Saturday, 26 October 2019 11:51

አዋሽ ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ እያከበሩ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 80 ቢ ደርሷል
                           
           በግል ባንክና ኢንሹራንስ ታሪክ ቀዳሚ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አዋሽ ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ የተመሰረቱበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ማክበር ጀመሩ፡፡ ትላንት ከሰዓት በኋላ በኩባንያዎቹ ዋና መስሪያ ቤት በር ላይ ያሰሩትን ቢልቦርድ በይፋ መርቀው በመክፈት፣  በዓሉን ማክበር የጀመሩ ሲሆን ለቀጣዩ አንድ ወር በአዲስ አበባና በመላ አገሪቱ በሚገኙ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶቻቸው ክብረ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ከሰራተኞቻቸው ጋር እንደሚያከብሩ የኩባንያዎቹ ሃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ ህዳር 10 ቀን 1994 ዓ.ም በ486 መስራች አባላት፣ በ24.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ተመስርቶ፣ የካቲት 13 ቀን 1995 ዓ.ም መደበኛ ስራውን የጀመረ ሲሆን ባንኩ 25ኛ ዓመቱን እያከበረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ 4369 ባለአክሲዮኖች፣ 4.4 ቢ. ብር የተከፈለ ካፒታል፣ ባለቤት መሆኑም ተገልጿል:: በ137 ሰራተኞች ሥራውን የጀመረው ባንኩ፤ የመጀመሪያው ዓመት ላይ ጠቅላላ የተቀማጭ መጠኑ 103 ሚ ብር ሲሆን ካፒታሉ 27 ሚ ብር እንደነበር ተገልጿል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 80 ቢ ብር የደረሰ ሲሆን የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን 62.2 ቢ ብር ደርሷል፡፡ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር 47.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን ስራውን ሲጀምር የነበሩት አምስት ቅርንጫፎች በአሁን ወቅት በመላ አገሪቱ ከ420 በላይ መድረሳቸውም ተነግሯል፡፡ ባንኩ ባለፉት 25 ዓመታት 11 ቢ ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን ለመንግስትም ከ3 ቢ ብር በላይ የትርፍ ገቢ ግብር በመክፈል ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ሀላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ማህበራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት ረገድ ግንባር ቀደም መሆኑን የገለፁት ሀላፊዎቹ፤ እስካሁን ከ62 ሚ ብር በላይ በማውጣት በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ሲያግዝ መቆየቱም ተጠቁሟል፡፡
ባንኩ ኮሜርስ ፊት ለፊት በሚገኘው ቦታ ላይ ባለ18 እና ባለ 16 ወለል መንታ ሕንጻዎችን ገንብቶ ዋና መስሪያ ቤት በማድረግ ቀዳሚ ሲሆን በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች 11 ሕንጻዎችን በመገንባት የሀብት መጠኑን ከማሳደግ ጎን ለጎን በከተሞች እድገትና በስራ እድል ፈጠራ ጉልህ ሚና መጫወቱን የባንኩ ሀላፊዎች ተናግረዋል:: ባንኩ በግል ባንክ ታሪክ በአመት ከ1 ቢ. ብር በላይ በማትረፍም መሪነቱን አረጋግጧል ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ እ.ኤ.አ ጥቅምት 1 ቀን 1994 ዓ.ም በ456 መስራች ባለአክሲዮኖች፣ በ4.8 ሚ ብር የተከፈለ ካፒታል የተመሰረተው አዋሽ ኢንሹራንስ፤ በ12 ሰራተኞችና በአንድ ዋና መስሪያ ቤት መደበኛ የኢንዱሹራንስ ስራውን ጀምሮ በአንድ አመቱ 15 ሚ ጠቅላላ የተፃፈ አረቦን መሰብሰብ መቻሉም ታውቋል:: ጁን 30 ቀን 2019 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የአዋሽ ኢንሹራንስ ቅርንጫፍና የአገናኝ ቢሮዎች 54 መድረሳቸውንና የሰራተኞቹ ብዛት ከ12 ወደ 560 ማደጉም ተጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል ከ425 ሚሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን የባለ አክሲዮኖቹም ብዛት 1364 መድረሱን የገለፁት የኩባንያው ሃላፊዎች፤ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት አጠቃላይ ሀብቱ ከ2.5 ቢ ብር በላይ ሲሆን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ797 ሚ ብር በላይ ጥቅል የተጻፈ አረቦን በመሰብሰብ ከሌሎች የግል የመድን ድርጅቶች የበላይነትን መያዙንና 176 ሚ ብር ዓመታዊ ትርፍ ማስመዝገቡን  ጨምረው ገልጸዋል፡፡


Read 979 times