Saturday, 12 October 2019 12:22

አዳምና ቃየን

Written by  ከመሐመድ ነስሩ (ሶፎንስያስ አቢስ) “ጥቁር ሽታ” የአጭር ልብወለድ መድበል የተወሰደ)
Rate this item
(4 votes)

“ሔዋን…ሔዋን”
እንደ እባብ ወደ ጐጆው ውስጥ እየተሳበ ይጣራል፡፡
ሀሳብ ጓዙን ጠቅልሎ፣ ግሳንግሱን በእጁ አንጠልጥሎ፤ ልቡ ውስጥ ውሎ ማደር ጀምሯል:: ሀሳቡ ምክንያት አልባ አልነበረም፡፡ ልጆቹ ከእናታቸው ጋር በፍቅር ሲተሻሹ አየ፡፡ ሚስቱ ልጆቿን እያገላበጠች ስትስም (ልክ እሱ መጀመሪያ እሷን ሲስማት እንደሆነው ልቧ ጥፍት እስኪል ስትስም) እንክብካቤም ስታበዛባቸው (እግዜር እሱ የኤደን አትክልት ቦታን እንዲንከባከብ ያሰበውን ያህል ስትንከባከብ) ስታሞላቅቅ ስታቀብጣቸው (እነሱ በተከፉ ቅጽበት ዓለም ድምጥማጧ የሚጠፋ እስኪመስል ስታቀብጣቸው) ቢመለከት ልጅ የመሆን ሃሳብ እንደ ወባ ትንኝ አንዴ ወግቶት ተውሳኩን ትቶበት ሄደ፡፡
አወቀ፡፡ ከሁሉም በላይ የሆነ በደል መበደሉን ተረዳ፡፡ ለካ አባት የለውም፡፡ ለካ እናት የለውም፡፡
አዳም ሆድ ባሰው፡፡ እንባው መጣበት:: ህፃን አልሆነም፡፡ ህፃንነትን ዘሎ ሰው ሆነ፡፡ በእናቱ ጭን ላይ የራስ ቅሉን አሳርፎ፣ በደረቷ ላይ በትናንሽ ብርሃንማ እጆቹ የሰኞ ማክሰኞ መጫወቻ የሚያሰምረውን ልጅን ቃየንን አየው:: ልጇን በስስት እያየች አስሬ ግንባሩን እንደ ቤተ አምልኮ የምትስመውን ሚስቱን ሔዋንን አያት:: የማያውቀው ልጅነት ናፈቀው፡፡ ጤግሮስ ወንዝ በውሃ እንደሚሞላ ዐይኑ በእንባ ተሞላ፡፡
“ምን ሆነሃል?” አለችው ሔዋን
ዝም፡፡
“አዴክስ ምንድን ነው እሱ?!”
የማልቀስ ነፃነቱን ያጣው ህፃን ባለመሆኑ እንደሆነ ሲረዳ፣ ንዴት ውስጡ ተቀጣጠለ፡፡
ድንጋይ እንደተወረወረበት ወፍ አፈፍ ብሎ ወደ ውጭ በረረ፡፡
“ሔዋን” ሌላ ጥሪ፡፡
መልስ አልሰጠችውም፡፡
ጭንቀቱን ሊያዋያት ፈልጐ ነበር፡፡
ጠፋች፡፡
ቃየን እጁን አፋትጐ፣ ጭቃውን እያራገፈ ገባ፡፡
አዳምም አለው፡-
“እናትህስ?”
“ወንዝ ወርዳለች”
“የት?”
“ኤፍራጥስ”
አዳም ፍለጋዋን ሊወጣ ሲል፣ ሔዋን ከሄደችበት ተመልሳ መጥታ ፊቱ ተገተረች፡፡
“አዳምዬ!”
ሲያያት እንደ መደንገጥም! እንደ መደሰትም፣ እንደ መናደድም አለ፡፡ ራቆቷን ነበረች፡፡ የጭንና ጭኗ መጋጠሚያ ግድም ቅጠል አገልድማለች፤ እንደ ብስል ፓፓያ ለመብላት የምታጓጓ፣ እንደ አመሻሽ ወርቃማ ጀንበር እንዳትወድቅ የምትሳሳ ሆናለች፡፡
አላት፡-
“የት ነበርሽ?”
ዐይኑ እሳት እየተፋ፤ ድምፁ ማዕበል ሆኖ እየተናወጠ፤ ዙሪያ ገባውን እየናጠ፡፡
“ሰውነቴን ልታጠብ ወንዝ ወርጄ ነበር”
የበረዳት ትመስላለች፤ እንደ ሐዋላ ወርቅ ንፁህ በሆኑት እጆቿ፣ እንደ ጨረቃ ብርሃን ተቀብሎ ብርሃን የሚረጭ ገላዋን ታሻሽለች፡፡
“ታዲያ ራቆት መሆን ደግ ነውን?! እግዜአብሔር ከቆዳ የሰራልሽን ልብስሽን አትለብሺም?!”
