Print this page
Saturday, 19 October 2019 13:27

ኪስ የሚያቃጥል የስፖርት ቁማር፣ አገር ከሚያቃጥል የፖለቲካ ቁማር ይሻላል፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹ኢትዮጵያ በስፖርት ቁማር ሰክራለች›› ብሏል ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት፡፡  
‹‹የስፖርት ቁማር ማለት፣ ‹የምትታለብ ላም› ማለት ነው›› ብሏል - አንደኛው የቁማር ድርጅት::  
ኪሳራውስ? በቁማርተኞች ላይ ነው፡፡ ኪሳቸውን እያቃጠሉ፣ ውስጣቸውን ያነድዳሉ፡፡  
በፖለቲካ የሚቆምሩ ግን፣ ሌሎች ሰዎችን ይማግዳሉ፡፡ አገርን ያቃጥላሉ፡፡
ክፋቱ፣ የፖለቲካ ቁማር፣ አይነቱ ብዙ ነው፡፡ አንዱ የዘር የብሔር ካርድ ይጥዳል፡፡ ሌላው የሃይማኖት ተከታይነትን እየመዘዘ ይለኩሳል:: ሦስተኛው ድሃ ሀብታም እያለ ምቀኝነትን ይቆሰቁሳል፡፡   
የስፖርትና የፖለቲካ ቁማር መሳሪያዎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሞባይልና ኢንተርኔት፣ እንዲሁም በተቃወሰ ኢኮኖሚና በስራ አጥነት አማካይነት፣ ለማገዶነት የተጋለጠ ብዙ ወጣት፡፡
በየመንገዱ፣ በርካታ ወጣቶች፣ ቁራጭ ወረቀት ይዘው፣ በትኩረት ጽሑፉን ሲመረምሩ የተመለከተ ባለስልጣን፤ ‹‹በቫት ደረሰኝ የሚመሰጥ ሰው በዛ›› ሊል ይችላል። የቫት ደረሰኝ ለዜጎች የሚቆጠቁጥ ቢሆንም፣ ለመንግሥት ግን ገቢ ይጨምርለታል፡፡
በእርግጥ ወረቀቶቹ የቫት ደረሰኝ አይደሉም:: የሰዎችን ኪስ የሚቆነጥጡ መሆናቸው ግን አልቀረም - በስፖርት ቁማር፡፡
ከቁማር ድርጅቶች ቁጥር መበራከት ጋር፣ የቁማርተኛ ወጣት ቁጥርም እጥፍ ድርብ ጨምሯል፡፡
ስፖርት፣ በተለይ እግር ኳስ፣ የብሽሽቅና የስድብ፣ የግርግርና የድብድብ ሰበብ፣ ከዚያም አልፎ የዘረኝነትና የጥላቻ፣ የሞትና የትርምስ ማራገቢያ በሆነበት አገር፣ “የስፖርት ቁማር በዛ” ብሎ ማማረር፣ ቅንጦት ሊሆንብን ይችላል፡፡
ለነገሩ፣ የስፖርት ምንነትና ዋነኛ አላማ፣ ቀስ በቀስ እየተዘነጋ ከሰዎች አእምሮ የደበዘዘ ጊዜ ነው፣ ነገር የተበላሸው፡፡
ስፖርቱ ተረስቶ፣ የስፖርተኞች ብቃት ተንቆ፣ በዚሁ ምትክ፣ የቲፎዞ ጭፈራ፣ “የአጫዋቾች” ቀልድ፣ የነገረኞች ተረብ፣ ዋነኛ የስታድዬም ድግስ መሆን የጀመሩ ጊዜ ነው፣ የቁልቁለት ጉዞ የተጀመረው፡፡
