Saturday, 19 October 2019 14:09

አንድነት ያለ ብዝኃነት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 የአንድና የብዙ ጉዳይ፣ የዓለም አፈጣጠር ምሥጢር ነው፡፡ የአንድና የብዙ ሁኔታ፣ የአያሌ ጠቢባን፣ የበርካታ ፈላስፋዎች ጥያቄ ነው:: አንዳንዶቹ በአሐዳዊው፣ ሌሎቹ ደግሞ በብዙው ላይ ያተኩራሉ፡፡
ሆኖም ብዝኃነትን ያለ ኅብረት፣ አንድነትን ያለብዝኃነት ማሰብ ይቻል ይሆን?
አንድነትስ አስደሳች የሚሆነው መቼ ይሆን? በደስታም ሆነ በኃዘን ጊዜ፣ በሰላምም ሆነ በጭንቅ ወቅት፣ ተፈጥሮን እየቃኙ ወደ ልብ ጓዳ መግባት ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ ለአንድና ለብዙ ምሥጢርም ሐይቁን መመልከት፣ የወፎችን ዝማሬ ማዳመጥ፣ በእጽዋት፣ በእንስሳትና በሰማዩ ውበት መማረክ ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮ ብዝኃነትንም፣ አንድነትንም አጣምራ ይዛለችና፡፡ ምን የመሰለ ኅብረ ቀለም፣ ምን የመሰለ ኅብረ ዜማ፡፡ የሷን ምሥጢር ማድነቅና ከእርሷ መማር የሚታክተው የሰው ልጅ ግን ያስተክዛል፤ ያሳዝናል፡፡ ሲተባበርና ሲስማማ ድንቅ ተአምር የሚሠራው የሰው ልጅ፣ ለምን ይሆን የሚከፋፈለው? ብዝኃነቱ ነው የሚያጣላው ወይስ ሌላ ምሥጢር ይኖር ይሆን? የሰው ልጅ በጸጥታ ከራሱ ጋር መሟገት፣ ወደ ህሊናውም ዞር ብሎ እራሱን መጠየቅ ይገባዋል፡፡ መፍትሔ የሚገኘው በመረጋጋት፣ በማዳመጥና በማሰላሰል፣ ከውሱኑ እውቀት በላይ ያለውን እውነት በመፈለግ ነው፡፡
ብዝኃነት ያለ ኅብረት አታምርም፤ ብዝኃነት ተብላ መጠራትም አትችልም፤ ወይም አይገባትም፡፡ ይልቁንም “አለመተዋወቅ”፣ “መራራቅ” በሚሉ ቃላት ብትገለጽ ይሻላል:: አንድነት ያለ ብዝኃነት፣ አንድነት ተብላ ልትጠራ ያስቸግራል፡፡ ብዝኃነት የሌላት ወይም ያልነበራት አንድነት ትርጉም የላትም፡፡ ከመጀመሪያው ወይም ከወዲሁ አንድንና አንድ ወጥ ለሆነ ነገር፣ አንድነት የሚባል ቃል ፍች የለውም፡፡ ወደ አንድነት ለመምጣትም ሆነ አንድ ለመሆን ቢያንስ ሁለት መሆን ያስፈልጋል፡፡ ብዙ መሆንም ያሻል፡፡ ብዝኃነት ውበት ሊሆን የሚችለው ከአሐዳዊነት ሲሻገር ነው፡፡ ከቃየልና ከአቤል ታሪክ የኤሳውና የያዕቆብ ታሪክ ያስደስታል፡፡ የዮሴፍና የወንድሞቹ መጨረሻ ያጽናናል፡፡ የቃየልንና የአቤልን ታሪክ ከመድገም የኔልሰን ማንዴላን ራእይ መድገም ይሻላል፡፡
ችቦ በደንብ ደምቆ እንዲያበራ ብዙ እንጨቶች ያስፈልጋሉ፡፡ እንጨቶች ኅብረት ሲኖራቸው እሳቱ ይደምቃል፡፡ የእሳቱ ውበት ሌሎችን ይሰበስባል፡፡ ይማርካል! እንጨቶቹ ሲለያዩ ግን እሳቱ ቀስ እያለ ይጠፋል፡፡ ብዝኃነት ያለ አንድነት ይበርዳል፡፡
