Print this page
Saturday, 19 October 2019 12:32

የኖቤል ሽልማት ታሪክ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በአስራ ዘጠነኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ላይ አሜሪካ መልክዓ-ምድሯን የሚከፋፍሉትን ተራሮች ቦርቡራ፣ ህዝቦቿን በመንገድ በማገናኘት ወደ አንድነት ለማምጣት ፈለገች:: ችግሩ እነዚህን የአለት ተራራ ግርዶሾች ለመቦርቦር ወይም ለመናድ ይውል የነበረው በፍንዳታ ከፍተኛ ሃይል ማመንጨት የሚችለው ናይትሮግሊስሪን የተባለ ፈሻሽ ፈንጅ ነበረ፡፡ ይህ ፈሳሽ ውሁድ እጅግ ያልተረጋጋና በድንገተኛ ቅጽበታዊ እንቅስቃሴ ፈንድቶ ከፍተኛ አደጋ ማድረስ የሚችል ፈንጅ ነው፡፡
ናይትሮግሊስሪን በመቶዎች የሚቆጠሩ የቁፋሮ ሠራተኞች በወራት ድካም ሊሠሩት የሚገባን አድካሚ የቁፋሮ ሥራ በቀላሉና በፍጥነት እንዲሳካ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የወርቅ ማዕድን አውጪዎች፣ የነዳጅ ጉድጓድ ቆፋሪዎች እንዲሁም ተራሮችን በመቦርቦር መንገዶችን የሚገነቡ ባለሙያዎች ሁሉ ይጠቀሙበታል፡፡ ነገር ግን ይህ ፈሳሽ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው፡፡ በነዚያ ጭለማ፣ እርጥብና የሚያዳልጡ ጉድጓዶች፣ ፈንጂውን ፈሳሽ የያዘው ባለሙያ የከተንገዳገደ እንደሆነ ዘግናኝ ዜና መሰማቱ አይቀርም ነበረ፡፡
በማዕድን ማውጫ ጉድጓዶች አካባቢ፣ ናይትሮግሊስሪን ያለ ዕቅድ በድንገት የፈነዳ እንደሆነ ጉዳቱ እስከ አጐራባች መንደሮች ይዘልቃል፡፡ በ1866 እ.ኤ.አ ዌልስ ፋርጐ በሚባል የጭነት አመላላሽ (አሁን ከፍተኛ የፋይናንስ አገልግሎት ድርጅት) ይጓጓዝ የነበረ የናይትሮግሊስሪን ፈሳሽ በጉዞ ላይ እያለ መንጠባጠብ መጀመሩን የተመለከቱት የትራንስፖርቱ ሰራተኞች የመያዣ ዕቃውን ከፍተው ለመመልከት በሚል እሽግ በርሜሉን በመዶሻና በመሮ መቀጥቀጥ በጀመሩበት ቅጽበት ፈንድቶ 15 ሰዎች ሰቅጣጭ አሟሟት ሞቱ፤ በኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የነበሩ ሕንፃዎች መስታዎቶቻቸው ከመሰባበራቸው በላይ የፍንዳታው በድምጽ ከስልሳ ኪሎሜትር ርቀት በላይ የተሰማ ነበረ፡፡ ነዋሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ ነበረ የመሰላቸው፡፡ በፍንዳታው የሞቱ ሰዎች አካላት ከአንድ ኪሎ ሜትር የበለጠ ርቀት ላይ ተበታትነው ተገኙ፡፡
በ1864 ታናሽ ወንድሙን በተመሳሳይ ፍንዳታ ያጣው አልፍሬድ ኖብል የተባለ ሳይንቲስት፤ ይህን ናይትሮግሊስሪን የተባለ ህይወትንም ሞትንም አስተሳስሮ ያዘለ ፈሳሽ ፈንጅ ጥቅም እንጂ ጉዳት እንዳይኖረው ለማድረግ ይታትር ገባ፤ እናም ተሳካለት፡፡
