Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Print this page
Tuesday, 08 October 2019 10:25

የሙዚቃ ሌላ ስሟ - ጥላሁን ገሠሠ

Written by  በስንታየሁ አለማየሁ
Rate this item
(3 votes)


           መደመም ውስጤን ሲሞላው
ግርምት አፌን ሲያሲዘኝ
እንዲህ ባዲስ አመት በር
በመስከረም የአበባ ወር
አንድምታዬን መግለፅ ሲያምረኝ
ጥላሁን ነው ትዝ የሚለኝ፡፡
ክቡር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 17 ቀን 2012 ዓ.ም 79ኛ ዓመት የልደት በዓሉ ነበር፡፡ እኔም ይህችን ማስታወሻ የከተብኩት የሙዚቃ ንጉሱን ልደት ለመዘከር በማሰብ ነው፡፡ እንደ ጥላሁን አይነቱን ምርጥ ኢትዮጵያዊ ሰብዕና ዓመቱን ሙሉ ዘክሮ፣ ዓመቱን ሙሉ ሲያከብሩት ቢዘልቁ ከፍ ያለ ደስታና ክብር ነው የሚያጐናጽፈው፡፡ ጥላሁን ከኢትዮጵያ ሰንደቅነቱ ባለፈ በመስከረም ወር ተፈጥሮ፣ በድምፁም ወርሃ መስከረምን ያነገሰ፣ የአዲስ ዓመት መባቻን አድምቆ በአድባርነት የቆመ እውነተኛ አርቲስትም ነው፡፡
ከልጅነት እስከ እውቀት አዲስ ዓመት ሲመጣ፣ በዓሉን በዓል ከሚያስመስሉልን ጣዕመ ዜማዎች ውስጥ እንደ ዘሪቱ ጌታሁን ‹‹እንቁጣጣሽ››፣ እንደ አስቴር አወቀ ‹‹እዮሃ አበባዬ›› ሁሉ የጥላሁን ገሰሰም ወርቃማ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጥሌ “እንቁጣጣሽ የ 13 ወር ፀጋ … ክረምት አልቆ በጋ” ሲል እንደተለመደው ትንፋሹ ከስጋ አልፎ ከነፍስ ይገጥማል፡፡
በያመቱ ለኛ እንቁጣጣሽ
ደስ ይበለን እንኳን ደህና መጣሽ
እያለ አደይ አበባዋን ልክ እንደ ሰው በመልካም ምኞት ይቀበላታል፡፡ ስለኛ ስትል መውጣቷንም በውብ ዜማው ከሽኗታል:: አበባን የአይን ቀለብ ፣ ልምላሜን የመንፈስ እርካታ የማድረግ ስነ-ልቦናዊም ፣ ሰዋዊም ሳይንስ አለ:: ይህንኑ እውነታ ነው… ጥላሁን ያውም ከአዲስ አመት መንፈስ ጋር አቆራኝቶ፣ በውብ ድምፁ ያቀነቀነው፡፡ በአበቦች መዓዛ መርካታችንንም እንዲህ አዚሞታል፡-
ክረምት አልቆ በጋ
መስከረም ሲጠባ
አውዳመት አልፎ
አዲሱ ሲገባ
በአበቦች መዓዛ ረክቷል ልባችሁ
ረክቷል ልባችሁ
ሕዝቦች ሁሉ በጣም እንኳን ደስ አላችሁ
እንኳን ደስ አላችሁ፡፡
የአዲስ ዓመት መባቻን በዚህ አይነት የደስታ መንፈስ ያውድና …. የ13 ወር ፀጋ እያለ… ከጳጉሜ እስከ ጳጉሜ ዓመቱን ሙሉ ስላሉን ክብረ በዓላት፣ ጭፈራና ፈንጠዚያዎች፣ ሰርግና ፋሲካ፣ ውብ ኢትዮጵያዊ ቀለማትን በዜማው ያደምቃል፡፡
በፀሀይ ብርሃን ደምቃ ክረምትና በጋ
የትውልድ ሃገር ያላት የአስራ ሶስት ወር ፀጋ
