Print this page
Saturday, 12 October 2019 12:15

ቪንሰንት ቫን ጐህና ኢትዮጵያዊው ወጣት የተጋሩት ችግር

Written by  ዮናስ ባህረጥበብ (ዶ/ር)
Rate this item
(2 votes)

  በ1980ዎቹ መጨረሻ በአንዱ ዕለት፣ አንድ መልከ መልካም ወጣት፣ በአምስት ቤተሰቦቹ የፊጢኝ ታስሮ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል መጣ፡፡ ዕድሜው በ20ዎቹ መጨረሻ የሚገመተው ወጣት፤ ፉከራና ቀረርቶ ያሰማል፡፡ የተለያዩ ዘፈኖችን እየደበላለቀ ያንጎራጉራል፡፡ ደስታው ከመቅጽበት ተለውጦ ከፍተኛ ሀዘንና ቁጭት የተሰማው መሆኑን ከንፈሩን በመንከስ ይገልጻል፡፡ ወጣቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ተወላጅ መሆኑን ከአነጋገሩ ቅላጼና ከሚጠቀማቸው ቀበሌያዊ ቃላት መረዳት ይቻል ነበር፡፡  
በዕለቱ በድንገተኛ ክፍል ውስጥ የነበርነው የጤና ባለሙያዎች፣ ወጣቱን ለማረጋጋት ጥረት ካደረግን በኋላ፤ የሆነውን ለማወቅ ከቤተሰቡ መረጃ ማሰባሰብ ጀመርን፡፡ ቀዳሚውን ምስክርነት የሰጡን የወጣቱ ወላጅ አባት ነበሩ:: ልፍሰስ እያለ የሚታገላቸውን ዕንባ ለማቆም እየታገሉ፣  አንገታቸውን አቀርቅረው በእግራቸው መሬቱን እየቆረቆሩ፣ ከሁለት ቀን በፊት ወጣቱ በራሱ ላይ የፈጠረው አደጋ አስደንጋጭና አሰቃቂ እንደነበር ተረኩልን፡፡ ልጃቸው መራቢያ አካሉን (ብልቱን) በቢላ ለመቁረጥ ሞክሮ፣ ብዙ ደም ስለፈሰሰው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወስደው ካሳከሙት በኋላ፤ የአእምሮ ሕክምና እንደሚያስፈልገው ስለተነገራቸው ነበር ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ያመጡት፡፡
ወጣቱ በራሱ ላይ እንዲህ ዓይነት አደጋ ከማድረሱ በፊት ያሳያቸው ስለነበሩ ምልክቶች ሌሎች የቤተሰቡ አባላትም ምስክርነታቸውን ሰጡን፡፡ ወጣቱ ዕድሜው ለአቅመ አዳም ከደረሰ በኋላ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ የጭንቀት ምልክቶች እንደሚታዩበት፣ የጭንቀት ምልክቶቹ የዓመት በዓላትን አስታከው እንደሚቀሰቀስበት አመልክተው፣ የባሕሪ ለውጥን የገለጹት በሚከተለው መልኩ ነበር፤ ‹‹አንድ ጊዜ እሳት፣ ሌላ ጊዜ በረዶ ይሆናል:: እሳት ሲሆን እኔን ስሙኝ፣ እኔን አዳምጡኝ፣ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ ይላል፡፡ ገንዘቡን ይበትናል:: አልረባም፣ ጥይት ጠጥቼ ልሙት፣ እራሴን አጠፋለሁ ይላል፡፡ በረዶ ሲሆን ደግሞ ከዚህ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ፀባይ ያሳያል፡፡››
በአማኑኤል ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ያለነው የጤና ባለሙያዎች፣ የሕክምና ዕርዳታ ፈልጎ ከመጣው ቤተሰብ ጋር በተያያዘ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ትዕይንቶችን ነበር የምንመለከተውና የምንሰማው፡፡ የራሱን መራቢያ አካል በቢላዋ በመተልተሉ ምክንያት ከወገብ በታች በፋሻ የተጠቀለለ ወጣት፣ በሆነው ነገር ጥልቅ ሀዘን የተሰማቸው ወላጅ አባት፣ ለደረሰው አደጋ ‹‹እኔ የምሰጠው መረጃ መፍትሔ ያመጣ ይሆናል›› ብለው ያመኑ ቤተሰብና ጓደኞች ምስክርነት … በአንድ ክፍል ውስጥ ነበር - ይህ ሁሉ የሚሆነው፡፡
