Print this page
Saturday, 26 October 2019 12:47

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም ቀዳሚ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

     “ሽልማታችን የኢትዮጵያ ነው” - ዳግማዊት አማረ

           ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ The Challenge Awards ላይ በጎዳና ላይ ሩጫ ዝግጅት ዘርፍ በአለም ቀዳሚ ሆኖ በመመረጥ ልዩ ሽልማት ተቀብሏል፡፡  ሰሞኑን ይህን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የተገኘው ሽልማት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ከአለማችን ስኬታማ የውድድር አዘጋጆች ጎራ እንደሚያሰልፈው የሀገራችንን ስም በበጎ የሚያስነሳ ሌላ ትልቅ ብሔራዊ ሀብትም የሚያደርበው መሆኑን አስታውቋል፡፡ ለዚህ ዓለም አቀፍ ስኬት እውን መሆን በተለያየ መንገድ ሰዎች ድምጽ እንዲሰጡ የጋበዙ፤ ጥሪ ያቀረቡና ያመቻቹትን እንዲሁም በድሉ የተደሰቱትንም ሁሉ በእጅጉ አመስግኗል፡፡
 ዘ ቻሌንጅ አዋርድን The Challenge Awards የሚያዘጋጀው ሌትስ ዱ ዚስ (Let’s Do This) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የድረገፅ ምዝገባ አገልግሎት ሲሆን የሽልማቱ አቅራቢ ደግሞ በከፍተኛና ልዩ የአትሌቲከስ ባለሙያዎች የተደራጀው ታዋቂው ራነርስ ዎርልድ  መፅሄት ነው፡፡ በዓለም የሩጫ ስፖርት ኢንዱስትሪ የኦስካርን ያህል ክብርና ግምት የሚሰጠው ሽልማቱ በመላው ዓለም የሚካሄዱ ፈታኝ የስፖርት ውድድሮችን የሚያዘጋጁ፤ ጎን ለጎን የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎችን የሚያከናውኑ  ማህበረሰቦችና ግለሰቦችን በልዩ መስፈርቶች አወዳድሮ እውቅና ይሰጥበታል፡፡   ዘንድሮ የሽልማት ስነስርዓቱ በእንግሊዝ ዌስት ኪንግስተን ውስጥ በሚገኘው Queens Club የተካሄደ ሲሆን፤ በስፖርቱ አለም ከፍ ያለ ስም ያላቸው ዝነኞች ስፖርተኞች እና እውቅ የውድድር አዘጋጆች እንዲሁም ሌሎች እንግሊዛዊያን ዝነኞች ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በማራቶን የቀድሞዋ የአለም ሻምፒዮን ፓውላ ራድክሊፍ፤ የፓራ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎቹ ሳራ ስቶሪ እና ታኒ ግሬይ ቶምሰን እንዲሁም የቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ ሪዮ ፈርዲናንድ ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር ፍሰሀ ሻውል ገብረ እና የህዝብ ዲፕሎማሲ ሃላፊ አቶ መኮንን አማረ እንዲሁም የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  የቀድሞ ስራ አስኪያጅ እና በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ልዩ አማካሪ ሆኖ የሚሰራው ሪቻርድ ኔሩካር የሽልማት ስነስርዓቱ ታዳሚዎች ነበሩ፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዘ ቻሌንጅ አዋርድ ላይ “Best International Running Event” በሚል ያሸነፈውን ልዩ ሽልማት በስፍራው በመገኘት የተቀበለችው ደግሞ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስትራቴጂክ እና የኢኖቬሽን ማናጀር  ዳግማዊት አማረ  