Print this page
Tuesday, 08 October 2019 10:25

አበሻ ምን ነካው ዛሬ?!

Written by  ነ.መ
Rate this item
(1 Vote)

የዛሬን አዳራሽ በሆንኩ
ዛሬን ብቻ አበሻ በሆንኩ
የአበሻ ልጅ ነቅሎ ወጥቶ፣ ባንድ አዳራሽ ተሰብስቦ
የአንድ ድምጽ ልደት ያክብር፣ የረሳውን ኮከብ ከቦ?!
ያለ ባህሉ? ያለ አመሉ?
አበሻ ምን ነካው በሉ?
ምን ምልኪ ነው በበለስ፣ ከቶ አለ ውሉ መዋሉ፡፡
ኧረ አበሻ እንዲህ አያውቅም፣ ዛሬ ነው የተወለደ
ያገር ኮከብ ያከበረ
ከ60 ዓመት ዋርካ ጥላ፣ ከአድባር ዛፍ ሥር የዘመረ
ክታብ መቁጠር የጀመረ፡፡
በበለስ ዛሬ ነው ኧረ!
ዛሬን ብቻ አበሻ በሆንኩ፡፡
ወዲያ ከወደ ወሊሶ
አንድ አራስ ድምፅ ተፀንሶ
እናት ልጅ ወለድኩ ብላ
አንቀልባ ሙሉ ድምፅ አዝላ
ልቅሶ መስሏት ስታባብል
በዝማሬው ስትማልል
ጥላሁን ብላ ብታዝለው፣ እሱ ፀሐይ ሆኗል ነግሦ
ከአድማሳት በላይ ነፍሶ
የሳቁን የዕንባውን አምባ፣ የዘመናት ግድብ ጥሶ
አንድ አገር ሙሉ ልደት፣ በአንድ ቀን አብራክ ደግሶ
የህዝቦች ኮንሰርት አወጀ፣ ስልሳ ጧፍ ባፉ ለኩሶ!!
ጠዋቶቻችን ባነሱ፣ ማታዎቻችን ሲስቁ
በአርባ ቀን ዕድል ታጅሎ፣ ሰው መኖር ሲሆን ጭንቁ
የልብ እህል - ውሃ ጥበብ፣ ሲያልም ለመንፈስ ትጥቁ
ሲያምጥ ለነብስ ስንቁ
ድምፆች መጅሊስ ተቀምጠው እንዲሰሙ ሲጨነቁ
ስንቶች ጆሮ ሲለምኑ ሲሰቀቁ… ሲባርቁ
ሲስረቀረቁ… ሲጠልቁ፣ ሽቅብ ሲነሱ ሲወድቁ
ያደለው እሱ፣ በዜማው፤ የዓለምን ልብ ይገዛል
በየዕለት መፈጠሩ አንሶት፣ በስልሳ ዓመት ይወለዳል!
ያደለው ሕዝብም በወጉ ልደቱን ያከብርለታል፡፡
እንደወግ ልማዱማ ለእንጉሥና ላገር በቀር
ማን አበሻ ሰምቶ ያቃል የኮከብ ልደት ሲከበር?!
አበሻ ምን ነካው ዛሬስ፣ ሰው በቁም ማክበር ጀመረ?
‹‹ድምፅ ተወለደ!›› ብሎ ባንድ ቅላፄ ዘመረ
ብሔራዊ ሻማ አበራ ብሔራዊ ኮከብ ጫረ!!
አበባ ለቀብር በቀር፣ ለኗሪ ማኖር ዌት-ተማረ?
ወቸ ጉድ ያበሻ ልጅ፤ ሰማይ ምድሩ ዛሬ አማረ
ዜማ እንደ ሐውልት ተክሎ፣ ውበት እንደ ቅርስ አኖረ
አበሻ ዛሬ ሻረ!
በድንገት እንደ ፈለቀ የድምፅ - አገር - ፍቅር ጠበል
አንደዜ ቃሉን አምጥቆ፣ ምድር ከሰማይ ቢያቻችል
ዕፅዋት ጆሮ እስኪያበቅሉ፣ ጽጌረዳ እስክትፈነዳ
ተራራው እስክስታ እስኪወርድ
የዜማ ቆሌ እስከምታብድ
ፍቅር እንስራውን አዝሎ፣ በሌሊት ወንዝ እስከሚወርድ
ይዘፍናል ያ ድምፅ በእልህ
የድምፆች ሁሉ ንጋት ጎህ
የቋንቋዎች ሁሉ ፅባሕ
ሲሻው ይሰርጋል ወይ ያርጋል
ሲሻው ያረገርጋል
አሊያም አርምሞን ያዜማል
ቃሉን ሁሉ ፀሎት አርጎ፣ ነብስን ሱባዔ ይከታል
የውሃ - ጉንጉን ቀለበት፣ በሠራ-አካለት ያሰርጻል
የዘፈን ጥቢ ነው ልደቱ
ይባቤ ዝማሬ ሽቱ
የድምፅ ሐዋዝ ሞናሊዛ፣ የገጠር-ቴምር ነው ጣሙ
ከማንቃቱ ማስለምለሙ!
አበሻ ይሄን ካከበረ የኮከቡን ልደት አየ
ዛሬስ ከእርግማኑ ማህል ምርቃቱን አበራየ!
ለበደለው ሁሉ ካሳ
የሞቱትን ሁሉ አስነሳ!
የሌለ ህይወት ፈጠረ
የሌ መዝሙር ዘመረ
የሌለ ምክር መከረ
ምን ፍርጃ ጣለበት ቁጣ
የሌለ አንድነት አመጣ!!

ማስታወሻ
(ለጥላሁን ገሰሰ በሕይወት ሳለ የልደት በዓሉ በብሄራዊ ቴአትር ከተከበረለት በኋላ የተፃፈና በዚሁ ጋዜጣ ላይ የወጣ ግጥም ነው)


Read 1573 times