Saturday, 12 October 2019 12:16

የገብረክርስቶስ ብትንትን ግጥም

Written by  ደ.በ
Rate this item
(1 Vote)

ገብረክርስቶስ ደስታ በስንኙ ዳንሶች ነፍሱ የሰከረች ገጣሚ ነው፡፡ እንደ አጀማመሩም ግጥም ከዳንስ ጋር መንትያ ነው፡፡ የተወለዱት በተመሳሳይ ዘመን፣ በአንድ ዓይነት ክዋኔ ውስጥ ነው፡፡ እንደ ኤሣውና ያዕቆብ፣ አንዱ ያንዱን ተረከዝ ይዞ ሳይሆን እኩል ዐይናቸውን ከፍተው፣ እኩል ልብ አቅልጠው ታሪክን መቀላቀላቸውን የዘርፉ ሊቃውንት በተደጋጋሚ ጽፈውልናል፡፡
ታዲያ ገብረክርስቶስ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በሚል ርዕስ የታተመው መጽሐፉ ውስጥ ሰዓሊ እንደመሆኑ መጠን፣ ቀለምን በስምና ቀለምን በተፈጥሮ፣ እየደጋገመ የሚገልጽባቸው ግጥሞች ጥቂት አይደሉም፡፡ በተለይ “አንተ ነህ መስከረም” የሚለው ግጥሙ አምስት ጊዜ ያህል ሲጠቅስ ጥቁር አረንጔዴ፣ ንፁህ አረንጓዴ፣ ከጫማ አረንጓዴ፣ ያተር አረንጓዴ እያለ በዝርዝር አይቷቸዋል፡፡
በተለይ ሙዚቃን በሚመለከት ክራር፣ ከበሮ የሚል ርዕስ የተሰጣቸው ግጥሞች ተጽፈዋል:: ይህም፤ ገጣሚ ከሙዚቃና ዜማ ጋር ያለውን ቅርበት ለማሳየት ዋቢ የሚሆን ይመስላል:: ሙዚቃና ግጥም ሁለቱም መነሻቸው ስሜት ነው፤ ከዚያ በኋላ ባንዲራውን ሲያውለበልብ ነፋስ ላይ የሚደንሰው ደግሞ ዜማ ነው፡፡ ለዚህ ነው፡፡ S.A Greening Lamborn `To exist as a poetry, emotion must be translated into music and visual images, clear and beautiful” የሚሉት፡፡ ግጥም በስሜት ወጀብ ነፍስን አናውጦ፣ ግጥም ሲፈጠር ሙዚቃና ምናባዊ ሥዕል ይከስታል፡፡ በዚህ መከሰት ውስጥ ውበት አይኖቹን ኩሎ፣ ሸማውን አጥቦ ብቅ ይላል፡፡
ይህ ስሜት ታዲያ ደስ በሚል ሁናቴ ውስጥ ብቻ አይደለም፡ ሀዘን በተከመረበት የሰው ልጆች ህይወትም ውስጥ የውበት ቬሎ አጥልቆ ብቅ ይላል፡፡ በእንባ ሰገነት ላይ የማይተነተን ቁንጅና የማይዘልቅ የምናብ ሽርሽር ወደ ጥበብ ሀገር ያሳፍራል፡፡ ይህንንም ከላይ የጠቀስኳቸው ሲቅ እንደሚከተለው ይገልፁታል፡፡ “They may be terrible or Saddling, but still beautiful for it has been said that the greatest mystry of poetry is its power to invest the saddest things with beauty”
በዚህ ሃሳብ ሌላም አሜሪካዊ የስነ ግጥም ፕሮፌሰር በእጅጉ ይስማማሉ፡፡ በእሳቸው አባባል ግጥም ማለት አንድን አሮጌ ወይም ነባር ነገር በአዲስ ዓይን ማየት ነው፡፡ ምናልባትም የሀዘኑን ድንኳን ወደ ሳቅ እልፍኝ መቀየር!
