Saturday, 19 October 2019 14:07

149 ሚ. የአለም ህጻናት በቂ ምግብ እንደማያገኙ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከአምስት አመት ዕድሜ በታች ከሚገኙት 700 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናት መካከል 149 ሚሊዮን የሚሆኑት ህጻናት በቂ ምግብ እንደማያገኙና የመቀንጨር ችግር ተጠቂ መሆናቸውን ተመድ ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ ሰሞኑን ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፤ 149 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናት ተገቢውን ምግብ ባለማግኘታቸው ሳቢያ የአእምሮና የተክለ-ሰውነት እድገት ውስንነት ያለባቸውና ለተለያዩ የጤና ችግሮች የተጋለጡ ሆነዋል፡፡
ዕድሜያቸው ከአምስት አመት ዕድሜ በታች ከሆናቸው አጠቃላዩ የአለማችን ህጻናት መካከል ግማሹ ለእድገትና ለጤንነት እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ቪታሚኖችንና ሚኔራሎችን እንደማያገኙም የተቋሙ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህጻናት የመቀንጨር ችግር ተጠቂ ከሆኑባቸው የአለማችን አገራት መካከል የመን ተጠቃሽ ናት ያለው ሪፖርቱ፣ ዕድሚያቸው ለትምህርት ካልደረሰ የአገሪቱ ህጻናት መካከል 46 በመቶ ያህሉ የመቀንጨር ችግር ተጠቂ መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
በአለማችን 800 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በቋሚነት የርሃብ ሰለባ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፤ ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በአንጻሩ ከሚገባው በላይ ብዙ መጠን ያለውና ለጤና ተስማሚ ያልሆነ ምግብ በመመገብ ሳቢያ ለከፍተኛ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ ለልብ ህመምና ለስኳር በሽታ እንደተጋለጡ አመልክቷል፡፡
ከአምስት እስከ አስራ ዘጠኝ አመት የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ የከፍተኛ የሰውነት ክብደት ተጠቂ ዜጎች ብዛት አሜሪካ ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን እንደምትይዝ የጠቆመው ሪፖርቱ፤በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አሜሪካውያን መካከል 42 በመቶ ያህሉ የችግሩ ተጠቂዎች መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 7725 times