በዕለቱ አይና እሰማው የነበረው ነገር፣ የተለያዩ ጥያቄዎችን በአእምሮዬ ፈጥሮብኝ ነበር፡፡   ሰው በራሱ ላይ እንዴት እንደዚህ ሊጨክን ይችላል? በምንስ ምክንያት ይሆን እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ላይ ሊደርስ የሚችለው? እራሱን ቢጠላ ይሆን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው?  ለተመልካች ጥልቅ ሀዘን፣ ከዚያም ከፍ ሲል የማቅለሽለሽና የማዞር ስሜት ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ፣ ቁስለትና ሕመሙን እንዴት  ቢችለው ነው ፉከራና ቀረርቶ የሚያሰማው? በፉከራና ቀረርቶ መሐል የሚታየውስ የሀዘን እንጉርጉሮ ከየት የመጣ ነው? ‹‹ወንድ ነኝ፣ ጀግና ነኝ›› የሚል ብርታት ያዘለ ገለጻና ‹‹በቃ አለቀልኝ›› የሚል የሀዘንና የተስፋ ቢስነት ስሜት በአንድ ጊዜ የሚመጡበት ምክንያትስ ምን ይሆን? እንዲህ ዓይነት ሁለት ተቃራኒ ክስተት (እራስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ መፎከርና ማዘን) በኢትዮጵያዊያን ብቻ የሚታይ ነው፤ ወይስ ዓለም አቀፋዊ የአእምሮ ሕመም ምልክት ይሆን?  የሚሉና መሰል ጥያቄዎች በአእምሮዬ ተመላልሰዋል፡፡
በዕለቱ ከማየውና ከምሰማው በመነሳት፣ በእኔ አእምሮ ውስጥ እነዚህ ጥያቄዎች እንደተነሱት ሁሉ፣ የሕክምና ባለሙያ የሆኑት የሥራ ባልደረቦቼም በተመሳሳይ ሁኔታ የሚሰማቸው የተለያየ ስሜት፣ ለየግላቸው የሚያነሱት ጥያቄም ይኖራቸዋል፡፡ የሆነ ሆኖ በራሱ ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰውን ወጣት ማገዝ ሙያዊ ግዴታችን ስለሆነ፤ ለእንዲህ ዓይነቱ ችግር የተማርነው የሕክምና ትምህርት ያስቀመጠውን ምክንያትና መፍትሔ መሠረት አድርገን፤ ወጣቱን በመርፌ ካረጋጋነው በኋላ፣ ለተሻለ ሕክምና ተኝተው ወደሚታከሙበት ክፍል አስተላለፍነው፡፡  
በሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍል ገጥሞኝ ካየሁትና ከሰማሁት በመነሳት በውስጤ የፈጠረውን ጥያቄ፣ በምሳ ሰዓት ላገኘኋቸውና ከእኔ የተሻለ ልምድና ዕውቀቱ ለነበራቸው ሐኪሞች አቀረብኩላቸው፡፡ በሻይና በምሳ ሰዓት በሥራ ላይ ባጋጠሙን ጉዳዮች ላይ እንወያይ ነበር፡፡  በሁሉም የሥራ ዘርፍ ጀማሪ ባለሙያዎች ከአንጋፎች ብዙ ልምድና ዕውቀት ማግኘታቸው የታወቀ ነው፡፡ የአእምሮ ሕክምናን በተመለከተ በመደበኛ ትምህርት ካገኘነው ዕውቀት ባልተናነሰ መልኩ፣ በኢ-መደበኛ ግንኙነት የተማርነው ብዙ ነገር አለ፡፡ ከአራት መቶ ዓመታት በፊት ዋሻ ውስጥ የተገኘው ‹‹ዴዝዴራታ›› ላይ ከሰፈሩ መልዕክቶች አንዱ፣ ጊዜ ወስደን በጥሞና ካየንና ከሰማን ‹‹ደደብ›› እና ‹‹አይረቡም›› ከሚባሉ ሰዎችም ብዙ ቁም ነገርና ትምህርት እንደሚገኝ ይመክረናል፡፡ ከእኛ የሚፈለገው ግን የሕይወት ዘመን ተማሪ ለመሆን መዘጋጀትና መጠየቅ ብቻ ነው፡፡
ጥያቄዬን የሰሙት አንጋፋ ባለሙያዎችም፣ በዕለቱ በድንገተኛ ክፍል የገጠመን ችግር ‹‹ቫን ኮህ ሲንድሮም›› እንደሚባልና ቫንጎህ ከሚባል አርቲስት ጋር በተያያዘ የተሰየመ የሕመም ምልክት መሆኑን አብራሩልኝ፡፡ ያገኘሁት ምላሽ ሌሎች ጥያቄዎችን እንዳነሳ ጋብዞኝ ነበር፡፡ ቪንሰንት ቫን ጐህ (Vincente – van Gogh) ማን ነው? ከአእምሮ ሕመሞች አንዱ በእሱ ሥም እንዲሰየም ምክንያት የሆነበት ታሪክና ክስተት ምን ነበር? ከሰሜን ኢትዮጵያ የመጣው ወጣት ገበሬና የቫን ጎህ ሕመማቸው በምን ይመሳሰላል፤ በምንስ ይለያያል?