አንድነት ያለ ብዝኃነት ያፍናል፡፡ ብዝኃነትና አንድነት ሲተቃቀፉና ሲሳሳሙ ደስ ያሰኛል:: አንድነትና ተስፋ ሲነግሱ፣ ብዝኃነት ቦታ አይጠበውም፤ ሀብትም አያንስም፤ መካፈልና መተሳሰብ ስላሉ አይርብም፡፡ አንድነትና ተስፋ ሲነግሱ፣ ሕይወት ትርጉም ይኖራታል፡፡ ጊዜም ይበረክታል፡፡ እኔ እኔን ለመሆን፤ እሱ እሷ፣ አንተና አንቺ ታስፈልጉኛላችሁ፤ ያለ አንተ፣ ያለ አንቺ፣ እኔ፣ የውሸት ጣዖት ነው የምሆነው፡፡ ያለ አንተና ያለ አንቺ፣ እኔ እራሴን ማወቅ አልችልም፡፡ ሰው ሰራሽ መስታወት ስለ ውጫዊ ገጽታዬ፣ ጊዜያዊ መረጃ ሊሰጠኝ ይችላል፡፡ አንተና አንቺ ግን ወደ ውስጤ ዘልቄ እንድገባ ታደርጉኛለችሁ፡፡ አንተና አንቺ ግን የፈጣሪ ሥራ በመሆኔ የሚገኘውን ጸጋና ሞገስ ታዩልኛላችሁ፣ ታሳዩኛላችሁ፡፡ መስታወቱ ሊወደኝ አይችልም፡፡ አንተና አንቺ ማፍቀርንና መፈቀርን ታስተምሩኛላችሁ፡፡ ኃላፊነትን ታለብሱኛላችሁ፡፡
የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት፣ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ወገን ወይም ማኅበር አልለየም፡፡ በዚህም ልዩ መልእክት አስተላለፈ፡፡ እጅግ ልዩ መልእክት! ጠላትንም መውደድ፡፡ ብዝኃነትን እያከበረ አንድነትን አወደሰ፡፡ እንዲሁም የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ማንነትና ስለ አባልነት ድንቅ ትምህርት አስተማረ:: ብዙኃነትንና አንድነትን ከማንነት ጋር አስተዋወቀ፡፡ ብዝኃነትን ሲያከብር አንድነትን አልተወም፡፡ አንድነትን ሲያውጅ፣ ብዝኃነትን አልጨፈለቀም:: እነኚህን ሁለት እውነቶች እንዴት ማያያዝ እንደሚቻል ያሳየበትን መንገድ ማጤን ልብ ይሏል፡፡ የእሱ መፍትሔ ለብዙ ፈላስፋዎች፣ ለምድር ጠቢባን ምንኛ በጠቀመ፡፡ “ማንነቴ በአባልነቴ አይወሰንም፤ ማንነቴ ከአባልነቴ ይበልጣል” አለ::
አይሁዳዊነት፣ ግሪካዊነት፣ ሮማዊነት፣ ወንድነትና ሴትነት የብዝኃነት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ አይሁዳዊው ልክ እንደ ግሪካዊው፣ ግሪካዊውም እንደ አይሁዳዊ መኖር አያስፈልገውም፡፡ እያንዳንዱ የራሱ ውበት አለው፡፡ ክርስቶሳዊ ኅብረት ግን የበለጠ ያስውባቸዋል፡፡ በግል ከነበራቸው ውበት የበለጠ ውበት ያጐናጽፋቸዋል፡፡ ምጡቁ ከወዲሁ የነበረውን አያጠፋውም፡፡ ይልቁንም ያሳድገዋል፤ ፍጹምም ያደርገዋል፤ “ማንነቴ አይሁዳዊነቴ ብቻ ነው፣ ግሪካዊነቴ ብቻ ነው” ማለት ማንነትን መወሰን ነው፡፡ ያለውን ውበት ማገድ ነው፡፡ የሰው ልጅ “እኔ” ሲል ጤነኛ “እኔ” እና ጤነኛ ያልሆነ “እኔ” እንዳለ ማወቅ ያስፈልገዋል፡፡ “እኛም” ሲል፣ ጤነኛ “እኛ” እና ወደ ጥፋት የሚወስድ “እኛ” እንዳለ ማጤን ይገባዋል፡፡ ከአባልነት የመጠቀ አንድነት ሲኖር ነው ውበትን መቃኘት፣ አንድነትን ማጣጣም፣ ሰላምን ማስፈን፣ ብልጽግናን ማምጣት የሚቻለው፡፡ ---
(ከዮናስ ዘውዴ ከበደ “ሔምሎክ”
መጽሐፍ የተቀነጨበ)


Read 3471 times