Saturday, 19 October 2019 12:43

ኬንያውያን በልግስና ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን ይዘዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የማያውቋቸውን የተቸገሩ ሰዎች በመርዳት፣ ለበጎ ምግባር ገንዘብ በመለገስና በበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ አላቸው የተባሉት ኬንያውያን፤በልግስና ከአፍሪካ የአንደኛ፣ ከአለም አገራት ደግሞ የ11ኛ ደረጃን መያዛቸውን ሰሞኑን የወጣ አንድ አለማቀፍ ጥናት አመልክቷል፡፡
ቻሪቲስ ፋውንዴሽን የተባለ ተቋም በ128 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ከአለማችን አገራት መካከል በልግስና ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው አሜሪካ ስትሆን በርማና ኒውዚላንድ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
አውስትራሊያ፣ አየርላንድ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድ፣ ሲሪላንካና ኢንዶኔዥያ በተቋሙ የ2019 እጅግ ለጋስ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን አገራት መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል በልግስና የመጨረሻውን ደረጃ የያዘችው አገር ቻይና ስትሆን፣ ግሪክና የመን በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ቻሪቲስ ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም፤ ዜጎች የማያውቁትን ሰው በመርዳት፣ ለበጎ ምግባር ገንዘብ በመለገስ ወይም በበጎ ፈቃደኝነት በመሳተፍና ሌሎች መልካም ተግባራትን በመፈጸም ረገድ ያላቸውን ተሳትፎ በመገምገም፣ የአገራቱን የልግስና ደረጃ እንደሚያወጣ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ኢንዶኔዢያ በልግስና ከፍተኛ መሻሻል ያሳየችዋ ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ናት ያለው የተቋሙ ሪፖርት፤ ኬንያን በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡

Read 1255 times