ገብረክርስቶስ ሰዓሊ ስለሆነ በመጽሐፉ ውስጥ ባሉት ግጥሞች ብዙ ስዕሎችን በቃላት ይሠራል፤ ስለዚህም ምሳሌዎቹ በእጅ የሚዳሰሱ ያህል ቅርብ ናቸው፡፡ ሥዕል ደግሞ ሃሳብን በሰዎች ምናብ ውስጥ ለማስቀመጥ በጣም ትጉህ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሌላው ቀርቶ “በእጅጉ ግጥምን አይወድም” የሚባለው ዳርዊን ለሚሰራቸው ጥናቶች ትርጓሜ - ቅርብነት ሲል ሥዕላዊ ገለፃ ይጠቀም ነበር፡፡ ገብሬ ደግሞ የወጣለት ሰዓሊና በስሜት የነደደ ገጣሚ ነበርና ይህንን በጉልህ አሳይቶናል፡፡
ገብሬ በፍልስፍናው ወይም በሚከተለው ርዕዮተ ዓለም የእርሱን ዘመነኞች ይመስላል:: በግጥሞቹ እንደሚስተዋለው ሶሻሊስታዊ ድምፀት አለው፡፡ ለጭቁን ህዝቦች መቆርቆር፣ አማልክትን መውቀስ፣ የጭቆናን ቀንበር ማስወገድ ይፈልጋል፡፡ በብዙ ነገሩ አፈንጋጭ ነው፡፡ በህይወቱ፣ በአኗኗሩ… በእምነቱ ከአብዛኞቻችን የተለየ መንገድ አለው፡፡
በግጥሞቹ ውስጥ እነዚህ ሁሉ ፍንገጣዎች እንዳሉ ሁሉ፣ በገፁ ጽሑፋዊ ቅርጽ አቀማመጥም ያፈነገጠበት ግጥም አለ፡፡ ግጥሙ የተበታተነ ቤት ውስጥ ያሉ ቁሳቁሶችን የሚያሳይ ነው:: ታዲያ ያን መበታተን ለማሳየት የግጥሙን አርኬዎች በወግ አልደረደራቸውም፤ ልክ እንደ ቤት ዕቃው በታትኖ ስሎዋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ምናልባት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4ኛው ክፍለ ዘመን ገደማ የተጀመረውና በጥንታዊት ግሪክ የነበረው… በ16ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ፣ ከዚያም በኋላ በሌሎች አገራት ገጣምያን እየተለመደ የመጣ ነው፡፡ የግጥሙን ገፀ - ጽሑፍ ቅርጽ በስዕል ማሳየት የተከተለ ነው፡፡
ይህ ዐይነቱ ፍንገጣ፣ በጥንታዊ ግሪክ ዘመን የተጀመረ ቢሆንም በሀገረ እንግሊዝም የተለመደ እንደነበር የስነ ጽሑፍ ታሪክ ይነግረናል፡፡ በኛም ሀገር ገጣሚ ጌትነት እንየው፣ ደበበ ሰይፉና ሌሎችም ወጣት ደራስያን ይህንን መንገድ ሲለማመዱት ይታያል፡፡ ይሁንና የገብረክርስቶስ ደስታ ፍንገጣ ግን “ለምን መበታተን ሆነ?” ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡
ምናልባት ሰውየው ልቡ ወደ ግጥሙም ወደ ሥዕሉም  ስለተከፋፈለ ይሆን… የቤቱ ዕቃ የተከፋፈለው? ለምን አልተሰበሰበም?! ደግሞስ በመግቢያ ግጥሙ “ሞኜ ተላላ” እንደሚለው ህይወት ጥድፊያና ድንገት ብቅ ብላ የምትከስም ምትሀት - ስለሆነች በዚያ ጥድፊያ ውስጥ መሰብሰብ አቅቶት ይሆን?! ደግሞም በሌሎች ግጥሞቹ ንፋስ - ሽውታ አውሎ የሚል ነውጥ፣ ውስጡ ነግሶ ይሆን?! የቱንም ነገር የሚበትነው ንፋስ ነውና! የሚያወዛውዘውም አውሎ ነው:: ይህ ደግሞ ስሜት ይፈጥራል፣ ስሜት ደግሞ ሃሳብ ላይ ይጥላል፣ ሃሳብ ሲፈተግ ግጥም ብቅ ይላል፤ ግጥም ደግሞ ሙዚቃና ዳንስ ያመጣል:: ታዲያ ንፋሱ የሚያስደንሳት ነፍስ ያመጣችው ሙዚቃ ይሆን? ነፍሱን ያመሳቀላት? ስነ ልቡናዊ ሕይወት ታሪካዊ ጥናት የሚያሻው ነገር ይመስለኛል፡፡ እስቲ “የሚያፅናኑት” የሚለውን ግጥሙን እንመልከት - ቃላቱና ሀረጋቱ ተበታትነዋል፡፡
ጅምር ሥራ
በየጊዜው የሚያድግ፣
ቀን የሚገፋ
ትንሽ ክፍል
ከዓለም ጣጣ የምትከልል፤
በገብረክርስቶስ ህይወት አውድ፤ ጅምር ሥራ ያለው፣ ግጥም ወይም ሥዕል ነው ብለን መገመት ይቀርብናል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ተጀምረው፣ ቀስ በቀስ ያድጋሉ፤ ጊዜ ይገፋሉ፡፡
ደሞ ትንሽ ክፍል አለች፤ እርሷ ከዓለም ጣጣ ትከልላለች፡፡ ይህ ክለላ ውጭ ከሚታየው የድሆች ጩኸት፣ የጭቆና ሰቆቃ፣ ወይም ወደ ግለሰብ ካመጣነው፤ ከብርድ ከውርጭና ከሀሩር የምትከልል ለማለት ይሆናል፡፡ ግን የግጥሙ ቃላትና ሀረጋት አልተሰበሰቡም፡፡ ባልተሰበሰበ ነፍስ በተሰጠ ስሜት እንዴት የተሰበሰበ ስንኝ ይታያል?
ትንሽ ወንበር፤
የምታቅፍ፣
የምትደግፍ፣
አሮጌ ልብስ                   አብሮ ያረጀ
የነተበ፡፡
የዚህ ቤት ኑሮ ጐስቋላ ነው፡፡ ወንበሯ ትንሽ ናት፡፡ ግና ታቅፋለች፣ ትደግፋለች፡፡ ታሳርፋለችም፡፡ ልብሱ አሮጌ ነው፤ የነተበ፡፡ ኑሮው ደስ አይልም፡፡ ሳቅ የተሞላ ቤት፣ የተሳካ ኑሮ አይነካካም፡፡ ብዙው ነገር ጥሩ ቀለም የለውም፡፡ ድምጽ የሌለው ጩኸት፣ ችሎት ያልቀረበ ክስ ይደመጥበታል፡፡
አሮጌ ጫማ             ያገለገሉ፤
የለፋ
ማንቆርቆሪያ፣ ሳህን ውሃ                  ውሃ መታጠቢያ
ፎጣ የሚሻክር                          ምድጃ ከሰል እሳት፣
እሳት፣ ሙቀት
ጫማው የደከመና የለፋ… ብዙ የተሄደበት የከርታታነት ማሳያ ይመስላል፡፡ ምናልባት በዚያ የለፋ ጫማ፣ የተገጠበ እግር ማጠቢያ የሚመስል ሣህንና ውሃ፣ ማንቆርቆሪያ አለ፡፡ ማንቆርቆሪያው የሻይ አይደለም፤ መታጠቢያ ነው፡፡
