Print this page
Tuesday, 08 October 2019 10:18

‹‹እሾኻማዋ ጀንበር›› እቴዋ ወ ስብሀት ለአብ

Written by  ፈለቀ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

        . . . እና ምን ይደረግ?
ስለእናቶች ክብር እናት ያለው ሁሉ ተነስቶ ይውረግረግ?
ሺ ሻማ ይለኮስ? ርችት ይተኮስ?
አዲስ ጥበብ ቀሚስ ኩታ፣ ቅቤና አደስ
ቀጤማ ይነስነስ? ምድሩ ይታረስ?
በእንቁ  ዕንቆጳዝዮን ልስራ እቴዋ መቅደስ?
የት አባቴ ልድረስ አንቺን ለማወደስ?
ውድ ሽቶ ይረጭ እጣን ጢሱ ይጨስ ከርቤና ሉባንጃ?
እልፍኝ ይሁንልሽ የወርቅ ስጋጃ የአልማዝ መጋረጃ
አንቺን ባሰብኩ ቅጽበት ሚነካኝን እንጃ !  . . .
(ውዳሴ እናት - የፀሐይ ገበታ 2005 ዓ.ም፡፡)
‹‹እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ፤ ታሳድግ የለም ወይ በችግር ተጠብሳ›› ይሄ ስንኝ ምናልባት እናት በችግር ስትጠበስ ትኖራለች እንጂ መቸም አትሞትም የሚል ምኞትን የእውነት ያህል እንዳምነው አድርጎኝ ይሁን እንጃ፡፡ በዚያ ላይ እሷም ‹‹የማርውሃ እናት እድሜሽ ስንት ነው?›› ሲሏት ‹‹ኡ...! ቢጠሩትም አይሰማ!›› ስለምትል፤ የተደበቀው እድሜዋ ውስጥ ከርዝመቱ ይልቅ ገና እምትኖረውን ብዙ ዘመን ተስፋ በማስላት ተጠምደን ኖርን፡፡ እድሜ በክፉ መጋዙ ውበትና ንቃቷን እየገዘገዘ አቅል ከድቷት እስክናያት ድረስ፡፡ ከየንታ ስብሀት ጋር ከነበራቸው ቆይታ አንድ ሁለት ትዝታ እናውጋ...
አያቴ እቴዋ እታገኘሁ ጎሹ የእውነትም ማራኪ ወግ ጠራቂ ነበረች፡፡ የስነ ቃል ሀብት:: ሌባ በበዛበት ቀዬ ባልተቋረጠ አፍርሳታ፣ ስራ በመፍታት የተሰላቸ ገበሬ በአውጫጭኙ መሀል ‹‹በሀገራችን ሌባው ለማ፤ ቢተው ይተው፤ ጀንበር በሰረቀ ቁጥር ስንሰበሰብ ልንኖር ነውንዴ?!›› ያለውን ሰውዬ ተረት አፍ መፍቻ አድርገን ለማደግ ቻልን፡፡ እናም ሌሎችም የትዬለሌ ጣፋጭ ወጎቿን፡፡ ድምጼ መጎርነን ብብቴ ጠረን ማመንጨት የጀመረ ሰሞን፣ ፈንድቼ ስንበጫበጭ ‹‹እማም እኔን’ኮ አትወጂኝም!›› ብላት ክው! ብላ የገረረችውን ፀሐይ ቀና ብላ እያየች ‹‹አንተን ጡቴን አጥብቼ ያሳደግኩህን ልጄን ባልወድህ ይቺ እሾሀማዋ ጀንበር ትመስክርብኛ!›› አለችና አስለቀሰችኝ፡፡ እውነቷን ማወጃ የተጠቀመችበት ‹‹እሾኻማዋ ጀንበር›› የቋንቋዋ ውበት ሼክስፒርንም ያስንቃል ለኔ፡፡ ካጋነንኩም እናቴን ነው! እናም ውሎ አድሮ የከተብኩት ስንኝ ከዚሁ የልጅነት አጋጣሚ (childhood trauma) በቀጥታ የተቀዳ ይመስላል . . .
