Saturday, 19 October 2019 12:33

የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ - የአዲስ አበቤ!

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)


አየ፡ ምነው እመ ብርሃን፡ ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከ መቼ ድረስ እንዲህ፡ መቀነትሽን ታጠብቂባት
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፡ ሰቀቀንዋን፡ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺኮ ማንም የላት . . .
+++
አዋጅ፡ የምስራች ብዬ፡ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከናቴ ማኅፀን አልፌ
በኢትዮጵያ ማኅፀን አርፌ፡
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ . . .
+++

ያቺን ነው ኢትዮጵያ/አዲሳባ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?
ያችን የልጅነት ምሥራች? የሕፃንነት ብሥራት
የሣቅ የፍንደቃ ዘመን፡ የምኞት የተስፋ ብፅአት
ያቺን የልጅነት እናት
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ ጥርሶችሽን ትነክሺባት?
+++
ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን፤ ‹‹ያችን ነው ኢትዮጵያ እምላት›› ብቻ ብሎ ነው የጻፈው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ባዘጋጀው የባለቅኔው አራት ተውኔቶች መጽሐፍ ምረቃ ላይ ጋሽ ፍቃዱ ተክለማርያም፤ አጤ ቴዎድሮስን፡ ጌትነት እንየው አጤ ምኒልክን፡ እንዳለ ብርሀኑ ዘርአይ ድረስን፡  ወክለን ቃለ ተውኔቱን  አጥንቸዋለሁ፡፡ ይሄኛው ምስል  የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ለኢትዮጵያ አባት አርበኞች ክብረ በአል ከሰራው ፕሮዳክሽን የተወሰደ ነው:: ውሎ አድሮ አጎቴ ተክለስላሴ ጋሻውጠና ከወላጅ እናቴ የማርውሃ አበበ ጋር፣ የሰላሌ ኦሮሞ በሆኑት ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ የትውልድ መንደር ፍቼ ተወልደው፣ ማደጋቸውን ነግሮኝ፣ ግጥምጥሞሹ አስገርሞኛል፡፡ ስንቀጥል . . . ባለቅኔው ጋሽ ጸጋዬ ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ሌሊቱን በገነተ ልዑል ቤተ መንግስት ምድር ቤት ውስጥ በግራዚያኒና አኮርባጅ አሽከሮቹ “ኢትዮጵያን ክድተህ በሙሶሎኒ እመን” ተብሎ ሲደበደብ ሲተፈተፍ አድሮ፣ በማግስቱ ጠዋት፣ ሰኔ 21 ቀን በጥይት እሩምታ ተደብድቦ ተገደለ፡፡ ጴጥሮስም እንኳንስ ሰዉ ምድሪቱም በፋሺስት እንዳትገዛ አውግዞ ሞተ›› ይለናል፡፡ እናም የያንዳንዱ አዲሳበቤ ህሊና በዚህ የተቃኘ ነው፡፡ ጋሽ ጸጋዬ ከአምቦ ከተማ ወደ አዲስ አበባ  በመጣ ጊዜ፣ አንድ ምሽት ያጋጠመውንና ለመጻፍ ንሻጤ የሆነውን፤ አቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ላይ ሽንቱን እየሸና ‹‹አንት ድንጋይ፤ ጓደኞችህ በመርሴዲስ ሲንፈላሰሱ  አንተ ግን ወድቀህ ቀረህ፤ ድንጋይ ነህ እሸናብሀለው!›› ከሚል ዠብራሬ ጋር በቡጢ ከተቀማመሱ በኋላ ሌሊቱን ጴጥሮስ ድንጋይ አይደለም ለማለት “ጴጥሮስ ያችን ሰአት”ን ስጽፍ አደርኩ ይለናል፡፡ ጽኑ አቋምና ትእግስት እንዲህ የሚመስላቸው ዠብራሬዎች በየዘመኑ ብቅ ይላሉ፤ አዎን፡፡ እነሆ እኔም መሀል አዲሳባ እምብርት፣ ምኒልክ ሀውልት ስር እየተኛሁ አድጌያለሁና፣ ዛሬ ሌሊቱን የአዛውንቱን ስንኝ (ለበጎ) ገድፌ ‹‹ያችን ነው አዲሳባ እምላት›› ብዬ ለመጻፍ ተገደድሁ፡፡ የአዲሳባ ልጅ ነኛ፡፡ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ መናኸሪያ - melting pot  ከተማ:: ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፤ አዲሳበቤ ነኝ ማለት ይችላል - በፍቅሯ እስከተጸለለ፤ ሰላሟን እስካላደፈረሰ ድረስ፡፡ ‹‹ባደፈርስስ ምን ታመጣለህ?›› የምትል ካለህ፤ ምላሼ ይኸውልህ ... እነሆ አንተ አዲሳበቤ ለመሆን የሞራል ብቃቱ የለህም!!!