ሔዋን የትዝብት ሳቅ ስትስቅ አያት፡፡
“ምን ያስገለፍጥሻል?!”
እንደ ኪሩቤል ሰይፍ አስበርጋጊነትን ተላበሰ::
“ያለነው የሰው ዘሮች እኔ፣ አንተና ልጆቻችን ብቻ ነን፤ ማን ያይብኛል ብለህ ነው?!”
“ሰይጣንስ ቢሆን?! መላዕክትስ ቢሆኑ?! ዕፅዋትስ ቢሆኑ?! ተራሮችና ሸለቆዎችስ ቢሆኑ ለምን ያዩሻል?!ኧረ ልጆቻችንስ ቢሆኑ?!! ባንቺ ማንን አምናለሁ?! ለራስሽ አንዲት ብቻ! ደግሞ ማን ያየኛል ብሎ ነገር!”
“ሆ…ሆ…ሆ…” ተሽኮረመመች፡፡
ሔዋን ደስ አላት፡፡ ገመዳም ሳቅ አሳየችው፤ አዳም ተጐተተ፡፡ ወፍራም ምራቅ ዋጠ፡፡
ከምራቁ ጋር ሃሳቡን ዋጠ፡፡ (ሊነግራት የነበረውን ረሳ) ወደ ቃየን ዞር ብሎ አለው፤
“በል ሂድና በሬዎቹን አስገባ”
- ሀ -
አቤል ከተወለደ እጅግ ቆየ፡፡ ቃየን እናትና አባቱ ጋር የነበረውን ተወዳጅነት ከአቤል መወለድ በኋላ ካለው ጋር ማነፃፀር የጀመረው ግን በቅርብ ነው፡፡ እንደ ቤተሰባቸውና እንደ እግዜር ህላዌ እጅግ የተራራቀ ሆኖ አገኘው፡፡ የተፈጠረበት የስሜት ለውጥም ሔዋን ልጃገረድ ሳለችና ከአዳም ጋር ከወደቀች ወዲህ ካሳየችው የማንነት አካላዊ ለውጥ ጋር የሚገዳደር ነበር፡፡ ሔዋን ከለግላጋነት ወደ እናትነት ተሻግራለች፡፡ ቃየንም ከደስተኝነት ወደ ፀለምተኝነት ተዛወረ::
ያኔ እንደ ንጋት ጮራ ፀሐይ በሚሞቁ፣ እንደ በለስ ቅጠል በሚለሰልሱ የሔዋን ክንዶች የሚታቀፈው እሱ ብቻ ነበር፡፡ (አዳም የኔ ነው ሲል ሰምቶት አያውቅም!)
ያኔ…እናቱ የሱ፣ የግሉ፣ የብቻው ነበረች፡፡
ያኔ…አባቱ የሱ፣ የግሉ የብቻው ነበር፡፡
እናትና አባቱ ከላይ እንደወረደ መና ይሻሙበታል፡፡ እንደ መንግስተ ሰማይ ተስፋ የደስታቸው ምንጭ የነበረው እሱ ነው፡፡ እሱ ብቻውን!
ሁለተኛው ልጅ መጣ፡፡ ቃየን ብርቅነቱ አለቀ፡፡ እንደ መልዓኩ ሳጥናዔል ማዕረጉን ተነጠቀ፡፡ የተፋለሙበት የጦር አውድ ሳይከሰት ወንድሙ የበላይነትን ወርሶ የድል አክሊል ተቀዳጀ፡፡ የፍቅር ዘውድ ጫነ፡፡
- 2 –
አዳም ወንድነቱን ካለዘበ በኋላ ከሔዋን ወጥቶ በሃሳብ እቅፍ ውስጥ ወደቀ፡፡ ልጁን ማባረሩ ተሰምቶት አይደለም፡፡ ሚስቴን አላስደሰትኳትም የሚል ስጋት አድሮበት አይደለም፡፡ ሚስትና ልጆች ብቻ እንዳሉት ትዝ ብሎት ነው፡፡
የልጅነትን ውብ፣ ማራኪ ጨዋታዎች አልተጫወተም፤ ቅል ቅቤ ተቀብቶ እንደሚብለጨለጭ …የሱ ፊት የልጅነት ወዝ ተቀብቶ አልተብለጨለጨም፤ እንደ ኤደን ሰማይ አልፈካም፡፡ እንደ ሐዋላ ሽቶ ውድ የሆነውን የህፃን አልባብ ሽታ ሰውነቱ አመንጭቶ አያውቅም፡፡
በህፃን ከንፈሩ የእናቱን ጡት አልጠባም፤ የአባት ፍቅር አላገኘም፡፡
እንደ የዓለም ጅማሮዎቹ አምስት ቀናት ሳይኖረው ባለፈውና እንደ ምጽዓት ቀን በማያውቀው ልጅነት ናፍቆት ተሰቃየ፡፡ እንደ እግዜር ባላያቸው፤ እንደ ነብያት ባልተፈጠሩት እናትና አባቱ ፍቅር ትዝታ ተንገበገበ፡፡ ብልሀቷን ያውቃልና ጭንቀቱን ለሚስቱ ሊያካፍል አሰበ፡፡
“ሔዋኔ” አላት፡፡
“ወ…ዬ”
ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ዝምታ አፉ ላይ ተከመረ፡፡ በዝምታው ውስጥ ብቅ ያለው ሀሳብ አስደነገጠው፡፡ ስነግራት እሷም ተመሳሳይ ቅሬታ ብታሰማስ? የባሰ ሕይወት ልትጨልምብን አይደለም?!
