Saturday, 26 October 2019 12:04

መንግስት በሕግ በተሰጠው ሥልጣን የዜጐችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጽንፍ የያዙ አመለካከቶች የሀገሪቱ ሁኔታ ወደ ውጥረት እየከተቱ፣ ዜጐችን ለጥቃት እያጋለጡ መሆኑን የጠቆመው በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ሲቪል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦሲዴፓ)፤ መንግስት የዜጐችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡
በኢትዮጵያ በተፈጠሩ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ምክንያት እየከሰቱ ያሉ ችግሮች የሠላማዊ ዜጐችን በሠላም የመኖር ዋስትና በእጅጉ እየፈታተኑ መሆኑን የገለፀው ፓርቲው፤ ህግ የማስከበር ኃላፊነት የተጣለበት መንግስት አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰድ የዜጐችን መብት ማስከበር አለበት ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ የምትተዳደረው በህገ መንግስት ሆኖ ሳለ ግለሰብ አክቲቢስቶችና ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች የሀገሪቱን ዜነች ሠላም እያናጉ ነው ያለው ፓርቲው፤ እነዚህ ሃይሎች ሃሳባቸውን ማቀንቀንና ፍላጐታቸውን ማስከበር ያለባቸው አሁን በስራ ላይ ባለው የሀገሪቱ ህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ መሆን አለበት ብሏል፡፡
ተገቢነት የሌላቸውና ወቅት ያልጠበቁ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በህግ መሠረት ስርአት ማስያዝ ይገባል ያለው መግለጫው፤ መንግስትም ይሄን ስርአት የማስያዝ ኃላፊነቱን በህግ በተሰጠው ስልጣን መሠረት እንዲወጣ አሳስቧል:: በተያያዘም ፓርቲው፣ አወዛጋቢ የሆነው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ማሻሻያ እንዲደረግበት ጠይቋል፡፡


Read 8931 times