“የላቀ የሰው ልጅ ብቃትን” አጉልቶ በግላጭ ማሳየት፣ ቀዳሚውና ዋነኛው የስፖርት ዓላማ መሆኑ ተረሳና፤ ለስም ብቻ ሆኖ ቀረ፡፡ “ስፖርት”፣ ከእግር ኳስ ስፖርት ውስጥ ጠፋ፡፡ ከስታዲየም አጠገብ የሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን እንኳ፣ ድሮም ያን ያህል ከስፖርት ጋር ጥሩ ትውውቅ ነበረው ማለት ያስቸግራል:: ህንፃ ላይ የተሰቀለው ባለመብራት የስም ማስታወቂያውም፤  “SPORT OMMISION” የሚል ሆኗል፡፡ ከስፔሊንግ ስህተት በስተቀር እውነተኛ መልዕክት የያዘ ማስታወቂያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ (“የመብራት ብልሽት ጉድ ሰራፀ” እንሚል ተስፋ እናድርግ፡፡)
ከህንፃው ስር እና በከተማዋ ዙሪያ፣ ታክሲ ወይም ባቡር እየጠበቁ፣ በየሰፈሩ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ወይም በየመጠጥ ቤቱ ድራፍት እየጠጡ፣ ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል ገደማ፣ ከስፖርት ውድድር በኋላ በስሜት የሚነጋገሩና የሚጨቃጨቁ ብዙ ወጣቶች፣ ስለ ጨዋታ ጥበብ፣ ስለተጫዋቾች ብቃትና ብርታት ነው ሃሳባቸውና ስሜታቸው? በከፊል አዎ፡፡ ገሚሶቹ ላይ አዎ፡፡ ይሄኛውን ወጣት ደግሞ ሰሙት፡፡ “ሲቲ፣ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ ዛሬ ምን ነክቶት እንደሞተ እንጃ፡፡ በጣም ነው ያፈርኩበት”…እያለ አንዱ ወጣት ሲናገር… አንዴ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁለቴም ሦስቴ እየደጋገመ ሲያወራ ስትሰሙ፤ “ለጨዋታ ብቃትና ብርታት የሚቆረቆር ነው” ትሉ ይሆናል፡፡ አዎ ይመስላል፡፡
በጣም ሲደጋግመው፤ ከጓደኛው የመጣበት ምላሽ፣ የታክቲክና የቴክኒክ ትንታኔ ሳይሆን፣ “ብር መበላት አዲስ ነገር አይደለም” የሚል ነበር፡፡
“ግን በጣም አፈርኩበት” አለ እንደገና በማንችስተር ሲቲ መሸነፍ የተንገበገበው ወጣት፡፡
በስፖርት ቁማር፣ ኪሱ ተቃጥሎበታል፡፡ እንደ ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ የመሳሰሉ ጠንካራ ክለቦች፣ ለቁማር አስተማማኝ ይመስላሉ፡፡ ግን፣ የሚያስገኙት የቁማር ገቢ ትንሽ ነው፡፡ ከተሸነፉ ደግሞ ኪሳራው ትልቅ ይሆናል፡፡ ወጣቱ፣ በጣም ቢንገበገብ አይገርም:: ስፖርት እንዲህ መሆን አልነበረበትም:: መንፈስን የሚያነቃቃና የሚያድስ ፀጋ፣ ስፖርትን የመሰለ ድንቅ የመንፈስ ምግብ፣ እንዲህ መርከሱ ያሳዝናል፡፡
ቢሆንም ግን፣ የስፖርት ቁማር፣ ኪሳራው፣ በቁማርተኞች ላይ ነው፡፡ ኪሳቸውን ነው የሚያቃጥሉ፡፡
