Saturday, 19 October 2019 12:37

ቅምሻ ከድረገፅ ዘገባ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በኦሮሚያ እጅግ ተስፋ ሰጪ የፖለቲካ መስተጋብር እየታየ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ እየተሸረበ ያለው የፖለቲካ ቁማር አስቀድሞ ወላፈኑ የሚገርፈው የኦሮሞን ሕዝብ በተለይም ወጣቶችን እንደሚሆን ስጋታቸውን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። አቶ ገመቹ ደንደና እንደሚሉት ግን ሳይገባቸው እንደ አቦሸማኔ የሚጋልቡት መብዛታቸው ከስጋትም በላይ ነው። ምልክቶችም እየታዩ ነው።
በተለያዩ መድረኮች በቃል ደረጃ ከሚሰማው በቀር በኦሮሚያ “ተስፋ ሰጪ” የሚባለው የፖለቲካ መስተጋብር በገቢር የሚታይ እንዳልሆነ “ተስፋ ሰንቀናል” የሚሉት ራሳቸው የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ለኦሮሞ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ ወገኖች፤ ከጥቅም ባሻገር ልዩነታቸውን አስወግደውና አቻችለው በሰላማዊ መንገድ ለመፎካከር መስማማት አለመቻላቸውን እነዚሁ ወገኖች በሃፍረት የሚገልጹት ነው። ልዩነት ቢኖርም ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ አለመቻልና ነፍጥ ይዞ እስከ መገዳደል መድረሳቸው የመጨረሻው መጀመሪያ ማሳያ አድርገውም ይወስዱታል።
ሕዝብን በማይወክል ደረጃ የሚራገቡ አጀንዳዎችና ፕሮፓጋንዳዎች አየሩን መሙላታቸው ዛሬ ላይ ድል ቢመስልም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ልብ የሚያደርስ መረጋጋት እንዳይፈጠር ምክንያት እንደሆነ አቋም ይዘው የሚወተውቱ አሉ። ጥፋቶችን የማረም ሥራ ከተሠራ “ተስፋ ሰጪ” የሚሰኘው የፖለቲካ ጅማሮ፣ ከተስፋ እንደሚዘል በተስፋ ላይ ተስፋ ደርበው ያምናሉ።
“ቁማር እየተቆመረ ነው” የሚሉት ወገኖች በበኩላቸው፤ በኦሮሚያ ክልል ምን እየተደረገ እንደሆነ ለመረዳት የሚያዳግቱ አጋጣሚዎች እየበረከቱ መሆናቸውን ያወሳሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎች አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ፤ ከራሳቸው ጉዳይ አልፈው የኦሮሞን ጥቅም እናስከብራለን የሚሉ ወገኖች፤ በሲዳማ፣ በቅማንት፣ በአገውና በሌሎች ጉዳዮች ውስጥ መነከራቸው የማንን አጀንዳ እያስፈጸሙ እንደሆነ ይጠይቃሉ።
በኦሮሞ ህዝብ ስም ቅማንት ውስጥ ገብቶ እሳት መቆስቆስ፣ አገው ምድር ገብቶ ረመጥ ማራገብ፣ ሲዳማ ውስጥ ገብቶ ሕዝብ እንዲጫረስ አቅጣጫ ማስቀመጥና በሚዲያ ማራገብ፣ በራያና መሰል ጉዳዮች መነካካት ፍጹም እንደማይጠቅም የሚናገሩ ወገኖች፤ “አጀንዳ ተሸካሚዎች” ለኦሮሞ ሕዝብ ጠላት እየገዙለት ነው ይላሉ።
ይህ አካሄድ የሰሜኑ ፖለቲካ ውጥረት የተነፈሰ ዕለት የኦሮሞን ሕዝብ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። እነዚህ ወገኖች ወደ ኋላ ሄደው “በእኔ ስም አይደረግም” በሚል ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም የሚፈጽመውን በደል እንዲያቆም ሲጠየቅ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬም የኦሮሞ ሕዝብ፣ በተለይም ልሂቃኑ በኦሮሞ ስም የሚያከናወኑትን አስከፊና ነገ ዋጋ የሚያስከፍሉ አካሄዶችን “በስማችን እንዲደረግ አንፈቅድም” ሊሉ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ለውጡን ወዳልሆነ አቅጣጫ በመግፋት ለውጡ እንዲጨናገፍ ሌት ተቀን ለሚታትሩ ቀበኞች አሳልፎ ለመስጠት የሚሰሩ የኦሮሞ ልሂቃን፤ ለውጡ የተከፈለበትን የደም ዋጋ፣ ዋጋ ቢስ እንዳያደርጉት ከሚሰጉት መካከል አንዱ አቶ ገመቹ ደንደና ናቸው።
ምንጭ፡- (“ጉልጉል” ጋዜጣ)

Read 1445 times