ውሃውም ቀዝቃዛ አይመስልም፣ ምክንያቱም ከሠልና ምድጃ አለ፡፡ እሳት አለ፤ ሙቀት አለ፡፡ አጠቃላይ ሁኔታው በባለፈው ጫማ የዋለው ሰው እግር መታጠቢያ ነው፡፡ ይህንን ሃሳብ የሚያግዘው የሚሻክር ፎጣ መኖሩ ነው፡፡ ፎጣውን ያሻከረው ዕድሜና አገልግሎት ነው፡፡ ምቾት የማይሰጥ ፎጣ ነው፤ ቢሆንም ማድረቂያ ይሆናል፡፡
ዳቦም አለ፡፡
ወተት በጠርሙስ
ቁራሽ ዳቦ           ፍሬ በሳህን
ሲጃራ
የተጋመሰ
የተጨሰ
እዚህ ቤት ሙሉ ነገር የለም፡፡ ዳቦው ቁራሽ ነው፤ የሚጨስ ሲጃራው የተጋመሰ ቁሬ:: ስለ ፍሬው ብቻ አናውቅም፡፡ በሣህን ላይ ተቀምጧል፡፡
ይህ ዳቦ፤ የተጋመሰ ዘመን ማሳያም ሊሆን ይችላል፤ የተገባደደ እህል ውሃ… የአጭር የህይወት ዘመን ስንቅ ተምሣሌት በጠርሙስ ያለው ወተትም ደረቁን ዳቦ ማማጊያ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ እሣቱ ለውሃው ማሞቂያ ብቻ ነው፡፡
የጐረቤት ሙዚቃ
ከሩቅ የሚመጣ
ደብዳቤ         ማስታወሻ ደብተር         ጋዜጣ
የዘመድ ፎቶግራፍ             የወዳጅ
የራስጌ መብራት         የግድግዳ ጥላ
የተሰቀለ ሥዕል
መጻሕፍት         መጻሕፍት     መጻሕፍት፤
ቤቱ ውስጥ ሙዚቃ የለም፤ እንደ ሰመመን የሚሠማ፣ የሚስረቀረቅ የሩቅ ድምጽ ግን አለ:: ጆሮው ውስጥ ይደልቃል፡፡ ይህ የአየር ጉዞ፣ የድምጽ ምስል ነው፡፡ ምሠላ (Imagery) ነው፡፡
ደሞ ደብዳቤ ተቀምጧል፤ ጠረጴዛ ላይ ይሁን፣ ሌላ ነገር ላይ አይታወቅም ማስታወሻ ደብተር፣ ጋዜጣም አለ፡፡ መጻሕፍት ግን በብዛት አሉ፡፡ እዚያም እዚያም መጻሕፍት አሉ፡፡ የተገለጡ ይሁን የተከደኑ አናውቅም፡፡ ግን አሉ::
ፎቶግራፎችም አሉ፡፡ እንደኛ ዘመን በአልበም ሳይሆን በፍሬም ውስጥ በመስታወት ግድግዳ ላይ የተሰቀሉ ናቸው ብሎ መገመት ይቻላል:: የገጣሚውን ዘመን የሚያሳየን ያንን ልምድ ነው::
የራስጌ መብራቱ፣ ምናልባት እነዚያን በየቦታው የተደረደሩ መጻሕፍት ለማንበብ የተዘጋጀ ነው፡፡ የግድግዳው ጥላም በዚያ የራስጌ መብራት ሙሉ ክፍሉ ስለማይታይ ከፊል ጥላ በግድግዳው ላይ አርፏል፡፡ ከዚያ ባለፈ ቤት ውስጥ ሥዕል ተሰቅሏል፡፡ ቤቱ የጥበብ ቤት ነው:: ንባብ የሚወድድ ነዋሪ ያለበት ነው፡፡ ሙሉ መልኩ ሲታይ ምናልባት የራሱ የገብረክርስቶስ ሊሆን ይችላል፡፡ መጻሕፍቱ ጥቅማቸው ምን እንደሆነ ራሱ ገፀ ሰቡ በቀጣዮቹ ስንኞች ይነግረናል፡፡
መጠጊያ፤ መሸሸጊያ መደበቂያ
የሚጫወቱ፤         የሚያስተምሩ፤         የሚያነጋግሩ
አልጋ፣ ፍራሽ፣ ትራስ
የሚውጥ አልጋ፤
የሚያሳርፍ፤