በአገር የሚቆምሩ ግን፣ አገርን ያቃጥላሉ፡፡ የቁማርተኞቹ ሳይሆን፣ የሌላ ሰው ነው ሸክሙ:: የፖለቲካ ቁማርተኞች፣ በዘር እና በሃይማኖት ሰበብ እሳት እየለኮሱ ያቀጣጥላሉ፡፡ ሌላው ሰውስ? አንዳንዱ ማገዶ ይሆንላቸዋል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ፣ የዘረኝነትን እሳት፣ በሃይማኖት ሰበብ የተቀሰቀሰውን ቃጠሎ ለማጥፋት ይለፋል፡፡
“አገር እንዳይተራመስ፣ ተፈጥፍጦ እንዳይፈረካከስ የመጠበቅ ኃላፊነት የእያንዳንዱ ሰው ነው” ብሎ የሚያስብ ጨዋና አዋቂ የስነምግባር ሰው ይኖራል፡፡ እንዲህ አይነቱ ጥሩ ሰው ላይ፣ የሃላፊነት ሸክም መጫን፣ በዚያ ላይም ሸክሙን ማብዛት፣ የፖለቲካ ቁማርተኞች መደበኛ “ስራ” ነው፡፡ ጨዋና አዋቂ የስነምግባር ሰዎች ጫንቃ ላይ ሸክም መጫን ብቻ ሳይሆን፣ ከስር ከስር በማጥና በረመጥ እረፍት መንሳት፣ ከፊት ለፊት እንቅፋት እየጋረጡ ማሰናከል፤
እንደ አሎሎ የኋሊት መጐተት፣ ከግራ በኩል እርግጫ፣ ከቀኝ በኩል ቀስፎ የሚይዝ የጐን ውጋት ለመፍጠር፣ ቀን ከሌት የክፋት ሰበብና ቀዳዳ መፈልፈል፣ የፖለቲካ ቁማርተኞች ክፉ አመል ነው፡፡ ለምን? ቁማርተኞቹ፣ ያለሃሳብ አገርን ማናጋትና ማናወጥ፣ እሳት መለኮስና ማራገብ ይፈልጋሉ፡፡ ግን፣ በለኮሱት እሳት እንዳይቃጠሉ አይሰጉም ወይ? በማን ነው የተማመኑት? ኪሳራው የነሱ እንዳልሆነ ያውቃሉ፡፡ የፖለቲካ ቁማርተኞች የሚፈጥሩትን መከራ ሁሉ ችሎ፣ አገርን ማቆየት የሌላው ሰው ፋንታ ነው፡፡
የፖለቲካ ቁማርተኞች የለኮሱትን እሳት ለማጥፋት፣ ያናጉትን ምሰሶ ለማጽናት፣ ሌላው ሰው መሯሯጥ ይችላል፡፡ ቁማርተኞቹ ግን፣ እጥፍ ቦታ እሳት እየጫሩ፣ ተጨማሪ ደርዘን ምሰሶ እየናዱ መቀጠል ነው የሚፈልጉት፡፡
በሌላ ሰው ኪስ እንደመቆመር ነው፡፡
የሌላ ሰው ሕይወትንና ንብረትን እያቃጠሉ፣ እንደ ማገዶ እያነደዱ መሞቅ የሚፈልጉ ናቸው፣ የፖለቲከኛ ቁማርተኞች፡፡
“ለምን” ብለን፣ የተሳከረ ሃሳባቸውን፣ የከሰረ የቆሸሸ ነፍሳቸውን፣ የረከሰ የወረደ ማንነታቸውን በጥልቀት ለመፈተሽ መሞከር እንችላለን፡፡ ነገር ግን፣ ከዚህ ጥያቄ የሚቀድም ትልቅ ጥያቄ አለ፡፡
ሌላው ሰው፣ ለምንድነው ለቁማርተኞች ማገዶ የሚሆንላቸው? ለምንድነው አገር፣ ለቁማርተኞች “የምትታለብ ላም” የምትሆንላቸው?
የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን እርግፍ አድርጐ ያልተወ ሰው፣ ሃይማኖትን ከፖለቲካ አጠገብ እንዳይደርስ በሙሉ ልብ ያልቆረጠ ሰው፣ ድሃና ሃብታም የሚል የምቀኝነት ፖለቲካን እርም ያላለ ሰው፣ የፖለቲካ ቁማርተኞች ሲሳይ ማገዶ ይሆናል፡፡  

Read 1846 times