አቶ ኖቤል (እንዲህ በአማርኛ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ፈረንጆች ስም ሲጠራ ሥራዎቻቸው የኛ ይመስሉኝና ደስ ይለኛል አርስቶትል አርጣጣሊስ፣ ፕሌቶ ጲላጦስ፣ ፒተር ጴጥሮስ…) ናይትሮግሊስሪንን ከሆነ የአፈር ዓይነት ጋር አደባልቆ ፈሳሹን ሊጥ በማድረግ ሆን ተብሎ ካልታዘዘ በቀር በድንገት እንዳይፈነዳ በማድረግ ዳይናማይት ብሎ ሰየመው፡፡
የዳይናማት ሊጥ እየተድቦለቦለ እንዲፈረካክሱ በሚፈለጉ የቋጥኝ ተራሮች ውስጥ በመወሸቅ እንዲፈነዱ ሲታዘዙ መፈንዳትና ጥቅም ላይ ብቻ መዋል ጀመሩ፡፡ እንደ ልብ ሊጓጓዙ ከመቻላቸውም በላይ ከሠራተኞች እጅ ላይ አምልጠው ቢወድቁ እንኳ ድንገተኛ ፍንዳታን የማያስከትሉ ሆኑ፡፡
ዳይናማይት የበርካታ ሰዎችን ህይወት ማዳን በቻሉና ጉዳት አልባ በመሆናቸው አቶ ኖብልን ሃብታም አደረጉት፡፡ አቶ ኖብልም ዕውቀቱን ለዓለም ጥቅም ማዋል በመቻሉ ሲደሰት፣ ታላቅ ወንድሙን በህመም ምክንያት በሞት አጣ፡፡ በዚህ ጊዜም አንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ወንድማማቾቹን በማምታታት፣ “የሞት ነጋዴው ሞተ” የሚል ዜና ይዞ ወጣ፡፡ አቶ ኖብልም በጋዜጣው በርካታ ሰዎችን በመግደል፣ ሃብት ስለማካበቱ የተፃፈውን ዝርዝር ዜና ሲሰማ፣ ከርሱ ሃሳብ እውነታ ጋር የሚፃረር በመሆኑ እጅግ ከመደንገጡም በላይ ማመን አቃተው፡፡
አቶ ኖብል በዓለም ታሪክ ጋዜጦቹ ባመኑበት መሰሪ ሁኔታ መታወሱን ፍፁም ባለመፈለጉ አንደ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ይህም ለዓለም ጥቅም አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች በየዓመቱ ሽልማት የሚሰጥ ድርጅት በገዛ ገንዘቡ አቋቋመ:: በየዓመቱም ለሳይንስ (ኋላም ለፊዚክስ) ለኬሚስትሪ፣ ለህክምና፣ ለሥነ-ጽሑፍ፣ በልዩ ሁኔታ የኖብል የሠላም ሽልማት በሚል በተዘረዘሩት ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረበቱ ሰዎች መሸለም ጀመረ፡፡ ይህ የአቶ ኖብልን ስም የያዘው ሽልማትም የማንኛውም ሳይንቲስትና የሀገር መሪዎችን ጨምሮ የሁሉም ሰው የመጨረሻና እጅግ የተከበረ የስኬት ግብ ምኞት መሆን ቻለ፡፡ እናም አቶ ኖብል በመጨረሻ በዓለም ታሪክ እንደ ጋዜጠኞቹ ያልተጣሩ “የሞት ነጋዴ” የሚሉ አሉባልታዎች ሳይሆን እንደ እውነተኛው ንፁህ ልባቸው መሻትና ዕቅድ መታወስ ቻሉ፡፡
እነሆ የአቶ ኖብል ታላቅ ትሩፋትም ቅንና ፀዓዳ ሰብዕና ባላቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አማካኝነት ለእኛም ደረሰን!!
የኖብል ሽልማት የግለሰብ ሽልማት አይደለም፤ እንኳንስ ለተሸላሚው ሰውና ለሀገሩ ቀርቶ ለአህጉሩም ጭምር የኩራትና (በተገቢው መንገድ ከተጠቀሙበት) የህብት ምንጭ ነው:: መላው ኢትዮጵያውያንና መላው አፍሪካውያን እንኳን ደስ አለን!!!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን እንኳን ደስ አልዎት ብቻ ሳይሆን ለዚህ ክብር ስላበቁን ላመሰግንዎት እወዳለሁ፡፡  


Read 1310 times
Administrator

Latest from Administrator