Print this page
Saturday, 02 November 2019 12:16

የአማራ ክልላዊ መንግስት በአራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ለብሮድካስት ባለሥልጣን ቅሬታ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

   ኦኤምኤን በአምስት ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠየቀ

           የአማራ ክልላዊ መንግስት በኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) በኦሮሚያ ኒውስ ኔትዎርክ (ONN)፣ በትግራይ ቴሌቪዥንና በድምፂ ወያኔ (DW) ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ለብሮድካስት ባለስልጣን ቅሬታ ማቅረቡ ታውቋል፡፡
ከክልሉ ለቀረበውም ቅሬታ በተለይ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) በአምስት ቀናት ውስጥ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጥ ባለሥልጣኑ ጠይቋል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም ለብሮድካስት ባለስልጣን በፃፈው ደብዳቤ፤ የኦሮሚያ ኒውስ ኔትዎርክ (OMN) ከሚዲያ ስነምግባርም ሆነ ከአገሪቱ የብሮድካስት ህግ ውጪ በሆነ አግባብ በአማራ ክልል ህዝብና መንግስት ላይ ጥላቻን የሚቀሰቅስ፣ የእርስ በእርስ እልቂት የሚሰብክና መሬት ላይ ካለው ሃቅ ፈጽሞ የራቁ የተዛቡ መረጃዎችን አሠራጭቷል ሲል ከስሷል፡፡  ድርጊቱ ለመፈፀሙም መስከረም 25 እና 27 ቀን 2012 የተሠራጩ “ሶና ሴና” የተሰኙ ፕሮግራሞችን እንዲሁም መስከረም 21 ቀን 2012 ዓ.ም የተሠራጩ “ዶ/ር ቀዲዳ ሾው” የተሰኘ ፕሮግራምን ቅጂ የክልሉ መንግስት በማስረጃነት ማቅረቡ ተጠቁሟል፡፡
በእነዚህ ቅሬታዎች ላይም የቴሌቪዥን ጣቢያው በአምስት ቀናት ውስጥ በጽሑፍ ምላሽ እንዲሰጥ ብሮድካስት ባለስልጣን አሳስቧል፡፡
በአማራ ክልል መንግስት ቅሬታ የተሰነዘረባቸው አራቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የቀረበባቸውን ቅሬታ የማጣራት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ፤ ማጣራቱ ሲጠናቀቅ ጉዳዩ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግስት በቅርቡ በጐንደር አካባቢ ተፈጥሮ ከነበረው ችግር ጋር በተያያዘ፣ መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያቆሙ ማስጠንቀቁ ይታወቃል፡፡  


Read 12129 times