Saturday, 26 October 2019 12:34

የሰው ልጆች ዐቅም

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 የሰው ልጆች በሕይወት ውስጥ የሚጓዙበት ውጣ ውረድ “በነባሩ የድርጊትና ምላሽ የፊዚክስ አስተሳሰብ የሚመራ ነው” የሚሉ በአንድ በኩል፤ እንዲሁም የሰው ልጆች “ዕጣ ፈንታቸውን በነጻ ፈቃዳቸው የሚወስኑ ነጻ ፍጥረታት እንጂ በማሽን ሕግ የሚተዳደሩ የአካባቢያቸው ባሪያዎች አይደሉም” የሚሉ በሌላ በኩል በሰው ልጅ ዐቅም ዙሪያ የቆየ ክርክር አላቸው፡፡ የሰው ልጆች “ነጻ ፈቃድ የላቸውም” የሚሉ ሰዎች የሰው ልጆችን ወይ በሥነ ሕይወታዊ ዕይታ የሚመለከቱ አልያም ደግሞ በአካባቢያቸው ተጽዕኖ ሥር ይወድቃሉ የሚሉ ናቸው፡፡
የሰው ልጆች ዕጣ ፈንታ “በሥነ ሕይወታዊ ዐቅማቸው” ላይ የተወሰነ ነው የሚለው የሥነ ሕይወታውያን ዕይታ “ሰዎች በተፈጥሮ ይዘውት የተወለዱት ነገር ይመራቸዋል” የሚል አስተሳሰብ አለው፡፡ ሰዎች “በተፈጥሮ የታዘዘላቸውን ወይም እንዲሆኑ ተደርገው ይዘውት የመጡትን ሊቀይሩት ፈጽመው አይችሉም፤ ያንኑ ይዘውና በዚያው ተመርተው መኖር አለባቸው” ብሎ ያስተምራል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በሰው ልጆች የረጅም ጊዜ ታሪክ ውስጥ ሰፊ ሥፍራ የያዘና አሁን ኋላቀር አድርገን ለምንቆጥራቸው አስተሳሰቦች መሠረት የጣለ ነው፡፡
የተለያዩ ቡድኖችን ልዩነት ሥነ ሕይወታዊ ትርጉም በመስጠት ቡድኖቹ ለእኩልነት የሚያደርጉትን ትግል ለማቀጨጭ ትልቅ መሣሪያ ሆኖ ያገለገለ ዕይታ ነው፡፡
ለምሳሌ የጥቁር ሕዝቦችን የመብት ትግል ለማኮላሸት ሲንቀሳቀስ የነበረው የነጭ አክራሪነት መንፈስ ዋነኛ መነሻው ነጮችን በተፈጥሮ ከጥቁሮች የበለጡ አድርጐ ማሰብ ነው፡፡ አሁንም ድረስ በአካዳሚያዊ ጽሑፎች ሳይቀር ይህንን ከሳይንስ ውጭ መሆኑ የተረጋገጠውን የሥነ ሕይወታዊ ልዩነት ተረክ የሚያራግቡ ምሁራን አሉ፡፡
በተመሳሳይ የሴቶች የመብት ትግል ዋናው ፈተና ሴቶች በተፈጥሯቸው ከወንዶች ያነሱ ናቸው የሚልና በሴቶችና በወንዶች መካከል የሚታየውን ሁለንተናዊ ልዩነት በተፈጥሮ የሚያሳብብ አስተሳሰብ ነው፡፡
ይህ የሰው ልጆችን ዕጣ ፈንታ ለተፈጥሮ የሚሰጥና ዕጣ ፈንታቸውን በራሳቸው ጥረት እንዳይለውጡ የሚያደርግ ዕይታ በአሁኑ ጊዜ እየተሸነፈ መጥቷል፡፡ የዕይታው ሌላ ገጽ ደግሞ የሰው ልጆች ማንነትና ዕጣ ፈንታ ከአካባቢያቸው ጋር በሚያደርጉት “የድርጊትና ምላሽ ሂደት የሚፈጠር እንጂ በሰው ልጆች ሐሳብና ፍላጐት የሚፈጠር አይደለም” የሚል ነው፡፡ ሐሳቡ “የሰው ልጆች የአካባቢያቸው ባሪያዎች ናቸው” የሚል አመለካከት አለው፡፡ ይህም ማለት የአንድን ሰው ባሕርይ የሚወስነው አካባቢው በእሱ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ እንጂ የእሱ የራሱ ምርጫ አይደለም ማለት ነው፡፡