ባጎረስኩኝ ተነከስኩኝ ቢሆንም፡ መልካሙን መስዋእት ሁሉ በእንግዳ ተቀባይነት ሲያቀርብ የኖረ፣ እሚኖረው ያዲሳባ ነዋሪ ሁሉ እየሞተም እየተገደለም፣ በመስዋእትነቱ እንደ አቤል ደስ ይለዋል፡፡ እግዚአብሄር ወደ አቤልና ወደ መስዋእቱ ይመለከታልን፡፡ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፡፡ ወደ ቃየንና መስዋእቱ ግን አይመለከትም፡፡ ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ። እግዚአብሔርም ቃየንን አለው። ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት። ቃየንም ወንድሙን አቤልን፦ ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም። እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፦ ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ፦ አላውቅም የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን? አለውም፦ ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ። ቃየንም እግዚአብሔርን አለው፦ ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት። እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል። እግዚአብሔርም እርሱን አለው፦ እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል። እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።
እግዚአብሔር ግን እንደ ሰው አይደለም፤ መኃሪ ነው፡፡ ቁርሾ ታሪክ እየዘበዘቡ ቂም ለሚያድሉን ጸረ- ኢትዮጵያዊያን አኮርባጆች ሁሉ! የምትሉት እውነት ቢሆንኳ ‹‹አይን ላወጣ አይኑ ይውጣ›› ዳኝነት ለአዲሳበቤዎች አይነፋም:: በፍጥረት ታሪክ ከተማን የሰራው ቃየን ነበረ፡፡ ቃየንም ሚስቱን አወቀ ፀነሰችም፥ ሄኖሕንም ወለደች። ከተማም ሠራ፥ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም ሄኖሕ አላት። ሄኖሕም ጋይዳድን ወለደ፤ ጋይዳድም ሜኤልን ወለደለ፤ ሜኤልም ማቱሣኤልን ወለደ፤ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ። ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ሴላ ነበረ። ዓዳም ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ። የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፤ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ። ሴላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች። ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው። “እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፥ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጕልማሳውን ለቍስሌ፥ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና ቃየንን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፡፡”ይላል መጽሀፉ፡፡ እኔ ደሞ እልሀለሁ፤ ከታሪክ እንደምናየው አዲስ አበባንና የአዲስ አበባ ልጅን የነካን ሰባ ሺህ ጊዜ ይበቀሉታል፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊ ሁሉ መዲና - የአገራችን ኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናትና፡፡