ናት፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዘ ቻሌንጅ አዋርድ ላይ በተወዳደረበት ዘርፍ ያሸነፈው ከተሰጠው ድምፅ 56 በመቶውን በማግኘት ነው፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በመከተል በቢዮንድ ኢቨንትስ የሚዘጋጀው የሳንዲያጎ ቢች ኤንድ ቤይ ማራቶን  በ24 %፤ በማስኮት ስፖርትስ የሚዘጋጀው ቤይ ብሪጅ ሃልፍ በ10 %፤ የኦፕአፕ ሊማሶል ማራቶን በ3% እና የሳንፍራንሲስኮ ማራቶን በ1% እስከ አምስትኛ ደረጃ አከታትለው ወስደዋል፡፡ ለሽልማቱ በእጩነት ከቀረቡት መካከከል ታዋቂዎቹ የኒውዮርክ፤ ቦስተንና ቺካጎ ማራቶኖች ጨምሮ ሌሎችም በሰሜን አሜሪካ እና በእንግሊዝ የሚካሄዱ ትልልቅ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮችና ማራቶኖች ይገኙበታል፡፡ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ 18 ዓመታትን ያስቆጠረው ውድድሩ 45ሺ ተሳታፊዎችን በመያዝ በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ መሆኑ፤ አስደሳኝ እና በቀለማት ያበበ እንዲሁም የኢትዮጵያ ግዙፉ የጎዳና ላይ ፓርቲ መሆኑ እየተጠቀሰ ከፍተኛ አድናቆት አግኝቷል::
ላለፉት 15 ዓመታት በድርጅቱ በተለያዩ የሃላፊነት ድርሻዎች ስታገለግል  የቆየችውንና በአሁኑ ወቅት የስትራቴጂክ እና የኢኖቬሽን ማናጀር ከሆነችው ዳግማዊት አማረ ጋር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያሸነፈውን ሽልማት  አስመልክቶ ይህን ልዩ ቃለምልልስ ለስፖርት አድማስ ሰጥታለች፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለዘ ቻሌንጅ አዋርድ ውድድር የበቃው እንዴት ነው?
ለዘ ቻሌንጅ አዋርድ The Challenge Awards  ለመወዳደር የበቃነው በሚያስገርም ሁኔታ ነው፡፡  የሽልማቱ አዘጋጆች በመጀመርያ በራሳቸው የግንኙነት መረብ ተጠቅመው በዓለም ዙርያ የሚገኙና በተለያዩ ስፖርቶች ተወዳጅ ውድድሮች የሚያዘጋጁትን ተቋማት በመለየት  የመረጡበትን አሰራር ተከትለዋል::  በዚሁ መንገድ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  Best International Running Event በሚለው ዘርፍ ለመታጨት ከበቁት 20ዎቹ ምርጥ የስፖርት ውድድሮች ተርታ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መግባቱን  ከሽልማቱ አዘጋጆች በኢሜል በደረሰን መልዕክት ነው ያረጋገጥነው:: ይህ ልዩ መልዕክት በኢሜል አድራሻችን ሲደርስ በጀርመን አገር ለጉብኝት ሄጄ ነበር፤ እጩ መሆናችንን በመመልከቴ ብቻ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ ምክንያቱም በመላው ዓለም በሚገኙ ስፖርት አፍቃሬዎች ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚታወቅ መሆኑን ስለሚያመለክት ነው፡፡ የሽልማቱ አዘጋጆች Best International Running Event በሚለው ዘርፍ እጩ መሆናችንን ሲያሳውቁን አሸናፊ የሚመረጠው በድረገፅ በሚሰጠው ድምጽ መሰረት መሆኑን ገለፁልን፡፡ በወቅቱ ልናሸንፍ ባንችልም እጩ ሆነን ስንቀርብ ኢትዮጵያን ወክለን በመሆኑ አስደስቶናል፡፡ በሩጫ ስፖርት ዓለም አቀፍ ተዓማኒነት ባለው ራነርስ ዎርልድ   መፅሄት የጎዳና ላይ ሩጫችን ልዩ ትኩረት ሊያገኝ መብቃቱ ብቻ ከሽልማቱ በፊት ለእኛ እንደድል የሚቆጠር ነበር፡፡
ዓለም አቀፉን ሽልማት  መቀዳጀቱ ምን ውጤትና ትርጉም ይኖረዋል?
