Print this page
Saturday, 26 October 2019 11:28

ሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት እንዴት ተጠናቀቀ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ከሦስት ዓመት በፊት የአገራችንን ሥነ ጽሑፍና ፀሐፍትን የማበረታታት አላማን ሰንቆ የተመሰረተው ‹‹ሆሄ›› የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር የሶስተኛው ዙር አሸናፊዎችን በመሸለም ተጠናቅቋል፡፡
 የሽልማት ሥነ ሥርዓት ዘንድሮ በዘጠኝ ዘርፍ ያሸነፉ ግለሰቦችንና ተቋማትን ሽልማትና እውቅና ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት ለንባብ ማደግና መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሁለት ተቋማት እውቅና አግኝተዋል፡፡ ተቋማቱ ‹‹ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ታንበብ›› (Ethiopia reads) ሲሆኑ ሚዩዚክ ሜይዴይ ላለፉት 15 ዓመታት ከ450 በላይ መጽሐፍትን በማስገምገምና ውይይት በማካሄድ እንዲሁም ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቴአትር፣ ሙዚቃና መሰል ስልጠናዎችን በነፃ በመስጠት ላበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ ታንብብ (Ethiopia reads) ደግሞ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ቢሮው በርካታ የልጆች መጽሐፍትን በማሳተምና ለየት/ቤቶች በማከፈፋል እንዲሁም በገጠር አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ ቤተ መጽሐፍትን በማቋቋም ባደረገው አስተዋጽኦው እውቅና አግኝቷል፡፡ ሌላው የሽልማቱ ዘርፍ የልጆች መጽሐፍት ዘርፍ ሲሆን ዘንድሮ ከአማርኛ በተጨማሪ በኦሮምኛና በትግርኛ የተጻፉ መጻሕፍት ራሳቸውን ችለው እያንዳንዳቸው ዘርፍ ሆነው ተካትተዋል፡፡ ዘንድሮም በልጆች የአማርኛ መጽሐፍት ዘርፍ የትክክል ገና ‹‹ጦጢት ጉድ ሆነች››፣ የሳለጌታ ይመር ‹‹ውሸታሙ ቢሊጮ››፣ እና የበሀይሉ ገ/እግዚአብሔር ‹‹ተረቶች በግጥም›› ለውድድር ቀርበው የበሀይሉ ገ/እግዚአብሄር ‹‹ተረቶች በግጥም ሲያሸንፍ፣ በትግርኛ ቋንቋ ሰዓሊና ደራሲ አዶናይ ገብሩ ከጻፋቸው 8 የልጆች መጽሐፍት ውስጥ ‹‹ስንዳየሁ›› አሸንፏል፡፡ በኦሮሚኛ ቋንቋ ደግሞ የጄዴለቻፊ ‹‹ከን ቢሮ›› መጽሐፍ አሸንፏል፡፡
ዘንድሮ በረጅም ልብ ወለድ መጻሕፍት ዘርፍ 16 መጻሕፍት ለውድድር ቀርበው አምስቱ ማለትም የዘነበ ወላ ‹‹መልህቅ››፣ የአለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) ‹‹መርበብት››፣ የአዳም ረታ ‹‹አፍ››፣ የዶ/ር ኤሊያስ ገብሩ ‹‹ኢትዮጵ›› እና የፍሬ ዘር ‹‹ጃን ተከል›› ወደ መጨረሻው ዙር አልፈው የአዳም ረታ የመጨረሻ ስራ የሆነው ‹‹አፍ›› አሸናፊ ሆኗል፡፡ በግጥም መጽሐፍት ዘርፍ 15 ያህል መጽሐፍት ለውድድር መቅረባቸው የተጠቆመ ሲሆን የሰለሞን ሳህለ ትዕዛዙ ‹‹የልብ ማህተም›› በድሉ ዋቅጅራ ‹‹የወይራ ስር ፀሎት›› የመስፍን ወልደ ተንሳይ ‹‹ክብ ልፋት›› የበቃሉ ሙሉ ‹‹የማያልቅ አዲስ ልብ›› እና የመዘክር ግርማ ‹‹ወደ መንገድ ሰዎች›› ለመጨረሻው ዙር አልፈው፣ የመዘክር ግርማ ‹‹ወደ መንገድ ሰዎች›› አሸናፊ ሆኗል፡፡  በዕድሜ ዘመን የሥነ ጽሑፍ አገልግሎት ዘርፍ ከ16 በላይ ረጅም ልቦለዶችን ጽፋ ለትውልድ ያስተላለፈችው አንጋፋዋ ደራሲ ፀሐይ መላኩ ተሸለማለች፡፡
ዘንድሮ አዲስ የተካተተው የስነ ጽሑፍ ዘርፍ የጥናትና ምርምር›› ሲሆን በዚህ ዘርፍ 3 መጽሐፍት ለውድድር ቀርበዋል፡፡ መጽሐፎቹም በአለቃ ተክለ የሱስ ግርማ ተጽፎ በግርማ ጌታሁን የተዘጋጀው ‹‹የጎጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ››፣ የብራና መጽሐፍት አዘጋጃጀት የተሰኘውና በሊቀ ጉባኤ ፈቃደ ስላሴ ተፈራ የተጻፈው፣ እንዲሁም በአለቃ አፈወርቅ ተጽፎ በስርግው ገላው (ዶ/ር) የተዘጋጀው ‹‹የግዕዝ ቅኔያት›› የተሰኙት ሲሆኑ የሊቀ ጉባኤ ፈቃደ ስላሴ አበራ፣ ‹‹የብራና መጽሐፍት አዘጋጃጀት›› አሸናፊ ሆኗል፡፡

Read 836 times