ኢትዮጵያዊ የሰው ዘር መገኛ፣ የድንቅነሽ ሉሲ ምድር ሰው ነውና፣ የሰው ልጅ ኃይማኖትን ሲፈጥር ገና በዛፍና ተራራ ከብቶችና ወንዞች ማመንን Animism ከጥንታዊያኑ ባቢሎናዊያንና ሜሴፖታሚያዊያን መሳ ሲጀምር ቀዳሚ መሆኑን፤ እንዲሁም በአንድ አምላክ ማመንን Phanotoism ከእባራዊያን ጋር ለነቢዩ ሙሴ ሴት ልጃችንንን ሲጳራን ድረን፣ በክርስትና ኢሱስን እና እናቱን ድንግል ማርያምን በስደታቸው አስጠልለን፤ በእስልምና የነቢዩ መሀመድን (ሰዐወ) ተከታዮች ከቁሬይሽ አሳዳጆቻቸው ሲሰደዱ ተቀብለን ያኖርን ህዝብ ነንና፤ እኒህ ሁሉ መስተጋብሮች የተከናወኑባት ታላቋ ኢትዮጵያ አስኳል የሆነችው አዲስ አበባ ከተማና ህዝቦቿ፤ እያንዳንዱን ጉዳይ እንደ ጀማሪ የሚሰበኩባት አለመሆኗ እንኳንስ ለእኛ ለአለም ሁሉ የተገለጠ ገሀድ እውነት መሆኑን አንክድም፡፡ አዲስ የሆነባቸው ሊያስረዱን ለሚሞክሩት ነው፡፡ እኛ ግን የአዲስ አበባ ልጆች በትህትና እንላለን፤ ‹‹አንቺም በኃይማኖትሽ እኔም በኃይማኖቴ መኖር እንችላለን አይጠበንም ቤቴ›› እንጂ አንዱን ጥሎ፣ አንዱን አንጠልጥሎ፣ አሁንም ለአዲሳበቤ  አይነፋም የምር! እሱ ነው ከፍ አላደርግ ብሎን ባለንበት መሄድን እንደ እርግማን ያከናነበንና!ለአለሙ ሁሉ የኃይማኖትና የባህል፣ የታሪክ መዘክርና ህያው ቅርስ መሆን እየተቻለን፣ በእኔ እበልጥ መጠላለፍና ሰርክ መነታረክ! ኤዲያ!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ በሸገር ሬዲዮ ከመአዛ ብሩ ጋር ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ፣ አሁን የሚያነብቡትን መጽሐፍ Sapiens ሰምተን፣ አዲሳባ መጽሐፍት ተራ አገኘነውና ‹‹አከቤ›› ቤት በጋራ እያነበብን ስናሰናስል ምን አስታወስን? ኦባማ የመጡ ጊዜ ሉሲን በጣታቸው እየነኩ  ‹‹እና ሉሲ ሳፒያን ናት ነው እምትሉኝ?.. ብለው የጠየቁትን፡፡ ምናልባት እሳቸው ስለ ጉዳዩ የነበራቸው እውቀት ይሄ አለምን በተነባቢነት ካጥለቀለቃት ሴፒያን የተባለ መጽሐፍ በፊት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እኛ ግን የድንቅነሽ ምድር ነን እያልን እንደገጋለን እንጂ ሉሲ ከዛፍ ላይ ወድቃ ከሞተች፣ የእሷ ዘመን ሰዎች ገና በ3 እስከ 2 ሚሊዮን አመታት በፊት የኖሩ ነበሩና፡፡ እሳትን የፈጠሩቱ ከኒአንደርታል በኋላ የመጡቱ ከ300 ሺ አመት በፊት የነበሩቱ:: ሳፒያኑ በምድር ላይ የኖሩት ከእነ ሉሲ በጣም ዘግይተው ከ200 ሺ አመት በፊት ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ በዝግመተ ለውጡ ውስጥ ያለንን ድርሻና ከቀረው አለም ጋር በጋራ ለመጓዝ ተቀራራቢ አስተሳሰብ Global thinking ለማዳበር ገና ብዙ የቤት ስራ evolution እንደሚጠበቅብን  ፍንትው አድርጎ የሚያስረዳ ነው፡፡ እና ይህን ሀሳብ የምናንሸራሽረው ተወልደን ባደግንበት ከተማ በየመንገዱ ላይ መኪናችንን አስቁመው፣ ብጥር አድርገው ፈትሸውን፣ ወደ አከቤ መከዳ ቤት ከተሰባሰብንና ይዘነው የመጣነውን ለምለም ቄጤማ ከጎዘጎዝን በኋላ ነው፡፡ አከቤ እሱ ያጋጠመው የጥድፊያ ፍተሻ እንደነበረና የተሳፈረበት መኪናም እንዳልተፈተሸ ሲያወጋን ቆይቶ እንዲህ አለ ‹‹የተሳፈርንበት ታንክ ቢሆን ኖሮ ብላችሁ አስቡት እስቲ፡፡ እኛ እንፈተሻለን፤ ከዚያ ታንኩን እየነዳን እንሄዳለን ማለት ነው?...›› በሳ....ቅ!!! (‹‹አከቤ››  አገሬ ከተማዬ ቤቴ፡፡ አዲስ አበባ፡፡
