Print this page
Tuesday, 08 October 2019 10:22

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

 “ልጆችን ከተፈጥሮ ጋር ማቀራረብ ሥልጣኔ ያፋጥናል”
                           
             አገርና ትልልቅ አእምሮዎች አንድ ናቸው:: በደልን ይታገሳሉ፣ ይቅር ይላሉ፡፡ “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም” እነሱ ጋ አይሰራም:: በደለኛ “በደለኛ” ሊሆን የቻለበትን ስር ምክንያት ይረዳሉ፡፡ ዘጠና ዘጠኙን ትቶ አንዱን ፍለጋ እንደሄደው መልካም እረኛ ይመስላሉ:: ድርሻውን አባክኖ ሲቸገር ከባሪያዎችህና ከነእሪያዎችህ የሚተርፈውን እየበላሁ እንድኖር እግሩ ስር ወድቄ ይቅርታ እጠይቀዋለሁ ብሎ ወደ አባቱ ሲመለስ እጅግ ደስ እንዳለውና የተፀፀቱትን ሁሉ ማቀፍ ተፈጥሮው እንደሆነው አባት ናቸው…ሆደ ሰፊ!!
የዛሬው ጨዋታችንን “የዓለም ህዝቦች ቤተሰቦቼ ናቸው፡፡”…እያለ በሚያስብ አንድ ጥሩ ሰው እንጀምር፡፡ ሃብትና ንብረቱን ለሰብዓዊ አገልግሎት በሚተጉ ድርጅቶች በኩል የስልጣኔ ግብዓት እንዲሆን በማመቻቸት ላይ እንዳለ ድንገት የሞተ…
ይኸ ሰው አንድ ቀን ሰማይ ቤት ቁጭ ብሎ ሲተክዝ እግዜር አየውና ፡-
“ምነው ከፋህ?” ብሎ ሲጠይቀው
“ሃሳቤን ሳልፈጽም ነው የጠራኸኝ” አለው፡፡
“ሰው ያሰበውን ሁሉ መፈፀም ይችላል? ሃሳቤ ሞላ፣ የልቤ ደረሰ የሚል ማን አለ?”
እዚህ ጋ እንደ መንፈስ ሰውየው ሊረዳው እንደማይችል ስለገባው፣ ራሱን ወደ ቅን ሰው አእምሮ ቀይሮ ነበር የሚያናግረው - እግዜር፡፡
“ማለቴ…ዕድሜዬን ሙሉ የደከምኩበት ሰብዓዊ ጉዳይ እንዲሳካ…”
“ይኸማ የኛ ስራ ነው፡፡ ያንተ ድርሻ በህይወት መድረክ ላይ እግዜር ዕጣ ፈንታህን ከውኖ ማለፍ ነበር” በማለት አቋረጠው፤ እግዜር እየሳቀ፡፡
“ሃሳባችንን መኖር ካልቻልን ምኑን ኖርነው ታዲያ? አንተስ ብትሆን ለኛ ብለህ መሞትህ ምን ጠቀመህ ምን ጠቀመን ሲያግዙህ እንኳ አታውቅም እንዴ?”
ሰውየው ቅር እንዳለው የተረዳው “አምላክ” አዘነና…”ሂድ የጀመርከውን ጨርስ፤ ሃሳብህ ሲሞላ ተመለስ” ብሎ ወደ ምድር አሰናበተው፡፡
አርባው በተዘከረበት ቀን ምሽት ከቤቱ ደረሰ፡፡ በዕለቱ ቤተሰቦቹ ስለንብረቱ ሲወያዩና “እግዜር የልባችንን ዐይቶ ፈረደ እንጂ እንደሱማ ቢሆን “ጉድ” ሆነን ነበር እያሉ ሲዘባበቱበት ዘው አለ፡፡ ከድንጋጤያቸው ሲባንኑ የሆነውን ሁሉ አስረዳቸው፡፡ እነሱ ግን ከጀርባው ተመካክረው እንደተኛ ገደሉት፡፡
ሰማይ ቤት ተመልሶ “ጥቃቱን” ሲያሰላስል እግዜር ተከስቶ…
“ምነው ወዲያው መለስክ አልተመቸህም?” አለው እየሳቀ፡፡
“የሆነውን እያወቅህ አትጠይቀኝ፡፡ ደግ በማሰቤ ተጠቅቻለሁ” ብሎ አቀረቀረ ሰውየው፡፡ እግዜር አሁንም አዘነና፡-
“እንደገና ሞክር፡፡ ፈቅጄልሃለሁ”
“እንደገና ቢገድሉኝስ?”…እግዜር ማሰብ ጀመረ፡፡ አሰበ፣ አሰበና…
“ሂድ! ሃሳብህን ሙላ! ማንም አያቆምህም!!” አለው፡፡
“Invisible man” ተወለደ፡፡ ሲፈልግ የሚታይ፣ ሳይፈልግ የማይታይ፡፡ እሱ ግን ሁሌና ሁሉን ማየት የሚችል፡፡ ጦርነቱም Invisible conflict ተባለ፡፡ እስከ ዛሬም ትግሉ አላበቃም፡፡
ወዳጄ፡- ስለ ጥቃት ካነሳን አይቀር ሚዲያ ጀባ ያለንን አንድ ሁለት እውነተኛ የእንስሳት ታሪክ እነሆ፡- የሰውማ ስንቱ ተነግሮ፡፡
