Saturday, 19 October 2019 12:22

‹‹እናትሽን አትውደጅ ለዘጠኝ ወር ዕድሜ ተሸክሜሻለሁ እስከ ዘላለሜ››

Written by 
Rate this item
(10 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ዕብድና አንድ ለማኝ በጓደኝነት ይኖሩ ነበር፡፡ መተሳሰባቸው፣ መተጋገዛቸው እጅግ ያስቀና ነበር፡፡
መሀላቸው፣ ‹‹አደራ እንዳንከዳዳ›› የሚል ነበር፡፡
ሰንብቶ ሰንብቶ ለማኙ በብርድ በሽታ ታሞ ሞተ፡፡ ዕብዱ የለማኙን አስከሬን በሰሌን ጠቅልሎ ወደ መቃብር ቦታው ይዞት ሄደ። እንዳጋጣሚ ወደ አሥራ ስድስት የሚጠጉ የሸዋ መኳንንት በመኪና የመገልበጥ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ያ ዕብድ ለለማኙ እንዲህ አለው ሲሰናበተው፡-
‹‹እንግዲህ ወዳጄ ከደህና ሰዎች አገናኝቼሃለሁ፤ ብታውቅ እወቅበት›› ብሎ አስቀምጦት ሄደ፡፡
* * *
የአዕምሮ ጤና የጎደለው ሰው መላ ነገሩን እስከሚያስተካክል ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ የተማረም የተማረውን እስኪተገብር ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ ያልተማረውም የተማረው ቦታ ለመድረስ ጊዜ ይፈጃል፡፡ አገር የተማረውን ቦታ ለመስጠትና ያልተማረውን ለማስተማር ትጨናነቃለች፡፡ መሯሯጥ ይጠበቅባታል። ሼክስፒር በፀጋዬ አንደበት፡-
‹‹…በምናውቀው ስንሰቃይ
    የማናውቀውንም ፈርተን በህሊናችን ማቅማማት
    ወኔያችንንም ተሰልበን
    ሕይወት የምንለው ውጥንቅጥ እንቅልፍ ላይ ነው ህመሙ
በየዕለቱ መስለምለሙ
እያደር ከህሊናችን ይደመሰሳል ትርጉሙ!
የዱሮ ፀሐፍት፤
‹‹እኛማ ብለናል
እኛማ ታግለናል
እኛማ አምፀናል
ጥንትም ወርቅ በእሳት
እኛም በትግላችን
እየተፈተንን እናቸንፋለን››
ለዘመን መልካም ምኞትና፣ መልካም ምስክርነት  መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ህልውናችን የተሰራው ከመልካምነታችን ልቡና መሆን አለበት፡፡ መንገዳችን ቀና የሚሆነው በዚህ ጎዳና ብቻ ነው፡፡
‹‹እንጫወት እንጂ
እንጫወት በጣም
ከእንግዲህ ልጅነት
ተመልሶ አይመጣም፡፡
(ከዱሮ ማስታወሻ)
ከፀጋዬ ጋር ስናስብ ደግሞ (ለኢትዮጵያ ይበለው አይበለው ባናውቅም፤
‹‹አልወድሽም ያልኩት ውሸቴ ውሸቴ
ሳይሽ እርር ኩምትር ይላል ሆድ አንጀቴ››
ኢትዮጵያን ከአንጀቱ የሚወድ ኢትዮጵያዊ፤
‹‹እናትሽን አትውደጅ ለዘጠኝ ወር ዕድሜ
ተሸክሜሻለሁ እስከ ዘላለሜ››
ቢል… አይገርምምና፣ ለሁላችንም እንደዚያው - መልካም አዲስ ዘመን!

Read 10136 times