‹እህት አገኘሁ› አንቺን የአስጋረደች ፍቅር ለዘር ማንዘር ተርፈሽ፤
እርጅት ብለሽ ጃጅተሽ ምርኩዝ ተደግፈሽ
አሊያም በአራት እግርሽ እንደኔ ልጅነት ብትሄጂስ በዳዴ፤
የእሾኻማዋ ጀንበር የቀትር ንጣቷስ ካንቺ ውብ ፀዳል ጋ ይተያያል እንዴ?
‹‹የስብሀት ተከታይ›› ሆነን አንድ ቀን ወደ ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም አቀናን፡፡ ከወዳጁ ዕሌኒ ደርቤ ቤተሰብ ዘንድ ጎራ ብለን፣ ወደ ‹‹ቀጨኔ የጥበብ ከተማ››  በሁለተኛው መንገድ በኩል ዘልቀን ‹‹መሀል ገነት›› ባለጅ መንደር ደረስን፡፡ የማርውሃ እናት እቴዋ እታገኘሁ ጎሹ፤ ለእንግድነቱ ክብር በማርያም ወንዝ ሸክላ አፈር መቀጠያ አምባ ‹በተኮቸመ› መንታ ፎንጭ ጀበና ቡና እየካደመችው . . .
‹‹ለመሆኑ በልጅነቱ አብሾ አጠጥታችሁት ኖሯልን ?!›› አለ ጋሽ ስብሀት ወግ ሲጀምር፡፡
እቴዋ ‹‹ሞገደኛነቱን አይተው ይሆን? ሲፈጥረውም እንዲሁ ነው - እሳት!›› አለችና ጊርጊራው ላይ ዕጣን ጨመረች፡፡
አባባ፤ የሽመና መወርወሪያቸው ፍጥነት ላፍታ ሳይናጠብ  ቀጠሉ -  ‹‹ነጋ ጠባ ተየትም እሚለቃቅመውን መጽሀፍ ጉያው ሸጉጦ እንደ ነፋስ ይከንፋል’ንጂ ይኸው እንደ እኩዮቹ ጥበብ ጥለት ለቅሞ ነጠላ ኩታም አልሰራ!››
‹‹እኩዮቹን ያስንቃልና!››
‹‹እኮ መች አየንና! እስቲ ምከሩት ተሰማዎት!›› አሉ አባባ፤ የዘሀውን ጥቅልል ተጎናቸው ተርትረው፣ የሸመኑትን ጠቅልለው፡ ወርቀዘብ ድውር ቀይረው፣ መኑን ገፍተው፣ በሞልድ ጫፍ ቀለም አጥቅሰው ድሩን እየቀጠቡ፡፡
‹‹እንግዲያውስ ያዩታል እድሜ ይስጥዎት፡!›› አለ ስብሀት፤ በገዳሞች ጽዋ የቀረበለትን የማር ጠጅ ጎንጨት እያለ፡፡
እድሜ ጓዘ ቅጥልጥሉ በየተራ ቢወስዳችሁም፤ በፊደል ማዕድ ገበታው ላይ (ከነባርኔጣው ኮርጄ) ምስሌን ያስተዋለች የጥዷ አክስቴ ጽጌረዳ አበበ፡- ‹‹እውነትም ሽማግሌው ታይቷቸው ነበርና! እኮ የታል ታዲያ ባውንዱ ?!›› አለች፡፡ ፍራንካው የለም! - ፊደል ዘሩ ግን ይኸው! ‹እግረ መንገድ› - የሽማግሌው ፈለግ ቅንጣት ተሞክሮ:: ምናምን ...›› ያልኋት መሰለኝ::