ወግና ልማዳችን የወረስነው ካበው
አውዳመቱ ትዝታው አይጠፋም ያው ነው
እንኳን ደረስክ ሲባባል
ወዳጅ ከጎረቤቱ
ትዝታው መች ይጠፋል
አቤት ማስደሰቱ፡፡
አቤት ባዲሱ አመት
ዘመኑ ሲለወጥ
ያበቦቹ ሽታ መአዛው ሲመስጥ
ኮበሌው ሲጨፍር
ሲል መስከረም ጠባ
ኮረዳዋም ባታሞ
ስዞር በራሷ ቀዬ
አሲዮ መስቀል ሲመጣ
አሲዮ ደምቆ ደመራ
ሁሉም በደጁ ችቦ ሲያበራ
በልጅ ባዋቂው ደምቆ ጭፈራ
በልልታ ሎጋ ደምቆ ሲደራ
ከብረው ይቆዩን በሚል ጨዋታ
የልጅ ምርቃት ያባት ስጦታ
እያለ ይቀጥልና… ስለ ገና ጨዋታው ፣ ስለ ጥምቀቱ ፣ ስለ ፋሲካው ያነሳሳና ወዲያ ተሻግሮ ደግሞ ስለ ሐምሌና ነሐሴ፣ ደመናና ሰብል ብሎም ስለ ቀጣዩ ቡሄ፣ ዳግመኛም ስለ መስከረም ባማረው ድምፁ እንዳሻው ዓመቱን ያስሳል…..ኑሯችንን ይቃኛል፡፡
ዛሬ ጥላሁንን ማውጋት፣ ጥላሁንን መፃፍ፣ ጥላሁንን መተረክ የፈለግሁት ልደቱን ለማስታወስ ነው፡፡ ነገር ግን  ጥላሁንን ለማንሳት ደግሞ ምን ምክንያት ያስፈልጋል!…..እሱን ለማንሳት ምክንያት መፈለግ ማለት ስለ ኢትዮጵያ ለማውራት ሰበብ መፈለግ እንደማለት ነው፡፡ በኔ እምነት፤ ሀገርን ለመተረክና ስለ ሃገር ለመወያየት ሰበብ አያስፈልገንም…ጥላሁንም እንዲያ ነው ለኔ፡፡
እንደሱ ያሉትን ምልክትና አድባር የሆኑ ሰዎች አብዝተን ብናስታውስና ብንዘክር ዘወትር እንደሚባለው፣ መሰል ክዋክብትን ለማፍራትም ሁነኛ መላ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንድ ወቅት በዚሁ በ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ስለ ጥላሁን ገሠሠ በቀረበ ፅሁፍ ላይ እንዲህ የሚል አንብቤያለሁ…. ‹‹ዘፈን ለጥላሁን የእንጀራ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ቁስል ማከሚያ መድኃኒት መሆኑንም በታሪኩ ውስጥ እናያለን፡፡ ምናልባትም ከብዙ አድናቂዎቹ በላይ በዘፈኖቹ ስሜቱ የሚነካው ጥላሁን ራሱ መሆኑን፣ ጥላሁንን እንደ አዲስ የማወቅ ስሜት ይሰማናል›› ይላል፡፡
ጥላሁን ኢትዮጵያዊ ስሜቱን ለማከም ተፈጥሮ በቸረችው ተሰጥኦ፣ በትንፋሹ ሲታገስና ሲያባብል የኖረ ይመስለኛል፡፡ ህመሙንና ቁስሉን፣ ማዘንና መደሰቱን ሁሉ በሀገሩ ስር ሆኖ፤ በሃገሩ ቃል ሀገርን እየጠራ አንጎራጉሮላታል፡፡ ጥላሁንን ማስታወስ የክፍለ ዘመናችንን ሙዚቃ ማስታወስ ነው፡፡ ….. ብንጠቅሰው ብንዘረዝረው አያልቅም፣ ትንፋሹ ያረፈባቻውና የሱ ድምፅ በኪነት ያባበላቸው ሃሳቦች የትየለሌ ናቸው…ሁሉም እንደየመረዳቱ መጠን የተለየ አተያይ የሚመዝባቸው ስራዎቹም በርካታ ናቸው፡፡ ጥላሁንን ለመግለፅ ሻለቃ ክፍሌ የደረሱለትንና ዜማውን እራሱ ያሰናዳውን አንድ ምርጥ ስራ ልጥቀስ …..