“ም…ነ…ው?” አለችው፡፡
የመጀመሪያ ሀሳቡን ደመሰሰና “በጣም እወድሻለሁ” ብሎ ወደሷ ዞረ፡፡
“ይህን ቃል ካንተ እኩል እንደምወደው ታውቃለህ መቼም!” ቃሉን ያሰማትን አፉን በአፏ ገጨችው፡፡
ቃየን ገበሬ ነበር፣ እንደ ገበሬነቱ ካመረተው ሰብል መስዋዕት አቀረበ፡፡ አቤል እረኛ ነበር፤ እንደ እረኛነቱ ከሚጠብቃቸው በጐች አንድ ጠቦት ሰዋ፡፡ የአቤል መስዋዕት እግዜርን ደስ አሰኘ፤ ሞገስም አሰጠው፡፡ የቃየል መስዋዕት ግን አስከፋው፡፡ የአዳም የበኩር ልጅ ባሰበት፡፡ አቤል ከእናቱና አባቱ አልፎ በእግዜሩ ዘንድም ወንበር ተሻማው፡፡ በገነ፡፡
ከኋላ የመጣ…
እንደ ጥንቱ ሊሆን አልቻለም፡፡ እንዴት ሆኖ ሊሆን ይችላል?! አባቱን አሰበ፤ የመጀመሪያው ወንድ ነው፡፡ እናቱን አሰበ፤ የመጀመሪያዋ ሴት ናት፡፡ አባቱ የሁሉ አባት ነወ፡፡ እናቱ የሁሉ እናት ናት፡፡ መነሻ ነጥቦች፡-
ታናሽ ወንድሙን አሰበ፤ በፈጣሪ ዘንድ ሞገስን አግኝቷል፡፡ ባቀረበው መስዋዕት ፈጣሪውን ደስ አሰኝቷልና የታሪክ መዛግብት አይዘነጉትም፡፡
“ቆይ እኔስ?”
ራሱን አሰበ፡፡ ምንም እንደሆነ ተሰማው፡፡ በእንግዴ ልጅና በእሱ መካከል ያለው ልዩነት ጐልቶ አልታይህ አለው፡፡
የተጣለ ነው፤ በሁሉም የተረሳ ነው፡፡
“ለምን?!...ለምን?!”
ወደፊት የማይረሳ ሰው መሆን እንዳለበት ለራሱ ቃል ገባ፡፡ “የመጀመሪያው” በሚል ቃል ከሚጀምር ሀረግ ቀጥሎ ስሙ እንደሚሰፍር እርግጠኛ ሆነ፡፡
- 3 –
አዳም አላረፈም፡፡ ሰይጣን መልኩን እየለዋወጠ ወደ እሱና ወደ ባለቤቱ እንደተመላለሰ ሀሳብ ቅርፁን እየቀያየረ ወደ አዕምሮው ተመላለሰ፡፡
“ምን ባደርግ ይሻላል?!”
ይህ ጥያቄ በምናብ ተራራ አስወጣው፤ ወንዝ አስዋኘው፡፡ ምርጫ ስላልነበረው በመጨረሻ ለሚስቱ አማከረ፡፡
አለችው፡-
“ለምን ፈጣሪያችንን አትጠይቀውም?!”
“ይሻላል?”
“አዎ ጠይቀው፤ በሽታውን ያልተናገረ መድሀኒት አይገኝለትም፡፡”
ሔዋን ነፍስ ናት፤ አዳም አካል ነው፡፡ ጥንትም አሁንም እንዲሁ ነው፡፡ ስጋ እንደ ነፍስ ስለማይታይ አናያትም፡፡
አዳም ከሷ ውጭ ህልውና የለሽ መሆኑን ያውቃልና “እሺ”! አለ፡፡
ወደ እግዜርም ሄደ፡፡
“ምን ነበር?!”