ጋሽ ስብሀትን እጅግ የማረከውና አፉን ያስከፈተው የ‹ጉድነሽ›? ማማሰያ - myth ታሪክ ነበር:: ሴትዮዪቱ የስሙኒ ዘይት ገዝታ ስትመለስ፤ በሰላቢነት የምትታማው ጎረቤቷ ጉድነሽ በራፍ ላይ የወጥ እንጨት አግኝታ ‹‹ውይ እንዴት እምታምር ማማሳያ ነች! ›› ብላ አንስታ ቤቷ ታመጣና አጥባ እሮብ ወይ አርብ ቀን ነው ልሙጥ ሽሮ ወጥ ጥዳ፣ በአዲሱ ማማሳያ አማስላ፣ ዞር እንዳለች ቤቱ በዶሮ ወጥ ታወደ፤ ብትከፍተው ድስት ሙሉ የዶሮ ብልት ብላ የነገረችው፡፡ ታዲያ አንድ ምሽት ተረት ሰፈር እነ ቱፈኔ ቤት አረቄ ጨብጠን፣ ምድርን ስናካልል፣ የንታ ስብሀት ‹‹ሁለት ግስ፤ ከዶሮ ማነቂያ ጀንበር መጥለቂያ መንከራተትህን ትተህ ወደ እትብት መንደርህ ተመለስና የባለጅ ወገንህን ታሪክ አጥና›› ያለኝ ያኔ ነበር፡፡ምክሩን ሰምቼ ተመልሼ ለአመታት ቀጨኔ ከረምኩ፤ እናም ‹‹ብርሃን እና ጥላ›› የግጥም መድበልን አሳትሜ ለንባብ አበቃሁ - መታሰቢያነቱም ‹‹ላገሬ ባለጆች›› ሆነ:: ለእማማ የተበረከተችው ‹‹ሸምግም ለሷ ልጅ ነኝና...›› ስንኝ ይች ነበረች...
ዛሬ ጠጋ አለችኝና
አይኗን በሀዘን ጨፍና
እንዲህ ባደርግስ ልጄ? ብላ
አማከረችኝ መላ
እማ
እንዲህ የውስጧን መዘርዘሯ
እኔ አድጌ ነው?
ችግሯ?
አቦይ ስብሀትን በሳቅ ያንፈቀፈቀው ደሞ የምራቶች ቤት ፈስ ተረት ነው...አዲስ የተዳረች ሙሽራ በምራቷ ፊት ድንገት ፈሷ ጡጥ! ብሎ በሀፍረት ከቤት ወጥታ በረረች፡፡ የባሏ ቤተሰቦች ሁሉ ተንጋግተው፣ ተከትለዋት እግራቸውን እያነሱ ‹‹ነይ ነይ አይዞሽ ይኸው እኛም’ኮ እንፈሳለን! ጡሩሩሩሩሩ ቤተሰቡ ሁሉ ሜዳውን በሩጫ እያቋረጡ እየተከተሏት ያለማቋረጥ እየፈሱ አሳምነው፣ ወደ ትዳሯ መለሷት፡፡ ጉዳዩ ከተራ ነፋስ ፈስም በላይ ነው ለኔ፡፡ ሽቶ መአዛው የሚያውድ የማህበረሰብ መስተጋብር ስብራት ጥገና ጉዳይ፡፡
እማማ ትዳር እንዲዘልቅ በየጋብቻው ውስጥ አሻራዋን በማኖር በሰፊው ትታወቅ ነበር፡፡ የጥምቀት ቀን የባለጅ ሚካኤልን ታቦት ስንሸኝ መኪናቸውን ተደግፈው የቆሙ ክብርት ወይዘሮ በስስት ጠርተውኝ ‹‹አንተ የማርውሃ ልጅ አይደለህምን፤ ይኸውልህ እኔ ከትዳር ውጭ ተወለድሁ (ዲቃላ) ነበርኩ፡ የአባቴን ሚስት አሳምና የቀላቀለችኝ ነፍሷን ይማርና ያንተ አያት እቴዋ እታገኘሁ ነበረች›› አሉኝ እንባ ባቀረሩ አይናቸው እያዩኝ፡፡ በተረፈ ስንቅ ቋጥራ. የታመመ የታሰረ ቱኩቶ (ለመንጻት ስርአት) የገባችን ሴት...