በመጀመርያ ደረጃ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትኩረት ማግኘት የጀመረው የእጩዎች ዝርዝር ይፋ ከሆነበት ቀን አንስቶ ነው፡፡ እንግዲህ  በተለያዩ ዘርፎች ለመወዳደር ለቀረቡት እጩዎች ድምፅ የሰጡት ከ86ሺ በላይ መሆናቸውን የሽልማት ስነስርዓቱ ላይ አዘጋጆች የገለፁ ሲሆን፤ በተወዳደርንበት ዘርፍ 56 በመቶውን የድምፅ ድርሻ በመውሰድ ማሸነፋችን ልዩ ትኩረት እንዳገኘን ያመለክታል:: ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ውድድር እንደማዘጋጀታችን እንኳን የሽልማቱ ቀን ደርሶ  አይደለም፤ በውድድሩ ከእጩዎች ተርታ መግባታችን በዓለም ዙርያ ስለ ጎዳና ላይ ሩጫው ብዙ ሰው እንዲያውቅና ትኩረት እንድናገኝ አስችሎናል፡፡ ሽልማቱን በማሸነፋችን እንደአዘጋጅ ትልቅ ብርታት የሚሰጠን የሚጨምርልንም ነው፡፡ በእውነቱም ጥሩ ነገር እየሰራን እንደነበር እንድናስብ ያደርጋል፡፡
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ በጎዳና ላይ ሩጫ ብቻ ሳይሆን፤ በማራቶን፤ በዋና ፤ በብስክሌት፤ በትራያትሎንና በሌሎች ስፖርቶች አዘጋጅነት የሚሰሩት ከዓለም ዙርያ በመሰባሰባቸው ለብዙዎቹ እንደአዲስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ያስተዋወቅንበትን እድል ፈጥሮልናል፡፡ በዓለም አቀፍ የውድድር ዝግጅት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ስለ ጎዳና ላይ ሩጫው በማወቃቸው አድናቆታቸውን ገልፀውልናል፡፡ ከተለያየ አገራት ስነስርዓቱን ታድመው ከነበሩት መካከል አፍሪካ ውስጥ ከ45ሺ በላይ ተሳታፊዎች ያሉት የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር መኖሩን ማወቃቸው አስገርሟቸዋል፡፡ በውድድሩ ላይ ለማሳተፍ ጉጉት የተፈጠረባቸውም ነበሩ፡፡
የሽልማት ስነስርዓቱ በሁለት የተለያየ ምድብ ማለትም በእንግሊዝ ብቻ የሚካሄዱና በመላው ዓለም በሚከናወኑ ውድድሮች ተከፋፍሎ የተካሄደ እንደመሆኑና የመጀመርያው ተሸላሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሸነፈው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሆኑ በበርካታ በተለይ በዩናይትድ ኪንግደም ውድድር በሚያዘጋጁት አካላት በልዩ ሞገስ እንድንታወቅ አድርጎናል፡፡ ለምሳሌ ያህል እኛ ስነስርዓቱን በታደምንበት ጠረጴዛ ላይ ከአሜሪካ እኛን በተከታታይ ደረጃዎች የተፎካከሩን የሩጫ ውድድር አዘጋጆችና ከአውስትራሊያ ደግሞ የትራይትሎን ውድድር የሚያዘጋጁ አብረውን ነበሩ፡፡
ሽልማቱ ምንድነው? ለወደፊቱስ ምን አዲስ ነገር ሊፈጥር ይችላል?