ቀደም ባለ ጊዜ የዓለም የዜና ማሰራጫዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ትልቅ ዜና የሆነ ጉዳይ ነበር፡፡ ሰውየው በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እየተዘዋወረ፣ ፈቃድ እያወጣ የዱር እንስሳትና አራዊትን የማደን “ሆቢ” የነበረው ታዋቂ ሃብታም ነው፡፡ ኢትዮጵያ መጥቶ አንበሳ ለማደን ወደ አንድ አገራችን ክፍል ሄደ፡፡ ከቲሙ ጋር ዝግጅቱን ጨርሶ ሲጠባበቅ አንበሳው ብቅ አለ፡፡ አነጣጥሮ መታው፡፡ አልወደቀም ደሙን እየዘራ አመለጠ፡፡ አዳኙ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለሌላ አደን ወደዛው ቦታ ተመለሰ፡፡ ገና ከመኪናቸው ወርደው ድንኳን ሲተክሉ አንበሳ ከሸመቀበት ከች አለ፡፡ ከቡድኑ መሃል ሰውየውን መርጦ፣ ዘነጣጥሎ ጥሎ ወደ ደኑ ተመለሰ፡፡ ሌሎቹን ዞር ብሎም አልተመለከተም፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ሀረር ውስጥ አንድ ዛፍ ቆራጭ የአንዲት አሞራ እንቁላል የነበረበትን ቅርንጫፍ በመቁረጡ፣ አሞራዋ እየተመላለሰች በጥፊ ሚዛኑን አስተው ወድቆ ሞቷል፡፡
ከቀናት በፊት ዳግሞ በሸገር ሬዲዮ ቀደም ሲል ከታተመ የፖሊስ ጋዜጣ ላይ የወጣ ጽሑፍ ሲነበብ ተመሳሳይ ነገር አድምጠናል፡፡ አንዲት አሞራ ሰውየውን ለስምንት ቀናት በተከታታይ ከሰው መሃል እየመረጠች፣ በጥፊ እየተመታች አላስቆም፣ አላስቀምጥ እንዳለችው በመግለጥ፣ መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ያመለክታል፡፡
የሚመለከተው ክፍልም አሞራዋ እንድትገደል ይወስናል፡፡ ለአፈፃፀሙም አሞራዋ ላይ ተደጋግሞ ጥይት ተተኮሰባት፡፡ አላገኛትም:: የሞተችው መርዝ የተነከረ ስጋ በልታ ነው፡፡ “…ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ”   ሆነባት፡፡
…ሆድ የማያታልለው፣ ሆድ የማያስጠቃው ማን አለ?
በፀጋዬ ገ/መድህን “ሀሁ በስድስት ወር” ተውኔት ውስጥ አንዱ ገፀ ባህርይ ለሌላኛው፡-
“ማሸነፍ ሆድን ነው” ብሏል አሉ ሲለው
“ማን” ብሎ ይጠይቀዋል ጓደኛው… ማን እንደሆነ ነገረው፡፡ ማን ይሆን?
***
ከመልሱ በፊት ከላይ በጠቀስነው ሬዲዮ በቀደምለት የሰማሁትን  የ“ጥቃት ታሪክ” አንድ ልጨምር፡- ሰውየው ላሟን ምን እንደበደላት አልተገለፀም፡፡ ክፉኛ ነክሰችው፡፡ በዚሁ ሰበብ ሰውየው ይሞታል፡፡ የሰውየው ልጅ “ይቺ አባቴን የገደለች ከብት እሠራላታለሁ” በማለት ዝቶ ለአባቱ አርባ ማውጫ ያርዳታል:: ከሶስት ወር በኋላ ወይፈን ልጇ ያድግና የናቱን አራጅ በቀንዱ አንጀቱን በመጐልጐል ቂሙን ይወጣል:: እሱን ደግሞ ሌላው ቤተሰብ ለሟች አርባ ያርደውና ጉዳዩ አበቃ፡፡ ሰውየውና ልጁ፣ ላሟና ጥጃዋ አለቁ፡፡
ወዳጄ፡- እንስሳት ምክንያታዊ ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ በባህላዊ እምነት እንደሰው የተፈጠረበት አምሳልም የለም፡፡ ሳይንሳዊውን ንድፈ ሃሳብ ለሚቀበል ካልሆነ፡፡ በደመነፍስ ይነዳሉ እንጂ ነገሮችን ማገናዘብ አይችሉም፡፡ ጥቃትን በጥቃት ቢመልሱ ተፈጥሯቸው ነው፡፡ ላያስገርም ይችላል፡፡
