Print this page
Saturday, 26 October 2019 12:20

ባላሳየነው ፍሬቻ፣ ‘ነገር’ ሲጠመዘዝ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 “ስሙኝማ…በተለይ ፖለቲካችን ውስጥ ‘ፍሬሽነት’ እያስቸገረን ነው፡፡ ሳይጣዱ ‘መብሰል’ እያስቸገርን ነው፡፡ ስሙኝማ… ‘ፍሬሽነት’ እኮ ካላወቁበት አለ አይደል…አስቸጋሪ ነው፡፡ ‘ፍሬሽ ቦይፍሬንድ’ ከእንትናዬ ጋር ለመውጣት ያለው ጣጣ፡፡ እሷ ስትዘገጃጅ የፈጀችው ሠላሳ ደቂቃ፡፡ እሱ ሲዘጋጅ የፈጀው አንድ ሰዓት ከሀምሳ አምስት ደቂቃ፡፡--”
            
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ባላሳየነው፣ ነገሮች እየተጠመዘዙ ተቸገርን፡፡ ደጋግመን እንደምናነሳው ሰላምታ እንኳን ስንሰጥ፣ ለቃላቶቻችን መጠንቀቅ ያለብን ጊዜ ላይ እንዳንደርስ የሚያሰጋ ነው፡፡ ልክ ነዋ… በተለመደ የሰላምታ አሰጣጥ “በጎ አደርክ!” የተባለው ሰው... አለ አይደል… “ሳልታመም በጎ አደርክ ያለኝ፣ የሆነ ያሰበው ነገር ቢኖር ነው፣” ሊል ይችላል፡፡ እኛ ሀገር በአማርኛ የተነገረው ‘በአማርኛ ሲተረጎም’ እንዲህ እየሆነ ነዋ! እናማ… ሰውየው ከዓመት ተኩል በፊት እንዲያነበው የሰጣችሁትን መጽሐፍ የሆነ ነገር ‘አስቸክችኮበታል’ ብሎ  ሊያሽቀነጥረው ይችላል፡፡
“እሷን በሁለት እጁ ጨብጦ፣ እኔን በአንድ እጁ ብቻ የጨበጠኝ ያሰበልኝ ተንኮል ቢኖር ነው” ምናምን ቢል አትገረሙማ፡፡ ልክ ነዋ…በአሁኑ ጊዜ እዚች ሀገር ላይ ከዚህ በብዙ እጥፍ የባሱ አስገራሚና ግራ አጋቢ ባህሪያት እያየን ነውና!
ለምሳሌ… “ወጥ የለኝም፣ እንጀራ በሚጥሚጣ ላቅርብልሽ?” የተባለች እንግዳ ልዩ በሆነ ‘ዘመናዊው’ አተረጓጎም፣ “በተዘዋዋሪ ሚጥሚጣ ምላስ ነሽ ማለቷ ነው” ልትል ትችላለች፡፡ ከዚህ በላይ ‘መሳከር’ ምን ሊኖር ይችላል!
ባላሳየነው ፍሬቻ፣ ‘ነገር’ እየተጠመዘዘ ተቸገርንማ!
እኔ የምለው…አለ አይደል…የፉከራ መብዛት፣ ዓለምን ሊያስደንቅ በሚገባ መልኩ የጀግና መበራከት ግራ አጋቢ ነው፡፡ በፊት እኮ ፉከራ እንትናዬ ላይ ሊሆን ይችላል…“ሁለተኛ ከእሱ ልጅ ጋር ባይሽ አንደኛው አገጨችሽን እጅሽ ላይ አስቀምጬ ወደ እናትሽ ነው የምልክሽ” አይነት፣ ወይም…“እንትንሀን አውጥቼ አንገትህ ላይ እንደ ከረባት ነው የምጠመጥምልህ” አይነት ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን አገጭ የለ፣ ከረባት የለ ብቻ ምን አለፋችሁ…የፎካሪው ብዛት! የማይክ ታይሰኑ ብዛት! የናቡከደናጾሩ ብዛት! በዚህ ላይ መፎከሪያው የግድ ወንዝ ዳር፣ ምናምን ላይሆን ይችላል፡፡ በሚዲያ ላይ ይቻላል፡፡ ይህን የሠላሳ ሁለተኛ ክፍለ ዘመን ምጥቀታችንን የሚያይልን ጠፋ እንጂ!