ቪንሰንት ቫን ጐህ እ.ኤ.አ ከ1853 እስከ 1890 የኖረ ሆላንዳዊ ሰዓሊ ነው፡፡ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ውስጥ አልፏል፡፡ ረዳት ፀሀፊ ሆኖ በሙዚየም ውስጥ አገልግሏል፡፡ አስተማሪ ሆኖ ሠርቷል፡፡ ማስተማሩን ሲያቆም የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪ ሆነ፡፡ መጽሐፍ ነጋዴም ነበር::  የ27ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ካከበረ በኋላ ነበር ከስዕል ጋር የተዋወቀው፡፡ ‹‹በሥዕል ፍቅር የተለከፍኩት ከልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ ነው›› የሚል ሰው አልነበረም፡፡ ሥዕልን በ27 ዓመት ዕድሜው ‹‹ሀ›› ብሎ በመጀመር ድንቅ ሰዓሊ መሆን ችሏል፡፡
ቬንሰንት ቫን ጐህ አርልስ የምትባል ትንሽ የፈረንሳይ ከተማ ከሄደ በኋላ እስካሁን ድረስ ዓለም የሚደመምበት ‹‹የሱፍ አበባ›› የሚባለው ስዕሉን አበረከተ፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ዓለምን እያስደምሙ ያሉ ከ300 በላይ ሥሎችን ለዓለም አበረከተ፡፡ አሁን በእኛ ሀገር ሰዓሊዎች እንደሚታየው፤ በቪንሰንት ጐን ኮህ ዘመን፣ ሰዓሊዎች አንድ ቤት እየኖሩ ሥዕል መስራት የተለመደ ነበር፡፡ ቪንሰንት ቫን ጐህ ከጓደኛው ጋር በአንድ ቤት ቢኖርም፣ ስለ ስዕል የነበረው አመለካከት ከጓደኛው የተለያየ ስለነበር ሁሌ ይከራከሩና ይጨቃጨቁ ነበር፡፡
እንደተለመደው አንድ ምሽት ላይ ሁለቱ ጓደኛማቾች ስዕልን በተመለከተ ሲጨቃጨቁ ርዕሰ ጉዳዩ ክርር ሲል፣ ቪንሰንት ቫን ጐህ ስለታም ካራ አነሳ፡፡ ጓደኛው ነገር ለማብረድ ይሁን ወይም ፈርቶ በሩን በርግዶ ወጣ፡፡ ቪንሰንት ቫን ጎህ በያዘው ስለታም ካራ አንድ ጆሮውን ሙሉ ለሙሉ ከቆረጠው በኋላ፣ በጨርቅ ጠቅልሎ በሴተኛ አዳሪነት ወደ ምትተዳደረው ወዳጁ ቤት ሄዶ የጆሮውን ቁራጭ በስጦታ መልክ አበረከተላት፡፡
የሀገራችን አንጋፋው አርቲስት ማህሙድ አህመድ ‹‹እንኪ ልቤ እኮ ነው፣ ስንቅሽ ይሁን ያዢው…›› እንዳለው፣ ቪንሰንት ጐን ኮህም ለወደዳት ሴት ‹‹እንኪ ጆሮዬን እኮ ነው፣ መስሚያ ይሁንሽ ያዢው…›› ያላት ይመስላል:: ቫን ጎህ የጆሮውን ቁራጭ ለሴተኛ አዳሪዋ ካበረከተ በኋላ ‹‹አደራ ተንከባከቢኝ›› ማለቱ ይነገራል፡፡
ከአእምሮ ሕመም ዓይነቶች አንዱ ለሆነውና ለ‹‹ቫን ጐህ ሲንድሮም›› ስያሜ ምክንያት የሆነው ይህ ድርጊቱ ነበር፡፡ በአሁኑ ዘመን የቪንሰንት ቫን ጐህ ስዕል አድናቂዎች ስዕሉን ብቻ ሳይሆን ጆሮውን በገዛ እጁ ቆርጦ ለወደዳት ሴት በመስጠቱ ጭምር ያስታውሱታል፡፡ በ1980ዎቹ መጨረሻ በአማኑኤል ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል የገጠመኝና ከሰሜን ኢትዮጵያ የመጣው ወጣት ገበሬ ታሪክም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡
በራስ አካል ላይ ጉዳት በማድረስ ችግር ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች፣ አካላቸውን በስለት ሲቆርጡ፣ ራሳቸውን ሲነክሱ… ድርጊቱን እንዲፈጽሙ የሚገፋፋቸው የተለያየ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ስኪዞፍሪንያ የሚባል ከፍተኛ የአእምሮ ሕመም፣ ጉዳት ያደረሱበት አካላቸው ክፍል ጥፋተኛ ነው ቅጣት ይገባዋል ብለው በተሳሳተ መልኩ እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ለሌላ ሰው የማይሰማ፣ እነሱ ብቻ የሚሰሙት ድምፅ በሚያዛቸው መሠረት ትዕዛዙን ተቀብለው ሊሆን ይችላል - በራሳቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱት፡፡
ቪንሰንት ቫን ጐህ ጆሮውን በመቁረጥ ብቻ አላቆመም፡፡ እራሱ ደረቱን በሽጉጥ አቁስሎ በሁለተኛው ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተሰናብቷል:: ለምን እራሱን እንደገደለ የተለያዩ መላ ምቶች ቢኖሩም እስካሁን ትክክለኛው መረጃ አልተገኘም፡፡ የሕይወት ታሪኩንና ትቷቸው የሄደው ሥራዎቹን ያጠኑ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት፤ ቫን ጐህ አልፎ አልፎ የሚመጣ የአእምሮ ሕመም እንደነበረው ይገልጻሉ፡፡ የዛሬ 30 ዓመት አካባቢ ከሰሜን ኢትዮጵያ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል የመጣው መልከ መልካም ወጣት ገበሬም በወቅቱ የአእምሮ ሕክምናውን ተከታትሎና ተሽሎት ወደ ትውልድ መንደሩ ተመልሶ የግብርና ሕይወቱን ሲመራ ለብዙ ዓመታት ቆይቷል፡፡ መድኃኒቱን በማቋረጡ ምክንያት ግን ከገደል አፋፍ ላይ ዘሎ እራሱን ማጥፋቱን የዛሬ ሁለት ዓመት በአጋጣሚ ያገኘኋቸው አባቱ ነግረውኛል፡፡
ሰዎች በራሳቸው ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ የሚያነሷሷቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው? በራስ ላይ ጉዳት በማድረስና እራስን በራስ በማጥፋት መሐል ያለው አንድነትና ልዩነት ምንድነው? በሁለቱም ድርጊቶች ላይ የአእምሮ ሕክምና ሳይንስ ጥናትና ባለሙያዎች ምላሽ ምን ይመስላል? በችግሩ ላይ የተለያዩ ኃይማኖቶችና የኃይማኖት አባቶች ምልከታ ምንድነው? የሕብረተሰብና ማሕበረሰብ ባህል፣ ወግና ልማድ ለችግሮቹ መስፋፋትና መቀረፍ ያላቸው ሚና ምን ይመስላል? በጠቅላላስ በኢትዮጵያ ያለው የአእምሮ ጤና ችግርና ተስፋ ከዓለም አቀፉ ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል? ችግሩን በተመለከተ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ለአንድ ወር በሚዘልቀው መርሐ ግብር ላይ እነዚህን ጥያቄዎች እያነሳን እንድንወያይባቸው በማሰብ ነው ይህን ጽሑፍ ያሰናዳሁት፡፡   
ከአዘጋጁ፡- ፀሐፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የአዕምሮ ህክምና ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 7973 times