Saturday, 19 October 2019 12:23

የፖለቲካ ድርጅቶች በህወኃት መግለጫ ላይ የተለያየ አቋም ይዘዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት መግለጫውን አጣጥሎታል

              የህወኃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ያደረገውን ምክክር አስመልክቶ ባወጣውና የኢህአዴግና አጋሮቹን ውህደት በተቃወመበት መግለጫ ዙሪያ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የተለያየ አቋም ያንፀባረቁ ሲሆን የጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ መግለጫውን አጣጥሎታል፡፡
 ለውጡ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በራሱና በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣበትን ጥቃት በመመከት ስራ ላይ መቆየቱንና ውጤታማ በሆነ መልኩ መመከቱን በመግለጫው ያመለከተው ህወሃት፤
‹‹በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እየተበራከቱ፣ ጥፋት በጥፋት ላይ እየተደራረበ፣ የጥፋቱ ስፋትና መጠን በየቀኑ እየጨመረ ወደ ከፋ የአገር መበተን ደረጃ እየደረሰ ነው ብሏል፡፡ የመበተን አደጋውን ወደ ከፋ ደረጃ እያደረሰው ያለው አንዱ ምክንያት በችኮላ የፓርቲ ውህደትን ለመፈፀም የሚደረግ ጥረት ነው›› ሲል ተችቷል፡፡
ውህደቱም በስልጣን ላይ ያለውን የፖለቲካ ድርጅት ህጋዊነት የሚያሳጣ ነው ያለው ህወኃት፣ በዚህ መንገድ የሚመሠረተው ድርጅትም ህገወጥ ነው›› በማለት ከወዲሁ የኢህአዴግንና አጋሮቹን ውህደት በመግለጫው ተቃውሞታል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ‹‹በህወሓት የወጣው መግለጫ ለውጡ ከመጣለት ሳይሆን ከመጣበት፣ ህዝብን ከማይወክል አካል የወጣ ነው›› ሲል መግለጫውን አጣጥሎታል፡፡
“መግለጫውን ያወጣው ቡድን ህብረተሰብ የማይወክል፣ መብትን የሚያፍን፣ ራሱ የወጣበትን ህዝብ ፍላጐት እያፈነ፣ ህዝቡ ወደ አደባባይ ወጥቶ ፍላጐቱን እንዳይገልጽ እየገታ ያለ ቡድንና ስርአት ነው” ብሏል - ጽ/ቤቱ፡፡
መግለጫውን ያወጣው በለውጡ ምክንያት ጥቅም የተቋረጠበት አካል መሆኑን ያወሱት የጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ ንጉሡ ጥላሁን፣ ይህ አካል የቀድሞው አሰቃቂ ግፍ እንዲመለስ ምኞት እንዳለውም አመላካች ነው ያሉት ሃላፊው፤ የታሰበው የኢህአዴግ ውህደት እንደማይስተጓጐል አክለው ገልፀዋል፡፡
“የህወሓት መግለጫ ከለውጡ በተፃራሪ የቆሙ ወገኖችን አቋም ያንፀባረቀ ነው” ያሉት አቶ ንጉሱ፣ ‹‹ሀገሪቱ በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፈች ብትሆንም አንድ ሆና ጠንክራ ለመሄድ አሁን የመጨረሻውን ምዕራፍ ይዛለች፤ የህወኃት መግለጫም አጠቃላይ ይዘቱ ከለውጡ በተፃራሪ ያሉ ሃሳቦችን ያንፀባረቀ ነው›› ሲሉ ተችተዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የነበረው ስርአት በስመ ፌደራሊዝም የተቀመጠ ነገር ግን አሃዳዊ ባህሪ የነበረው መሆኑን ያወሱት የጽ/ቤቱ ሃላፊ፤ ‹‹ይሄ ስርአት እንዲስተካከል የተደረገው ትግል ዛሬ ፍሬ እያፈራ ነው›› ብለዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ሁሉም ክልሎች ከዚህ በፊት እንደነበረው ማንም በሞግዚትነት ሊያስተዳድራቸው አይችልም፤ በሴራ እየከፋፈለ ሃብታቸውን አሟጦ የሚወስድ ሃይል የለም፤ ለእያንዳንዱ ክልል የጡት አባት ሆኖ የመግባባት ሁኔታ ቆሟል፡፡ ይሄ በመቆሙ ጥቅማቸው የተነካ አካላት ግን ተረብሸዋል›› በማለት አብራርተዋል አቶ ንጉሡ::
ከጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ይህን መሰል ተቃውሞ በቀረበበት የህወኃት መግለጫ ላይ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችም ለአዲስ አድማስ የየራሳቸውን ሃሳብ ያጋሩ ሲሆን የተለያዩ አቋሞችን አንፀባርቀዋል፡፡
የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፤ ‹‹መግለጫው በስልጣንና ስልጣንን መያዝ በሚያስገኘው ጥቅም ላይ ብቻ ካተኮረ ድርጅት የተሰጠ በመሆኑ ብዙም አይደንቅም›› ብለዋል፡፡
“ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን የበላይነት ሲያጣ ወደዚህ አቅጣጫ ሊሄድ ይችል እንደነበር ግልጽ ነው›› ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፣ ‹‹ይህ መግለጫ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ አደገኛ አዝማሚያ ያለው፤ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት የሌለውና የሚኮነን ነው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የህወኃት አቋም ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው የቀቢፀ ተስፋ ህልም መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አረጋዊ፣ የትግራይ ህዝብ በነፃነት ቢጠየቅ እንደማይቀበለው ግልጽ ነው ብለዋል፡፡
የአረና ትግራይ ም/ሊቀመንበር አቶ ጐይቶም ፀጋዬ በበኩላቸው ህወኃት ውህደቱን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ የራሱ የውስጥ ጉዳይ እንጂ የትግራይን ህዝብ የሚመለከት አለመሆኑን አስገንዝበው፤የሚሻላቸውን እነሱ ናቸው የሚያውቁት ብለዋል፡፡
ህወሓት በአጠቃላይ እየሄደበት ያለው መንገድ የማያዋጣ ነው ያሉ አቶ ጐይቶም፤ ‹‹በዚህ እንቅስቃሴ ግን ህወኃት እንዳስፈራራው ግን ሀገሪቱ ትበተናለች የሚል እምነት የለኝም›› ብለዋል - የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ጽኑ መሆኑን በመግለጽ፡፡
‹‹በትግራይ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ የተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ የማይቻልበት፣ አማራጭ ሚዲያ የሌለበትና አፋኝ ስርአት የሰፈነበት ነው፡፡
ህወኃትም ይሄን አፈና በማስፈራራትና ህዝብን ከህዝብ በማራራቅ የበለጠ ለማስቀጠል ማቀዱን መግለጫው ያመላክታል ነው›› ብለዋል አቶ ጐይቶም፡፡
በቅርቡ የተመሰረተው ‹‹ባይቶና›› ፓርቲ አመራር አባል የሆኑት አቶ ክብሮም በበኩላቸው ህወኃት ውህደቱን አለመቀበሉ ተገቢ መሆኑንና ያወጣው መግለጫም ከሞላ ጐደል የሚያስማማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ወቅታዊው የትግራይ ፖለቲካም በትግራይ ህዝብ መካከል አንድነትን እየፈጠረ ያለና ተበታትኖ የነበረን ሃይል እየሰበሰበ ያለ ጠንካራ ፖለቲካ አካሄድ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ክብሮም አስረድተዋል፡፡

Read 8193 times