ስሙኝማ…በተለይ ፖለቲካችን ውስጥ ‘ፍሬሽነት’ እያስቸገረን ነው፡፡ ሳይጣዱ ‘መብሰል’ እያስቸገርን ነው፡፡ ስሙኝማ… ‘ፍሬሽነት’ እኮ ካላወቁበት አለ አይደል…አስቸጋሪ ነው፡፡ ‘ፍሬሽ ቦይፍሬንድ’ ከእንትናዬ ጋር ለመውጣት ያለው ጣጣ:: እሷ ስትዘገጃጅ የፈጀችው ሠላሳ ደቂቃ:: እሱ ሲዘጋጅ የፈጀው አንድ ሰዓት ከሀምሳ አምስት ደቂቃ፡፡ ጸጉሩን እንኳን እንደ ኤልቪስ እከፍላላሁ ብሎ ሲፈቀፍቅ፣ የራስ ቅሉ ሰንበር በሰንበር ሆኗል::
እናላችሁ…ዘንድሮ መቼም ሀውልት፣ ሀውልት እያስባለን ነውና… አለ አይደል… በተለይ መሀል ከተማ የዘጠኝ ቁጥር አውቶብስ ፌርማታ፣ ለሸገር ልጆች ለዋለው ውለታ ስፍራው ላይ ሀውልት ይቁምልንማ፡፡ ሱሪው እግሩ አካባቢ ያለው ስፋት (ቤልቦቶም የሚሉት) ከወገቡ ስፋት ሊቀራረብ ምንም ያልቀረው፣ ጸጉሩን ያጎፈረ፣  ወይም ለራስ ምታት ቅቤ የተቀባ እስኪመስል በቅባት ‘ለጥ’ አድርጎ፣ በሀገር ሰላም…ግንባሩን ሠላሳ ስፍራ የከሰከሰ (እንትናዬዎች “ኮስታራ ወንድ ይወዳሉ” የምትል ኒቼ ያልደረሰባት ፍልስፍና ነበረች፡፡) ቅርጽ ይሠራልንማ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የእሱ ሰፈር ሹሮ ሜዳ፣ ነገር ቢኖር ነው እንጂ የጉለሌዋ አስራ ዘጠኝ ቁጥር የምትቆምበት ፌርማታ ምን ይገትረዋል! ቂ…ቂ…ቂ… ደግሞላችሁ… የልዑል መኮንን ኬክ ቤት ግድግዳ ተደግፎ፣ አንድ ሰዓት ያህል የቆመው ነገር ቢኖረው ነው እንጂ… ኬክ አይወድ፣ ባቅላባ የሚባል ነገር እንኳን ሊቀምስ ሲያየው እንኳን ያቅለሸልሸዋል! (“እኔ ቤት ጠጥቼ ነው የመጣሁት፣ አንቺ ቡና በወተት ጠጪ፣” ተብሎ ‘ሁሉም ነገር’ በሦስት ብር ከሰላሳ አምስት ማጠናቀቅ ይቻል የነበረበት ዘመን፡፡)
የምር ግን …‘ፍሬሽነቱ’ ክፋት የለውም:: ችግሩ ምን መሰላችሁ…ገና በመልስ ምትና በፍጹም ቅጣት ምት መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ ሳናውቅ፣ በአንድ ጊዜ “የፕሬሚየር ሊግ ዙፋኑን ካልሰጣችሁኝ…” የምንል መብዛታችን ነው፡፡ ሼፊልድ ዌንስዴይ እኮ መከራውን በልቶ ነው ፕሬሚየር ሊግ የገባው! (ይህ ምሳሌ ከማንቼ ጋር የሚያነካካ ነገር እንደሌለው ይሰመርበትማ! ቂ…ቂ…ቂ...) እናላችሁ… የ‘በጨ/ጠቆረ’ አይነት ፈረንጅ ‘ፔዴስትሪያን’ ሊለው የሚችል ብልጥነት ሲያመጣባችሁ…አለ አይደል… አሪፍ አይደለም፡፡
የብልጥነት ነገር ከተነሳ ይቺን ስሙኝማ…አንዱ ጓደኛውን…
“በአንድ ወቅት የአንተን የሚመስል አይነት ጢም ነበረኝ፣ እንዴት አስጠሊታ እንዳደረገኝ ሳይ ተላጨሁት” ይለዋል፡፡ ያኛውም ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው…
“በአንድ ወቅት አንተን የሚመስል ፊት ነበረኝ፣ እንዴት አስጠሊታ እንዳደረገኝ ሳይ ጢሜን አሳደግሁት፡፡” እናማ ምን ለማለት ነው… ሁልጊዜ ብልጥነት እናንተ ዘንድ ብቻ ያለ የሚመስላችሁ የፖለቲካችን ድንኳን ሰባሪዎች ንቁ እንጂ! ባቡሩ አንዴ ከሄደ መቼ ተመልሶ እንደሚመጣ አይታወቅምና!
እንደ ዘንድሮው አያያዛችን ሰርግ መደገስ አንችልም፡፡ “ኸረ ሚዜው ድሀ ነው ሽቶው ውሀ ነው” የሚለው ስንኝ ሀገር ሊንጥ ይችላል:: “አናስገባም ሰርገኛ ደጅ ይተኛ” የተባለ ሚዜ፤ “መብታችን ተነካ” ብሎ አጃቢዎችና ዘመድ አዝማዶቹን ሊሰበስብ ይችላል፡፡
ባላሳየነው ፍሬቻ፣ ‘ነገር’ እየተጠመዘዘ ተቸገርንማ!