የተቀበልነው ሽልማት Best International Running Event የሚል ዋንጫ ሲሆን የገንዘብ ሽልማቱ ደግሞ 1000 ፓውንድ ነው፡፡ በእኛ በኩል ካገኘነው ዓለም አቀፍ እውቅና ባሻገር በጣም ያስደሰተን በተካሄደው ምርጫ ላይ ብዙዎች ድምፅ በመስጠት በከፍተኛ ደረጃ ድጋፋቸውንና  አድናቆታቸውን ማሳየታቸው ነው፡፡ በዘንድሮ የቻሌንጅ አዋርድ በጎዳና ላይ ሩጫ ዝግጅት ዘርፍ በአለም ቀዳሚ ሆነን በመመረጣችን በተጨማሪ ያገኘነው እድል በራነረስ ዎርልድ መፅሄት ወደፊት በሚወጣ ልዩ እትም ላይ በሙሉ ገፅ ስለውድድራችን በነፃ ማስተወዋቅ  ነው፡፡ ይህን ሽልማት ምክንያት በማድረግ በዘንድሮው ውድድራችን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሩጫ ስፖርትና ውድድር ተፅእኖ የሚፈጥሩ ልዩ እንግዶችን ለማስተናገድ እየተዘጋጀን ነው፡፡
 በአጠቃላይ ያገኘነውን ሽልማት በዘንድሮ ውድድር ሳይሆን በቀጣይ ዓመት በምናዘጋጀው 20ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ በዓለም አቀፍ ዙርያ የላቀ ትኩረት በመሳብ እና በማህበራዊ ሚዲያ ልዩ ስትራቴጂ በመዘረጋት ልንሰራበት አስበናል፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በኩል ሃሳባችን በራነርስ ዎርልድ መፅሄት ላይ ያገኘነውን እድል ከ20ኛው ውድድራችን ጋር  አያይዘን ልንጠቀምበት ነው፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ የክብር ሽልማት ሲያገኝ የመጀመርያው አይደለም፡፡ በ2013 የመጀመርያውን የAIMS Social Award  የማህበረሰብ አዋርድ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ይህንን ሽልማት በስፍራው በመገኘት አንቺው መቀበልሽንም አስታውሳለሁ…ለወደፊትስ ሌሎች ለማሸነፍ የምትፈልጓቸው ሽልማቶች አሉ
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር AIMS አባል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኤይምስ AIMS በየዓመቱ የውድድር አዘጋጆች በሚያቀርቡት ማመልከቻ መሰረት ለአባል የማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫ አዘጋጆች በሁለት ዘርፎች አወዳድሮ የሶሻል እና የግሪን አዋርዶችን በማዘጋጀት ይሸልማል፡፡ ይህን ሽልማት በድጋሚ ለማሸነፍ ነው የምንፈልገው፡፡ ከ6 ዓመታት በፊት ዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫ ማህበር በግሪክ አቴንስ ባዘጋጀው የሽልማት ስነስርዓት ላይ የAIMS Social Awardን አሸንፈን ነበር፡፡  ያኔ ሽልማቱን ስረከብ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማንኛውንም ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ በማከናወን ሰፊ ልምድ እያገኘን እንደመጣን፤ ከምናዘጋጃቸው ውድድሮች ስኬታማነት ባሻገር በተያያዥ የምናስታልፋቸው መልዕክቶች እና መርሆች ውጤታማ እንደሆንን አረጋግጠናል፡፡

      የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስትራቴጂና ኢኖቪሽን ማናጀር ዳግማዊት አማረ Best International Running Event ሽልማቱን ከተረከበች በኋላ በመድረኩ ላይ ባሰማቸው ንግግር
“ ሁላችሁም ጥቁር የለበሳችሁበት ምክንያት የሽልማት ስነስርዓቱን አለባበስ በማክበር ሊሆን ይችላል፡ እኔ ግን ሙሉ ነጭ ለብሼ ከፊታችሁ ቆምያለሁ፡፡ የለበስኩት የአገሬን የባህል ልብስ ነው፡፡ ለተሰጠን ሽልማት በጣም እናመሰግናለን:: ይህ ለእኛም ለኢትዮጵያውያንም ክብር ነው፡፡ በእርግጥ ሁላችሁም ኢትዮጵያ የረጅም ርቀት ሯጮች አገር መሆኗ ታውቃላችሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በጥንታዊ ስልጣኔ እና ታሪክ ውስጥ የቆየች፤ የዳበረ ባህል ያላት እና ከዓለማችን ብዙ ልዩ የሚያደርጓት ሁኔታዎችን ያቀፈች ናት፡፡... Let’s do this ይህን የሽልማት ስነስርዓት በማዘጋጀት ልዩና በዓለም ቀዳሚ ያደረገንን ሽልማት ስለሰጠን እናመሰግናለን፡፡ አዎ! ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጀው ውድድር አስደሳች ነው፡፡ በየዓመቱ ሺዎችን  በማሳተፍ በሆታ፣ በዜማና በጭፈራ በዳንስ ታጅቦ ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያዊ መንፈስ የሚንፀባረቅበት ነው፡፡ …ወደ ኢትዮጵያ መጥታችሁ በውድድራችን እንድትሳተፉ እጋብዛለሁ፡፡  ሽልማታችን የኢትዮጵያ ነው” ብላ ተናግራለች፡፡


Read 1010 times