ወዘተ. ሁሉ ስትጠይቅ ነው የኖረችው፡፡ የተራበ አጉራሽ፣ የታረዘ አልባሽ፤ የተራራቀን አቀራራቢ፤ መሄጃ የጠፋውን ሰብሳቢ የዘመድ አውራ ነበረች - እቴዋ፡፡ አባባን’ኳ ‹‹እታጉ›› ብለው በቁልምጫ ይጠሩና በዜማ እያንጎራጎሩ ሲያሞግሷት ‹‹የባቄላ ጠላ አይጠጣም ጉሹ አሁንም ቅድምም እታገኘሁ ጎሹ፡፡›› ይሉ ነበር፡፡ እግረ መንገድ የአባባን የግጥም መታሰቢያም እዚህ እንዘክር ‹‹ጉዞ ወደ...››
ሽምግልና አፋፍ ላይ ሆኖ
ቁልቁል እያየኝ በአርምሞ
በእፎይታ አልጋው ላይ ተጋድሞ
ቆሜ! ቁልቁል እያየኝ
‹‹ለኔ አታስብ ላታቆየኝ
ፍቅርን ዝራ ልጄ!›› አለኝ፡፡
የወጣውን ዳገት ጉዞ
እያየው ቁልቁል ተክዞ
የእድሜን መሰላል እርዝማኔ
አቀበቱን ገና እምደክምበትን እኔ፡፡
ሌላው የጋሽ ስብሀትን አይን ያስፈጠጠው የእማማ ድንቅ ተረኳ ‹‹መስቀሉን የሸረፈ እና ያልሸረፈ›› ነበር፡፡ ሁለት ሰዎች የድንጋይ መስቀል ተሸክመው ወደ ሩቅ ቤተ ክርስቲያን እንዲያደርሱ ተላኩ፡፡ አንዱ በየደረሰበት ሲሸርፍ፤ በአቋራጭ መንገድ እየተንደረደረ የእውር ድንበሩን አየሩን ሲቀዝፍ፤ ሌላኛው ታማኝ ሰው አደራውን ጠብቆ ሙሉውን የድንጋይ መስቀል ተሸክሞ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ በመጨረሻ በገደል የተከበበችው ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ባቋራጭ እየሸረፈ የደረሰው መስቀሉን ቢያጋድመው ጉርጓዱ ውስጥ ገባበት፡፡ በዙሪያው ደሞ ዛፍ የሚባል የለም፡፡ በቀጥታው መንገድ የደረሰው መስቀሉን አውርዶ ቢያጋድመው መሻገሪያ ሆነለትና በዚያ ተራምዶ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዐምባ ገባ፡፡ የሸረፈው ግን ወደ መጣበት እያዘነ ተመለሰ፡፡
አያቶቼ እርጅና እየተጫናቸው ሲሄዱ ስጋቴ እየጨመረ መጣ፡፡ ለአባባ የመጨረሻ ቀናት ቀደም ሲል በ‹‹ብርሃን እና ጥላ›› መድበል ከጻፍኩት ... ግጥም ሌላ ለሁለቱም ደግሞ...
እድሜ ጓዘ ቅጥልጥል መኖር በወሰን ተጠብቆ
ያሉበት ሆነው ሳልደርስ እንዳይወስድብኝ አርቆ
ፈራሁ!...