የምር ግን፣ በዕለት ተዕለት ማህበራዊ መስተጋብራችን መግባባት የራቀን ሲመስል መልካም አይሆንም፡፡ ለችግሩ ምክንያቶቹ እኛው ራሳችን መሆናችንን ክደን ሰበብ እንፈጥራለን:: አለ አይደል…የሆነ ራቅ ያለንን፣ ልናገኘው የሚቸግረንን ነገር  ‘ታሪክ’ እንፈጥርለታለን፡፡
“ስማ ሁሌ ምስሩን፣ ድንቹን ምናምኑን ነው ስትበላ የማይህ፡፡ ለለውጥ ያህል በአሥራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ እንኳን ለምን ስጋ አትበላም?” ሲሉት ምን ሊል ይችላል መሰላችሁ…
“ሥጋ መብላት ቶሎ ያስረጃል አሉ” አሪፍ አይደል! “ደህና ኪሎ ስጋ እኮ ሦስት መቶ ገብቷል!” ብሎ ነገር የለ… “በእኔ ደሞዝ አይደለም ስጋ ልገዛ፣ የሥጋ ስእል ያለበት መጽሄት እንኳን መግዛት አልችልም” ብሎ ነገር  የለ…በቃ “ያስረጃል” ተብሏል… ያስረጃል! አሪፍ አይደል!
እግረ መንገድ፣ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… አንድ አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤት ከእንግዲህ ወርሀዊ ሂሳቡን በጊዜ ገቢ ካላደረጋችሁ ዝም ብሎ ቅጣት ሳይሆን ወለድ እየታሰበ ነው ቁጭ የምታደርጉት አይነት ብሏል፡፡ የአገልግሎት ሂሳብን በጊዜ ማስከፈሉ ጥሩ ነው፤ ለሰጪውም፣ ለወሳጁም፡፡ ግን በዛ ሰሞን የአገልግሎት ለመክፈል በየወሩ ስንንገላታ የነበረውስ! በፀሀይና በቁር ስንጉላላ የነበረውስ! ቢያንስ ለዚህ ትልቅ ይቅርታ ልንጠየቅ አይገባም ነበር እንዴ!
ደግሞ ሌላም አለ…ያለፈው ጭማሪ ገና እያመሰን እያለ ከታህሳስ ጀምሮ እንደገና ይጨመራል እያሉ ነው መብራቶች፡፡ “ምን ማድረግ ይቻላል!” ይሉ የለ ወጣቶቹ!… ቀደም ባሉ ጊዜያት እኮ የመብራት ሰዎቻችን፣ በዓለም ዋንጫ ጊዜ መብራት እንደማይቋረጥ በመገናኛ ብዙኃን ማረጋገጫ ይሰጡን ነበር፡፡ አዎ፣ እዚቹ እኛይቱ ሀገር፣ እኛይቱ ከተማ… “በዓለም ዋንጫ ሰሞን መብራት እንደማይቋረጥ መብራት ኃይል አስታወቀ” አይነት ቃና ያላቸው መልዕክቶች ይተላለፉ ነበር፡፡ “ነበር እንዲህ ሆኖ ሊቀር” የሚሉት ነገር አለ አይደል! አሁን ደግሞ ሌላ ጭማሪ፡፡
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
ነዋሪሽ ወደታች ዋጋሽ ወደላይ…
የሚል ‘ሲንግል’ ልንለቅ እንደምንችል ግንዛቤ ይያዝልንማ፡፡ ኸረ እንተሳሰብ!
እናላችሁ…አለ አይደል…አንድ ናሺፍ ለሦስት የሚበላበት ዘመን ቀረና፣ አሁን አንዱ ሌላኛውን ‘ናሺፍ’ የሚያደርግበት ዘመን መጣ፡፡ (ናሺፍ በምን ነበር የሚሠራው?) እኛ በምናገኘው ከምንደሰተው በላይ፣ ሌላው በማጣቱ ጮቤ የምንረግጥበት ዘመን፡፡
ሰው ሲለፋ ወጥቶ ወርዶ
ከደስታ ነፍሱን ጋርዶ
ጥሮ ግሮ ሲበረታ
ያለብሱታል የሀሜት ኩታ
ነገ እኮ…አለ አይደል… “እንትን የተባለ ሰፈር በሆነ ጉዳይ ግማሹ አገልግሎት ሲያገኝ ግማሹ እያገኘ አይደለም” ቢባል…በተለመደው የሦስተኛ ዓለም ፖለቲካ ባህል መሰረት፣ የሆነ ጭቃ ሹም ቢጤ… “ይህ አስተያየት የተሰነዘረው በነዋሪዎች መሀል ጥርጣሬን ለመፍጠርና እርስ በእርስ ለማጋጨት ሆነ ተብሎ ነው…” አይነት የ“ነብር አየኝ በል” ክስ ሊያቀርብ ይችላል፡፡
ባላሳየነው ፍሬቻ፣ ‘ነገር’ እየተጠመዘዘ ተቸገርንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2505 times