የሚገርመው ግን ከወደዱህ ያለምክንያት አይክዱህም፡፡ ይሞቱልሃል፡፡ ድሮ የእንግሊዘኛ መሣሪያ በነበረ መጽሐፍ ውስጥ ይህንን የምታረጋግጥ አንድ ትርክት ነበረች፡፡ አንድሮ ክሊፐስና አንበሳው (Andro clipse and the lion) የምትል፡፡ ፈልግና ለልጆችህ አንብብላቸው፡፡ ትገረማለህ፡፡ ልጆችን ከተፈጥሮ ጋር ማቀራረብ፣ ስልጣኔን ያጥፋናል፡፡ አ/መ ወዳጄ፡- ፀሐፊዎችና ስቶር ፈጣሪዎች ባይኖሩ የዓለም ገጽታ አይቀየርም፣ ስልጣኔ አይስቅም፣ የአውሬነት ባህሪያችን አይገራም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰውን ልጅ ሰብአዊነት የደፈሩት/ ነፃነቱን ያሳጡት አምባገነሮች፣ ሌቦችና ዘራፊዎች አይጋለጡም፣ እርቃናቸውን አይቀሩም ነበር፡፡
ማ;; እንዳለችው “ብዕር ከአውቶሚክ ቦንብ የበለጠ ዓለምን የሚነቀንቅ ሃይል አለው፡፡”
ታላቁ ፀሐፊ አሌክሳንደር ሶልዣንስታይን በብዕሩ ቀዝቃዛውን ጦርነት አደብ አስገዝቶታል፣ ሩሲያ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን አፋኝ ስርዓት ተበቅሏል፡፡ “The First circle” በተባለው መጽሐፉ የ1960 (እኤአ) ዓ.ም የኖቤል ሽልማት አሸንፏል፡፡ ሶልዣንስታይን በስደት ከሚኖርበት አሜሪካ ወደ አገሩ ሩሲያ የተመለሰው፣ ፕሮስቶሪካና ግላስኖት የተሰኙ፣ ጊዜያቸውን ያንቀጠቀጡ አዳዲስ ሃሳቦች ባፈለቀው ፕሬዚዳንት ጐርቦቾቭ ጥሪ ነው:: ከሶልዣንስታይን “ዘ ፈርስት ሰርክል” ትንሽ መንፈስ ውልብ ቢልብን ምን ይለናል?
የጆሴፍ ስታሊን ዋና የደህንነት ሹም እስረኛው ሬዚኒን ወደ ቢሮው ያስጠራዋል:: ለፈረንሳዮቹ በስልክ መረጃ ሰጥቷል… የተባለውን ሰው (ፕሮፌሰር) ድምጽ ለመለየት ባዘጋጀው የምርመራ ፕሮጀክት ላይ ሙያዊ እገዛ እንዲያደርግ ለመጠየቅ ነበር፡፡ ሬዚን የድምጽ ኢንጂነር ነው፡፡ ወደ ቢሮውን እንደገባ ወንበር ስቦ ተቀመጠ፡፡
“…እንድትቀመጥ ማን ፈቀደልህ?”
“…ከመቆም መቀመጥ ይሻላል ይላሉ ቻይናዎች፡፡ በዚህ ላይ…”
“በዚህ ላይ ምን?”
“ማስፈቀድ አያስፈልገኝም፡፡”
“ለምን?”
“የምፈራው ነገር ሰለሌለ”
“ማለት?”
“ሰው የሚፈራው የመጨረሻው ነገር ሞት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ሞት አልፈራም፡፡ ኑሮዬን፣ ቤተሰቦቼን፣ ነፃነቴን ተቀምቻለሁ፣ የማጣው ነገር የለም”
---
ወዳጄ፡- ጥቃት የተቀበረ ፈንጂ ነው፡፡ ጥቃት ቆራጥ ያደርጋል፡፡ ዕውነትን የሚጽፉልን ሰዎች ሲጠቁ የኛ ጥቃት ነው፡፡ የአገር ጥቃት፡፡ “ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል” መባሉ ያለ ነገር አይደለም፡፡ የሶልዝንስታይን ብዕር የዓለምን ካርታ ቀይሯል፡፡ ትልልቅ መሪዎች ትልልቅ ፀሐፊዎች ወይም የትልልቅ ፀሐፊዎች ወዳጆች የነበሩ ናቸው፡፡ እነ ኬኔዲ በስነ ጽሑፍ የፑልታይዘር ሽልማት አሸናፊዎች ነበሩ፡፡
ለማንኛውም “ብዕር፣ ብዕር፣ ብዕር” የሚለውን የመልካሙ ተበጀን ሙዚቃ መርጬልሃለሁ፡፡ በነገራችን ላይ “ሰው ጥቃቱን መመለስ ያለበት ተሽሎ በመገኘት ነው” የሚለን ታላቁ ፍራንክ ሴናትራ ነው፡፡ ትስማማለህ?”
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- በፀጋዬ ተውኔት ላይ
“ማሸነፍ ሆድን ነው” ብሏል ሲለው
“ማን?” ብሎ ጠየቀው ብለን ነበር፡፡
መልሱ፡- “ትጉህ አሳማ!”
ሠላም!!

Read 1427 times