…የምትል ስንኝ ቋጠርኩ፡፡
ለአመታት ሳብሰለስል ኖሬ ኖሬ  ‹‹እምልሽ እማም፤ ከእነዚያ የነገርሽኝ ሰዎች አንደኛው ‹መስቀሉን የሸረፈውስ ተመለሰ እሺ፤ ያልሸረፈውስ መስቀሉን ካደረሰ በኋላ በዙሪያው ጫካም ዛፍም ከሌለ ጉድጓዱ ላይ ምን አጋድሞ ወዲህ ይመለሳል?›› አልኳት፡፡ መልስ እማታጣው እማማ ‹‹አይ ልጄ መስቀሉን ያልሸረፈ ሰውማ ወደ አለም አይመለስም፡፡›› አለችኝ፡፡
ከዚህ በኋላ እማማ እድሜዋ ገፍቶ በአልዛይመር ህመም ስትጠቃ ደጋግማ ድንገት ብድግ ትልና ‹‹ተነሱ እንሂድ እንጂ!›› ትል ነበር፡፡ ወዴት? ስንላት ‹‹ወደ አባቶቻችን ነዋ! ይጠብቁናል’ኮ!›› ነበር መልሷ፡፡ ብዙዎች እንደሷ ጉልበት ሳይከዳቸው ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ ብለው ወጥተው ቀርተዋል ይባላል፤ ስናድግ ታላላቆቻችን ሲያወሩ፡፡ እማማ በህይወት ሳለች የሞነጫጨርኩት ቅዠት መሳይ ምኞት ደሞ ይኸው . . .
ምናልባት ምናልባት ወይ አንቺ ቀድመሽኝ ወይ እኔ ቀድሜሽ በሞት ብንለያይ
ከእንጦሮጦስ አዘቅት ድቅድቅ ጨለማው ላይ
ጽኑ ጀርባሽ አዝሎኝ ገነት ያደርሰኛል
ፍቅርሽ አክናፍ ሆኖኝ ሽቅብ ያከንፈኛል
ወደ ላይ  ወደ ላይ ሰባተኛው ሰማይ
ከመንግስተ ሰማይ፣ ምህረቱ በራፍ ላይ
ቆመሽ ለኔ ባዝነሽ ሞተሽም አታርፊ አይንሽ አይኔን እስኪያይ፡፡
እኔ ሲኦል ብጣል አንቺ ገነት ሆነሽ
‹ላም እሳት ወለደ› ተረቱን አዳፍነሽ
በናፍቆት ተቃጥለሽ በፍቅር ራብ ጥም አልቀሽ
ማልቀስሽ አይቀርም ከአምላክ እግር ወድቀሽ
‹‹እባክህ ፍቀድልኝ ልጄን አይ ዘንድ?›› ብለሽ
አንድዬም ይራራል አይደራደርም
‹‹በእናትህ›› ያሉት ቀን ጌታም አይጨክንም፡፡
(ውዳሴ እናት - የፀሐይ ገበታ 2005 ዓ.ም፡፡)
እነሆ ዛሬ የእማማ ሰባተኛ አመት መታሰቢያ ቀን ነው፡፡ በዚህች ቀን አንዲት ነገርን ልጠይቅሽ ዘንድ ፍቀጂልኝ...አንቺ እንድሆን እንደምትሺው ስላልሆንኩ ይቅርታ አድርጊልኝ እቴዋ:: ቢሆንም የዘወትር ምርቃትሽ ‹‹ልጄ የሰው መውደድ ይስጥህ›› ነበርና፤ እንደኔ ‹ሞገደኛነት› ሳይሆን እንዳንቺ ጽኑ ምኞት የእናትነት ምርቃትሽ ከክፉ ሁሉ ጠብቆ በደጋግ ሰዎች መውደድ እቅፍ ውስጥ ሸሽጎ አኑሮኛል፡፡ አንቺ ወደር የሌለሽ ፍፁም ሰው አፍቃሪ ደግ ነበርሽና... አዎን እማማ ናፍቆትሽ ያንገበግባል፤ ከእንግዲህ ወደ አለም አትመለሺም፡፡ ትዝታሽ ግን ህያው ሆኖ ለምንጊዜም  አብሮን ይኖራል . . . አሜን!!
መልካም ስም
ቢርቅም አይጠፋ ይልቃል ከሽቶ
በሰው ልብ ይኖራል ከመቃብር ሸሽቶ፡፡

Read 2931 times