መጻሕፍቱን እንደ መጠጊያ ይቆጥራቸዋል:: ብቻውን ሲሆን፤ የሃሳብ ዶፍ ሲያሳድደው፣ ወይም አንዳች ነገር እረፍት ሲነሳው፣ ወደዚያው ገብቶ ራሱን የሚያስጠጋ ገፀ ሰብ ይታየናል፡፡ በዚያ ብቻ አያበቃም፤ ይሸሸግበታል፤ መሸሸግ ደግሞ ከሚያሳድድ ብቻ ሳይሆን ለአደጋ ከሚጥል ነገርም ማምለጫ ነው፡፡ እንዳይገኝ ራሱን የሚያሰውረው በመጽሐፉ ነው፡፡ ይደበቅበታል፡፡
በዚያው ደግሞ ያጫውቱታል፣ ያሳስቁታል፣ ታሪክ ይነግሩታል፤ ሽንፈትና ድልን ይተርኩለታል፡፡ የቂሎችን ጨዋታ፣ የብልሆችን ቀጭን መንገድ፣ የሲዖልን ወለል ያለ በር፣ የጽድቅን ኮስታራ ሠፈር፣ እያዋዙ ይነግሩታል:: ከያዙት ቁምነገር እየተቆነጠሩ ወይም እየዛቁ፣ ያስተምሩታል፡፡ እገሌ እንዲህ ሆኖ ወደቀ፣ እገሌ እንዲያ ሆኖ ተነሳ፣ ከዚህኛው ይልቅ ያኛው ጥሩ አድርጓል፡፡ አንተም የሚሻልህ ይህኛው መንገድ ነው ወዘተ እያሉ ያስተምሩታል፤ያናግሩታል፡፡ ለዚህ ነው ከዳቦውም ከወተቱም ይልቅ እዚህም እዚያም ቤቱ ውስጥ መጻሕፍቱን ያኖራቸው፡፡
ወደ ፍፃሜው የሚወስደው… ከዚህ ሁሉ ጣጣ ዘወትር የሚያደርገው ደግሞ አልጋው ነው፡፡ አልጋው የሽቦ አልጋ እንደሆነ ያስታውቃል - “የሚውጥ አልጋ” ብሎታል፡፡ የረገበ አልጋ መሆኑ ነው፡፡ ቢሆንም ያሳርፋል፤ ትን እንዳይለው፤ ቀና አድርጐ የሚያመቻቸው ትራስም አለ፡፡ ከዚህ ዓለም ጣጣ የተወሰኑ ሰዓታት ወስዶ፣ ሌላ ሀገር አቆይቶ የሚመልስ… እንቅልፍ የሚባል ሌላ ሀገር አለ፡፡ እዚያ መሄጃ ባቡሩ አውሮፕላኑ፣ ወይም መኪናው ነው፡፡
እንዲሁም ሌላ፤
እንዲሁም ብዙ፣
ብዙም ሌላ
ያድናናሉ፡፡
ከአልጋው ባሻገር ሌላም ብ0ዙ ነገሮች አሉ - ይለናል፡፡ ምናልባት ሲጋራ፣ መጠጥ የመሳሰሉት ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ መጽናኛ ናቸው እያለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚተርከውን ገፀ-ሰብ አንዳች ሀዘን ያለ ማረፍ፣ ብክንክንነት ያናወጠው እንደሆነ እንረዳለን፡፡ መጽናናት የሚያሻው ላዘነ ሰው ነው፡፡ ትግል፣ ፍልሚያ… ላለበት ህይወት ነው፡፡ ደግሞም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ቤቱ ብትንትን ባለ ቁሳቁስ የተሞላው… ሃሳቡ የተበታተነ ስለሆነ አይደል? ስንኞቹስ ብትንትናቸው ለምን ወጣ? ከተበታተነ ልብ… የህይወት ሞገድ ሜዳ ላይ ላይ ስለረጫቸው መሆኑን እንዴት እንጠረጥራለን፡፡ ያው እስኪሰበሰብ የመጨረሻው ሽልብታ ውስጥ እስኪገባ እንደዚያው ነው፡፡ የገብረክርስቶስም ወሬ ይኸው ነው፡፡   

Read 1931 times