Saturday, 12 October 2019 12:31

“የተቀዛቀዘውን ሙዚቃ ያነቃቃና በአዲስ ስልት የታደገ ነው”

Written by  (ሙሉ ገበየሁ፤ የሙዚቃ ባለሙያ)
Rate this item
(2 votes)


              ከኤልያስ ጋር ያለን ቅርበትና ዝምድና እንዳለ ሆኖ ኤልያስ ማን ነበር? ለሙዚቃው ያበረከተው አስተዋጽኦ ምንድን ነው? የሚለውን ስንመለከትና በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ በመኖሩ አበርክቶው ምን ያህል ነው? የሚለውን ስናስብ፣ ለዘርፉ አዲስ ስሜት በመፍጠር፣ ተቀዛቅዞ የነበረውን ሙዚቃ አነቃቅቷል::  ምናልባትም ከ90ዎቹ በፊት ተደጋጋሚ የሙዚቃ ስታይሎችና ሥልቶች አሰልቺ የነበሩበትን ሁኔታና የሰውንም ጥያቄ በመለወጥ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻገረ፣ ለሙዚቃ አዲስ ጣዕም የሰጠ ልጅ ነበር - ኤልያስ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ በኖረባቸው ጥቂት አመታት ደግም በጣም በርካታ ሥራ በመስራት አርአያ መሆን የቻለ ፈርጥ ነበር፡፡ ለብዙ ታዳጊ ለሆኑ ልጆች መድረክ በመፍጠር እንጀራ ያበላ፣ ለሙያውና ለሙያተኛው የመብት ተከራካሪ በመሆንም፣ ሙያተኛው ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ የተለመና ጫፍ ያደረሰ ሲሆን፤ እውቀቱንም፣ ጊዜውንም፣ ጉልበቱንም ሳይሰስት፣ አንጠፍጥፎ የሰጠ ድንቅ ባለሙያ ነው፡፡ እናም ኤልያስን ከዕድሜው አንፃር ስንመዝነው፣ አበርክቶው ከዕድሜው የገዘፈ ነው፡፡ ዋጋና ትርጉም የሚሰጠው ስራ ሰርቶ፣ የሙያ ፍቅርን አሳይቶ፣ ለተከታዮቹ አርአያ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡
ኤልያስ በሙያው ያበረከተው አስተዋጽኦ፣ ያደረገው እንቅስቃሴ ብዙ ሙያተኞችን ፈጥሯል:: ብዙ ወጣት ሙዚቀኞች በኤልያስ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ኤልያስ ለሌሎች መንገድ ጠርጓል፤ አቅጣጫ አሳይቷል፤ብዙዎችን መስመር አስይዟል፡፡ ስለዚህ ተተኪ አፍርቷል ማለት ነው፡፡ ልብ ያለው ሙያተኛ፣ ፈለጉን ተከትሎ፣ የእሱን መንገድ መያዝ አለበት፡፡ እነ ቴዲ አፍሮ፣ እነ ዘሪቱ፣ እነ ሃይሌ ሩትስና ሌሎችም አሁን በሙያቸው አንቱ የተባሉ አርቲስቶች፣ ገንነው የወጡት በእርሱ ሥራ ነው፡፡ በሱ አዲስ መስመር ነው ሳይሰለቹ እየተደመጡ የዘለቁት፡፡ ወደፊትም መደመጣቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ኤልያስ ሥራው ይሄው ነው፡፡ ብልህ ሰዎች የእሱን ፈለግ ከተከተሉ፣ ኤልያስ ብዙዎቹን ተክቷል:: እስከ ዛሬ የሰራቸው ስራዎች፣ የፈጠራቸው አዳዲስ ስልቶች በራሳቸው ት/ቤቶች ናቸው፡፡ ተወዳጅ ናቸው፤ ዘመን ተሻጋሪ ናቸው፤ ሰውን ከመሰልቸት ያወጡና ጣዕም የሰጡ ናቸው፡፡ የሙዚቃውን ደረጃም ከፍ ያደረጉ ናቸው፡፡  
ኤልያስ በዚህ ዕድሜው ህይወቱ ማለፉ ትልቅ ኪሳራ ነው፤ ምክንያቱም ኢንዱስትሪው የሚፈልገውና በሙያው የተካነ ሰው ነበር፡፡ ይህ የኪነ ጥበብ ሰው ከኢንዱስትሪው ሲጐድልና ሲጠፋ፣ ኢንዱስትሪው ላይ ክፍተት መፈጠሩ ግልጽ ነው፡፡ ኤልያስ በህይወት ቢኖር፣ እስከ ዛሬ የሰራቸውን የሚገመግምበት፣ ወደፊት የሚሰራቸውን ደግሞ የሚያሰላስልበትና ይበልጥ የሚበስልበት እንዲሁም የሚያፈራበት ጊዜ ላይ ነበር፡፡
ሆኖም ፈጣሪ አልፈቀደም፡፡ ምን ይደረጋል፡፡ ይበልጥ ሊሰራ በሚችልበት ጊዜ፣ በአጭር ተቀጬ ነው የምለው፡፡ የሙያ አጋሮቹ፣ የእሱን አሻራ ተከትለው፣ ከእርሱ ትምህርት እንዲቀስሙ አደራ እላለሁ፡፡  ለቤተሰቡ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለመላው ህዝብ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡ ነፍሱን በደጋጐቹ ጐን ያሳርፍልን!

Read 1339 times