Saturday, 12 October 2019 12:23

“ኤልያስ ራሱን በተግባር ያስተማረ ጎበዝ ልጅ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ለ30 ዓመታት አስተምሬያለሁ፡፡ ኤልያስም አንዱ ተማሪዬ ነበር፡፡ እንደ ማንኛውም ተማሪ ነበር እኔ ጋ የተመደበው፡፡ ያስተማርኩት ቼሎ የሚባለውን ባለ አራት ክር መሳሪያ ነበር:: ቼሎ ደግሞ ለመማር ፆታ አይለይም፡፡ በሳምንት ሦስት ቀናት ክላስ ነበረው - ሰኞ፣ ረቡዕና አርብ፤ ለአንድ አንድ ሰዓት ማለት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በ80ዎቹ መጨረሻ ይመስለኛል፡፡ ለአራት አመት በት/ቤቱ ውስጥ ሲቆይ ጐበዝ ተማሪ መሆኑን አስተውያለሁ:: የኤልያስ ሜጀር ቼሎ በመሆኑ በመደበኛ ትምህርቱ ነበር የማገኘው፤ ነገር ግን ማይነር ላይ ፒያኖና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን የተማረ ይመስለኛል፡፡ እንዳስተዋልኩት ትልቅ የሙዚቃ ፍቅርና ስሜት ነበረው:: በዚያን ወቅት “ይህ ልጅ ትልቅ ቦታ ይደርሳል” ብዬ አስብ ነበር፤ እንዳልኩት ነው የሆነው፡፡ በሥነ ምግባርም ቢሆን ምንም እንከን አልነበረበትም፡፡ ትምህርቱን፣ መምህራኑንና  ጓደኞቹን ያከብራል:: የሙዚቃ ስሜትና ፍቅር ስለነበረው የምንሰጠውን ይቀበላል:: እኔ ኤልያስን ጊታር አላስተማርኩትም፤ አሬንጅመንትም ሆነ ኦርኬስትሬሽን አላስተማርኩትም፡፡ ግን ከላይ የገለጽኳቸውን ተክኖባቸው ነው ያገኘሁት፡፡ ይህን ያመጣው ደግሞ የሙዚቃ ፍላጐቱና ጥረቱ ነው፡፡
ከት/ቤቱ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ተገናኝተን አናውቅም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስንገናኝ እንኳን በርቀት ነበር ሰላምታ የምንለዋወጠው:: ሙዚቃው ላይ ብቻ ደፋ ቀና ስለሚል የትም ቦታ አይገኝም፡፡ እዚያው ስቱዲዮው ከትሞ ነው ይህን ሁሉ ተዓምር ሲሰራ የኖረው፡፡ በመንግስት ቤት ተቀጥሮ መስራት አይፈልግም ነበር፡፡ ብዙ ያስተማርኳቸው ልጆች፣ የተለያዩ ቦታዎች ተቀጥረው ሲሰሩ እመለከታለሁ፡፡ እንደ ኤልያስ መልካ ያሉት ደግሞ በራሳቸው ጥረትና አቅም አንቱ ለመባል ችለዋል፡፡ በጣም ጐበዝ ልጅ ነበር:: ብዙ በመስሪያው ጊዜ ነው ያጣነው:: ስራዎቹን ከወጣት እስከ አንጋፋ አዳምጥ ነበር፡፡
ሙዚቃዎቹ ስሜት አላቸው፣ ህይወት አላቸው፡፡ ስራዎቹ የተለዩ ናቸው፡፡ ከማንም የሚገጥሙና የሚመሳሰሉም የሚሰለቹም አይደሉም፡፡ ሌላው ይቅርና ኤልያስ በግጥም ደረጃ እንዲህ ያለውን ልህቀት ከየት አመጣው ብዬ ይግረመኛል፡፡ ሃሳቡን ከየት ነው የሚያመነጨው? እያልኩ እገረማለሁ:: እንደሱ ያሉትን ሳይተካ ሄደ ይሆን እያልኩ እቆጫለሁ:: ቢሆንም የሰራውም ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ ዕድሜው በማለፉ የተሰማኝ ሀዘን ከባድ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሙዚቃም ጉድለት ነው፡፡ ነፍሱን ይማር፡፡ ለቤተሰቡ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለአድናቂዎቹ በሙሉ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

Read 1024 times