኋላ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የፕሬዚዳንት ቪዛርካ ደጋፊዎች አደባባይ ወጥተው ድጋፋቸውን ማሳየታቸውን የገለጸው ዘገባው፤ የፖሊስና የጦር ሃይሉን ድጋፍ የያዙት ቪዛርካ በመጪው ጥር አዲስ የፓርላማ ምርጫ እንዲካሄድ ሃሳብ ቢያቀርቡም ምክር ቤቱ ግን ሰሞኑን አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ፣ ፕሬዚዳንት ቪዛርካን እስከ መጨረሻው ከስልጣን ለማባረር ድምጽ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡

Read 11527 times