“እናት የለኝም፤ አባት የለኝም!”
“ማን ነው እንዲህ ያለህ?”
“አየሁ፤ ተረዳሁ?! አወቅሁ”
“ጥንትም ማወቃችሁን ያልፈለኩት ለዚሁ ነበር” እግዜር አለ፡፡
“ለማንኛውም አለህ፡፡”
“እንዴት?! ከየት?!”
“አባትህ እኔ ነኝ፡፡”
“እናቴስ?”
“መሬት፡፡”
አዳም ዝም አለ፡፡ መልሱ በደንብ የተዋጠለት አይመስልም፤ ፈልጐ ከመጣው ነገር ጋር አልተዛመደለትም፡፡
ለማንኛውም ሁለተኛውን ጥያቄውን አቀረበ::
“ህፃን ሆኜ አልኖርኩም፤ ህፃንነትን ማየት እፈልግ ነበር!”
“ጥሩ!” አለ እግዜር፡-
“ትሆናለህ፡፡ ህፃንነትን ወደፊት ትኖረዋለህ፡፡”
አዳም እጅ ነስቶ ተመለሰ፡፡
ደስም፣ ቅርም እያለው፤ በግማሽ ደስታና በግማሽ መከፋት ታጅቦ ወደ ቤቱ አዘገመ፡፡
- ሐ -
የመጨቆን ስሜትና የመጀመሪያው ገዳይ የመሰኘት ምኞት በቃየን ልብ ውስጥ እንደ ሔዋን ጡቶች መንታ ሆነው በቀሉ፡፡ ወደ ማዕድ ቤት ገብቶ የሔዋንን ሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ ድጉ ውስጥ ከሻጠ በኋላ ወንድሙን አለው፡-
“ና ወጣ ብለን አየር እንቀበል!”
ወጡም፡፡
- 4 -
አዳም ቤት ሲደርስ፤ ሔዋን እንባዋን እየዘራች ነበር- የሰማይ ውሃ ቧንቧዎች የተከፈቱ እስኪመስለው!
“ምንድን ነው?”
“ጉድ ሆንኩልህ አዳምዬ! ጉድ ሆንኩልህ!”
“እኮ ምን ሆንሽ?” እያቀፋት አላት፡፡
“ጉድ! ጉድ!”
“ኧረ ንገሪኝ ምንድነው?”
“ጉድኮ ነው…ጉድ! ጉድ!”
ግራ ገብቶት ወገቡን ይዞ መንጐራደድ ጀመረ፡፡ ዐይኑን ወዲያ ወዲህ እየጣለ ተሽከረከረ:: ድንገት ዐይኑ ቃየን ላይ ወደቀ፡፡ ደረቱን ነፍቶ በርጩማ ላይ ቁጭ ብሏል፡፡
“ልጄ፤ እናትህ ምንድነው የሆነችው?”
“እኔ እንጃ!”
“ወንድምህስ የት አለ?”
“እኔ ገበሬ እንጂ እረኛ ነኝን?!”
ወደ ሔዋን ተመለከተ፤ ወደ ቃየን ተመለከተ:: ምክንያቱ ገባው፡፡ አቤል በአየር ፋንታ ሞት ተቀብሏል፡፡ አዳም በቆመበት እንደ ድንጋይ ደርቆ ቀረ፡፡
- 5 –
ከቀናት በኋላ ሀዘን ተቀምጠው ሳለ፣ ከሀዘኗ ሊያዘናጋት ሽቶ፤
“ህፃናንነትን ትኖረዋለህ ተባልኩኮ”
አላት፡፡
“እንዴት?”
“ለፈጣሪ ፍላጐቴን ስነግረው ወደ ፊት እንደምኖረው ቃል ገባልኝ፡፡”
ሔዋን እንደ ራሷ ፀጉር የረዘመ ሃሳብ፣ ረጅም ጉዞ አስጓዛት፡፡
“ይኸ ነገር?” አለችው፡፡
“የቱ?”
“ይኼ ህፃን የመሆን ነገር!”
“እ?”
“ከእርጅና በኋላ የሚመጣ ሳይሆን አይቀርም፡፡”
“ማለት?”
“ሌላ ስሙ መጃጀት መሆን አለበት፡፡ ቃል ከተገባልህ ህፃን የምትሆነው ስትጃጅ መሆን አለበት፡፡”
“እኔ ምን አውቄ?” አለ አዳም - በዐይኑ ዐይኗን እየተመለከተ፤ በልቡ በብልሃቷና በጥበቧ ረቂቅነት እየተደነቀ፤ በስሜቱ እሷን የሰጠውን ፈጣሪ እየወደደ፡፡

Read 1857 times