ከነገረ ቀደም እንደ መጽሀፉ የየእለት ውሎ ስንቁን በየጉያው ሸጉጦ የሚላወስን ሰላማዊ የአዲሳባ ነዋሪ፣ ምን አድርግ ብለህ እንደ ባእድ ቆጥረህ በፍተሻ ታጉላላዋለህስ? መቸም የአዲስ አበባ ልጅ ሱሪ ኪሱ ፍቅር፣ ሸሚዝ ኪሱ ሰላም፣ ጃኬቱ ውስጥ ተስፋ ሸጉጦ ነው እሚንከላወሰው:: የተረፈው ቢኖር ከመላው የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት በየዘመኑ የሚወረወር የግጭት እሳት ማቀጣጠያ ማገዶና ምድጃ መሆን ብቻ ነው:: እሚመጣ የሚሄደው፤ያለፈ ያገደመው ሁሉ በየምክንያቱ ወህኒ እሚወረውረው፤ በጥይት አረር የሚያሳርረው የየአብዮት ተብዬዎች ቁጣ ማብረጃ  መሆን፡፡ የጅብራልተሩ አለት የይድነቃቸው ተሰማ አባት ሁለገቡ ጉምቱ ኢትዮጵያዊ፣ አራት አይናው ባለቅኔ በዘመን በትዝብት እንዳሉት ‹‹ተሰማ እሸቴ፤ ታስሬ አለሁኝ በገዛ ቤቴ፡፡››
በትምህርት አጋጣሚ ምዕራብ አፍሪቃ ያገኘናቸውና 500 ብሄረሰብና ቋንቋ ተናጋሪዎች 130? ሚሊዮን ህዝቦች ያላቸው እናም በአንድ የፖሊስ እዝ በመተዳደር በአፍሪቃ ዘመናዊ ‹‹መንግስትና የህዝብ አስተዳደር›› ስልጣኔያቸውን የሚያሳዩን ናይጄሪያዊያን ጓደኞቻችን፤ የሰሞኑን የአገራችንን ሁናቴ እየተከታተሉ ማሽቆልቆላችን እየገረማቸው፣ የሚጽፉልኝ መልእክት ያሳቅቀኛል፡፡ ምክንያቱም እነርሱ እኛን እሚያስቡን በቀደምት የስልጣኔ ባለቤትና ሉአላዊ ህዝብነት፣ ልክ እንደ የአፍሪቃዊያን ሁሉ የነጻነት ቀንዲል፣ የመላው አለም ጥቁር ህዝቦች ኩራት አድርገው ነዋ/ነበራ! ኩራታችንን በጋራ የኢትዮጵያ ህዝቦች መስዋእትነት እንዳላመጣነው ሁሉ የአንድ ወገን ድል አድርገን ለማዳፈን ስንርመጠመጥ እንዴት አይገረሙ፡፡ እኛስ ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ እያልን መሆኑን እንዴት እናስረዳቸው:: እነርሱማ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ክብር ልክ ወደ ተስፋዋ ምድር ለመሄድ በመቃተት ላህይ በሚቀነቀን ታዋቂ ሙዚቃ አጅበው ነበር የሸኙን፤ እንዲህ እያሉ . . .
There is a land
far far away
tis called Addis Ababa...
ሁሉም ያልፋል፤ ደሞ ይህም ያልፋል:: እንዲል ቃሉ፤ ባለፈውም፣ በሚኖረውም፣ በሚመጣውም ውስጥ ሆነን፤ የዘወትር ዜማችንን አናቋርጥም . . . ‹‹ውብ አዲስ አበባ የትውልድ አገሬ›› እንላለን፡፡ እንዲሁም ከየትኛውም  ሀገር የመጣን አዲሳባን በመኖሪያነት ከተጠለሉ ጋር ሁሉ እየተቀባበልንም እናንጎራጉራለን - ‹‹አዲስ አበባ ቤቴ›› እያልን፡፡  ‹‹አመል እንጂ ቦታ አይጠብም››፡፡ እኔነት ቀፍድዶ የያዛቸውና የአዲስ አበባን ክፉ የሚመኙ ሁሉ በዘመናት ውስጥ እንደተስተዋለው፣ መጨረሻቸው ውርደትና ሽንፈት መሆኑንም በአደባባይ ለመመስከር እንቆማለን፡፡
ክብር ለአዲስ አበባና ነዋሪዎቿ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ አገራችንንና ህዝቦቿን ይባርክ!
 አሜን!!!

Read 792 times