በተቃራኒው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ “የሰው ልጆች ዕጣ ፈንታቸውን በራሳቸው የሚገነቡ ፍጥረታት ናቸው” የሚለው አስተሳሰብ እያየለ መጥቷል፡፡ አብዛኞቹ የሰው ልጅ የሚገኝባቸው ማህበራዊ እውነታዎች ራሱ የገነባቸውና በጊዜ ሂደትም ራሱ የገነባቸውን ነገሮች እንደ ውጫዊ ሕግ የሚመለከትበት ሁኔታ ተፈጥሯል የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ምንም እንኳን በግለሰቦች መካከል ተፈጥሯዊ ልዩነቶች እንዳሉ ሳይንስ ያመነበት ቢሆንም ማኅበራዊ የቡድን ልዩነቶችና የሕዝቦች ኋላቀርነት ግን በማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥሪቱ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያትታል፡፡ ይህም የሰው ልጆች ሕይወታቸውን የመቀየር ችሎታ በእጃቸው ነው የሚል አስተሳሰብ ነው:: ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የግለሰቦች የአእምሮ ብቃት ሳይቀር በግለሰቦች ፍላጐትና ጥረት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚያትቱ ሐሳቦች እየበዙ ነው፡፡ ይህም የሰው ልጆች ዕጣ ፈንታ በነጻ ፈቃዳቸው ላይ የተመሠረተ ነው የሚለውን ሐሳብ ያጐላዋል፡፡
በመደመር ፍልስፍና መሠረት የሰው ልጆች ነጻ ፈቃድ በየጊዜው እያደገ የሚሄድና በዕድገቱ ውስጥም የዕውቀትና የሥነ ልቦና ኃይል እያዳበረ የሚሄድ ነው፡፡ የሰው ልጆች ጉዞም ነጻ ፈቃዳቸውን እያጠነከሩ ከአካባቢና ከተፈጥሮ ባሪያነታቸው ነጻ እየወጡ የሚመጡበት ሂደት ነው፡፡ ስለዚህም የሰው ልጆች ነጻ ፈቃድ ቀደም ብለው በሠሩት ሥራ ላይ የሚመሠረት ነው:: ይህም ማለት ትናንት የሠሯቸው ሥራዎች ለቀጣይ ሥራቸው መነሻ ወረት ይሆናቸዋል ማለት ነው፡፡
ሰዎች ነጻ ፈቃድ አላቸው፡፡ ነጻ ፈቃዱ ግን ሙሉ ፈቃድ አይደለም፡፡ ተፈጥሮን እያሸነፉ በመጡ ቁጥር ነጻ ፈቃዳቸው እየጐለበተ ይመጣል፡፡ ሆኖም ይህ እየጐለበተ የመጣው ነጻ ፈቃድ ተፈጠሮን ቢያሸንፉም የራሳቸው የእጅ ሥራ መልሶ ራሳቸውን የሚያሸንፋቸውና ነጻ ፈቃዳቸውን የሚወስንላቸው እየሆነ መጥቷል:: ለምሳሌ ቴክኖሎጂ በሰው ልጆች አጠቃላይ ሕይወት ላይ፤ እያመጣ ያለው ተጽእኖ ከተፈጥሮ በላይ የሰው ልጆችን ነጻ ፈቃድ የሚፈታተን ነው፡፡