“በአካል ሳይፈተን በአካል ሳይነካ
የማን ምንነቱ ግብሩ ሳይለካ
እርግጥ በተፈጥሮ በወል ስም ይጠራል
በቁም ነገር መድረክ ሰው ከሰው ይለያል”
ጥሌ ጥሩ ሃሳብ ሲያገኝ ዜማውን በሚፈልገው መንገድ እራሱ የመስራት ልምድም እንዳለው ባለሙያዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ….በቁም ነገር መድረክ ሰው ከሰው እንደሚለይ ጥላሁን እራሱን ማየት በቂ ነው፡፡ ሀገራችን ውስጥ በርካታ ድንቅ የሆኑ ባለሙያዎች አሉን፤ ይሁንና ከሁሉ በላይ ከፍ ባለ ስሜትና ጥልቀት….በመሰጠት ሙዚቃን መስሎ ሳይሆን ሆኖ በመኖር ፣ አያሌ ሃሳቦችንና ቁምነገሮችን አሳምሮ በማንጎራጎር ፣ ሲሻው እንደ አርበኛ፤ በል ሲለው እንደ ተዋናይ፣ ባስቀመጡት መድረክ ልክክ ብሎ አምሮ፣ በከፍታ በመስራት ጥላሁንን ‹‹በቁምነገር መድረክ ሰው ከሰው ይለያል›› ብንለው….ጎልቶ መለየቱን ብንነግረውና ዛሬም በምናብ ብናወጋው ስህተት እንደማይሆን አልጠራጠርም፡፡
ጥላሁን በተጠየቀበት መድረክ ሁሉ እንጉርጉሮ ህይወቱ መሆኑን፣ ያለ እንጉርጉሮ መኖርም ማሰብም እንደማይሻ ሲናገር ብዙ ጊዜ አድምጠናል፡፡ የሱ እንጉርጉሮዎች ሁሉ ጌጦቻችን፣ ትንፋሾቹ ሁሉ እስትንፋሳችን ሆነው ስሜታችንን በመኮርኮራቸው ምህኛት፣ ይህ ሰው ትክክለኛው የሙዚቃ ወዳጅ ብቻ ሳይሆን ጥላሁን ማለት ሌላው የሙዚቃ ስሟ ነው ብለን ቁጭ ብድግ ብለንለታል….ለዘመናት ትውልድ በስሜት ተቁነጥንጦለታል፡፡
በጦር ሜዳ ውሎ እነ‹‹ዘማች ነኝ››፣ ‹‹አጥንቴም ይከስከስ››፣ እነ‹‹ወደፊት በሉለት ይለይለት››፣ ‹‹ለውዲቷ ሀገሬ››ን የመሳሰሉትን በማቀንቀን፣ ከወታደሩ ጎን መቆሙን፣ ሀገር የሁላችን አድባር፣ የሁላችን አለኝታና መከታ መሆኗን ሲያንጎራጉር ኖሯል፡፡
ከመጀመሪያ ስራው ‹‹ጥላ ከለላዬ›› ጀምሮ እስከ መጨረሻ ስራው ‹‹ቆሜ ልመርቅሽ›› ድረስ ሀገር በትንፋሹ ስትነግስ፣ በድምፁ ስትከብር ኖራለች፡፡
‹‹ትንፋሼ ተቀርጾ ይቀመጥ ማልቀሻ
ይህ ነው የሞትሁ’ ለት የኔ ማስታወሻ››
ብሎ ነበር የሙዚቃ ንጉሱ ጥላሁን ገሰሰ:: በእርግጥ እሱ እንዳለው ትንፋሹ ነው ማስታወሻችን፡፡ በትንፋሹ ውስጥ ያንቆጠቆጣት ኢትዮጵያም እንዲሁ፡፡ ጥላሁን፤ ለዝንታለም ትንፋሹ ትንፋሻችን ሆኖ ወደፊትም ይዘልቃል፡፡

Read 890 times