የሰው ልጆች ነጻ ፈቃድ አላቸው ስንል ባሕርያቸው ከአካባቢያቸው ጋር በሚደረግ ድርጊትና ምላሽ አይወስንም እያልን አይደለም:: የሰው ልጅን የከበቡት ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ነገሮች በሰው ልጅ ባሕርይ ላይ አሻራቸውን ያሳርፋሉ፡፡ ከዚህም አንጻር የሰው ልጅ ራሱ የሚዘረጋው መዋቅር የራሱን ባሕርይና ሕይወት የሚቀርጽ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ከአካባቢው የሚማረው በንፁህ የድርጊትና ምላሽ የፊዚክስ ሕግ ሳይሆን ንቁ አእምሮውን በመጠቀም ነው፡፡ ስለዚህም ከአካባቢው የሚማረውን የመምረጥና የመተርጐም እንዲሁም የማሻሻል ተፈጥሯዊ ብቃት አለው ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት የሰው ልጅ የፖለቲካ መዋቅሮች እንደፈለጉ የሚያሾሩት ግዑዝ ነገር ሳይሆን የፖለቲካ መዋቅሮችን የሚተረጉምና የሚጠመዝዝ ንቁ አእምሮ አለው ማለት ነው፡፡ ይህም በተቋማት ግንባታ ላይ ብቻ የተንጠላጠለው የሊበራሊዝም አስተሳሰብ ሩቅ እንደማያስጉዝ ያመለክተናል፡፡
የሰው ልጅ በብዙ ነገሮች እየተራቀቀ ከመጣበትና አሁን ከደረሰበት የሥልጣኔ ሠገነት ላይ ቢገኝም ቅሉ የሰው ልጆች ፍላጐት አሁንም በአግባቡ በተሟላ መልኩ እየተመለሰ አይደለም፡፡ አሁንም የሰው ልጆች በረሃብ ይረግፋሉ፡፡ አሁንም በመድኃኒትና በሕክምና እጦት ይማቅቃሉ፡፡ አሁንም እርስ በርሳቸው የሚገዳደሉና ኑሯቸው ከተዘዋዋሪ አደን ያልተላቀቀ ነው፡፡
የሰው ልጆች ሥልጣኔ ስለምን ቡራቡሬ ሆነ? የአንዱ ፍላጐት ሲሟላ የሌላው ፍላጐት ስለምን ጦሙን ያድራል? በዚህ ሁሉ የሥልጣኔ ገድል መካከል መከራና ሰቀቀን፣ ሞትን ቁስለት፣ እንባና እሪታ እንዴት በዚህ መጠን የዓለማችን የዘወትር እውነታዎች ሆኑ? በርካታ ምሁራን በሰው ልጆች መካከል ስላለው የሥልጣኔ ወይም የልማት ደረጃ ልዩነት ከተፈጥሮ ጸጋዎች፣ ከአመራር ብቃት፣ ከመንግሥት ባሕርይ፣ ከባህል፣ ከተቋማት ዐቅም፣ ከዓለም አቀፍ ግንኙነትና ቅኝ ግዛት ጋር የተያያዙ በርካታ መንሥኤዎችን ቢያስቀምጡም በመነሻነት ይህ የሥልጣኔ ልዩነት ጥያቄ የሰው ልጆችን ተፈጥሮ በተመለከተ ሌላ ክርክር የሚያስነሳ ነው፡፡
በአንድ በኩል የሰው ልጅ ስግብግብ፣ ራስ ወዳድ፣ ተፎካካሪ እና ጠበኛ ፍጥረት ነው የሚለው ዕይታ እና በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጅ በመሠረቱ መልካም፤ ተባባሪ፣ እና ለሌሎች አሳቢ ፍጥረት ነው የሚለው ዕይታ የክርክር አጀንዳ ፈጥሯል፡፡
ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሥነ ሕይወትና የሥነ ዝግመት ሊቃውንት ጦርነቱ በፈጠረባቸው ተጽእኖና ሽብር ምክንያት “የሰው ልጅ ጨካኝና አደገኛ ፍጥረት ነው” የሚል ሐሳብ አምጥተዋል፡፡ የሰው ልጅ ከሌሎች እንስሳት ቀድሞ የሰለጠነበት ምክንያትም “በከፍተኛ ጭካኔው አካባቢውን እየተቆጣጠረ በመምጣቱ ነው” ይላሉ፡፡ ይህ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የተጀመረ አስተሳሰብ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲከሰት ይበልጥ ተጠናክሮ የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ ሆነ:: በአንጻሩ በዓለም ላይ የኮምዩኒዝም ርእዮተ ዓለም እየሠፈነ ሲመጣ የሊቃውንት ቀልብ በሰው ልጆች የትብብርና የመልካምነት ተፈጥሮ ላይ እያተኮረ መጣ፡፡
ከፉክክር ይልቅ ትብብርን የሰው ልጅ ተፈጥሮ አድርጐ መቁጠር ተጀመረ፡፡ ኮሙኒዝምን የሚተቹ ሊቃውንት ደግሞ በተቃራኒው “ኮሙኒዝም የሰው ልጆችን የራስ ወዳድነትና የፉክክር ተፈጥሮን የዘነጋ ነው” በሚል ሐሳባቸውን መሰንዘር ጀመሩ፡፡ ውሎ አድሮም የሊበራሊዝም አስተሳሰብ ተቀባይነቱ እየሰፋ ሲመጣ የሰው ልጆችን ስግብግብ፣ ራስ ወዳድና ተፎካካሪ ፍጥረታት እንደሆኑ የሚቆጥረው አመለካከት የበላይነት እያገኘ መጣ፡፡ በዚህ የሰው ልጅ ተፈጥሮን በመበየን ሂደት ውስጥ የሚስተዋለው ዋናው ችግር ብያኔው ከርእዮተ ዓለም የሚቀዳ መሆኑ ነው፡፡ መሆን የሚገባው ግን በተቃራኒው ነበር፡፡ ስለሰው ልጅ ተፈጥሮ ያለንን ዕይታ በነጻ አእምሮ ከመዘንን በኋላ ርእዮተ ዓለማችንን ብንቀርጽ የበለጠ ትክክል እንሆን ነበር፡፡
ጋሪውን ከፈረሱ በማስቀደማችን ምክንያትም በሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ የምንሠነዝራቸው ድምዳሜዎች ርእዮተ ዓለማችንን ተመራጭ ለማድረግ የሚደረግ መቅበዝበዝ ሆነ፡፡
የሰው ልጆች ተፈጥሮ ለበጐነትም ለክፋትም፣ ለፉክክርም፣ ለትብብርም፣ ለራስ ወዳድነትም፣ ለሰው አሳቢነትም፣ ለጠበኝነትም ለሰላማዊነትም ክፍት የሆነና በየትኛውም አቅጣጫ የማደግ ዕድል ያለው ነገር እንጂ በአንድ ጽንፍ ላይ የሚቆም ነገር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ የምጡቅ አዕምሮ ባለቤት ነው፡፡ ይህን ምጡቅ አእምሮውን ለበጐነትም ለክፋትም ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ለበጐነት ሲጠቀምበት በዓለማችን በበጐነታቸው እንደሚጠቀሱት መልካም ሰዎች፤ ለክፋት ሲጠቀምበትም በክፋታቸው መጠን እንደሚጠፉት ክፉ ሰዎች ሊሆን ይችላል፡፡
በመደመር ዕይታ መሠረት የሰው ልጅ የፉክክርም ሆነ የትብብር፣ የጠበኝነትም ሆነ የሰላማዊነት ዝንባሌው በእጁ ላይ ነው፡፡ የሚፈልገውን ባሕርይ መገንባትና የማጠናከር ዐቅሙ አለው፡፡ ወጣ ገባ ብሎ የበሰለው የሰው ልጅ ሥልጣኔ የእያንዳንዱን ሰው ፍላጐት በማሟላት ሙሉ በሙሉ የበሰለ እውነተኛ ሥልጣኔ እንዲሆን ይኸን የሰው ልጆች ዐቅም መገንዘብ የግድ ይላል፡፡      

Read 3364 times