Saturday, 02 November 2019 12:34

ይድረስ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  መቼም ለጤናዎት እንደምን አሉ ብዬ አልጀምር ነገር፣ የአካል ደህንነትዎን እያየሁት ነው፡፡ የመንፈስዎን ደግሞ መገመት ይቻላል:: ኢትዮጵያን የሚያህል ሀገር፣ ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ ጋር መምራት ከባድ እንደሆነ ለመረዳት አይቸግርም፡፡
ክቡር ሆይ፤ እርስዎ ወደዚህ መንበር ከመጡ በኋላ ሀገራችን ብዙ ተስፋ የጫሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተውበት፣ የ2019 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በነገራችን ላይ እንኳን ደስ ያለዎት ብዬ መጀመር ነበረብኝ፡፡ እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ሽልማቱ መቶ በመቶ ይገባዎታል ብዬ የማምን ዜጋ ነኝ፡፡  
በእኔ ምልከታ በብዙ ፈተና ውስጥ እያለፉም ቢሆን ብዙ ውጤቶችን በማስመዝገብዎት ትልቅ እውቅና እሰጣለሁ፡፡ በሀገራችን የህግ የበላይነት ባለመከበሩ ከዕለት ወደ ዕለት የዜጋው ሰላም ውሎ መግባት ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ማየት በእጅጉ የሚረብሽ ጉዳይ ነው፡፡ የዕለት ተዕለቱን ችግር ትተን እርስዎ ለሥራ ወደ ውጭ በወጡባቸው ጊዜያት እንኳን  የሚነሱ ችግሮች፣ የሰው ሕይወትን የሚያስገብሩ መሆናቸው በጣም አሳሳቢ ነው:: ሕዝቡም ያለብዎትን ጫና ለመረዳት እየሞከረ እንደሆነ የሚያመላክቱ ነገሮች ቢኖሩም፣ በተለይ ለውጡን ተከትሎ በሞት እያጣናቸው ያሉት ዜጎች ቁጥር መጨመር ስጋት እየፈጠረ ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ የተከሰተው አሳፋሪ ጭፍጨፋ እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ በእርግጥ ብዙዎቻችን ነገሮችን የምንመለከተው በተናጠል በመሆኑ መፍትሔው ቀልሎ ቢታየንም፣ ሀገር መምራት የብዙ ዘርፎች ድምር ውጤት ነውና ሊከብድ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
ለመሆኑ ሰሞኑን የተከሰተው ግጭትና የሰዎች ህልፈት መነሻው ከወዴት ይሆን? ወንጀል ፈፃሚዎቹስ እንዴት የልብ ልብ ተሰማቸው? የሚለውን ስናስብ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ጥቂቶቹን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ከለውጡ በኋላ የህግ የበላይነት ለማስከበር የተደረገው እንቅስቃሴ ደካማ መሆን
ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ ለውጡ እጅግ መልካም የሆኑ አያሌ ገጸ በረከቶችን ይዞ የመምጣቱን ያህል፣ የመንግስት ሆደ ሰፊነት  ችግሮችን የሚያይበት መንገድ ጉድለት ያለበት በመሆኑ ነው እላለሁ፡፡ ለዚህም በእርስዎ ሲነሱ የነበሩ ምክንያቶች ታፍኖ የነበረ ማህበረሰብ በሩ ሲከፈት ለመውጣት የሚፈጠረው ግፊት ነው፣ የለውጥ ደንቡ ነው፣ በሃገራችን ታሪክ የማንግባባ ዜጎች በመሆናችን ታሪክን የምንመለከትበት እይታ የፈጠረው ችግር በመሆኑ ወደፊት እየተስተካከለ ይሄዳል ተብሎ መታሰቡና በመሪው ፓርቲ ውስጥ ያለው መከፋፈል የፈጠረው ችግር ነው እየተባለ የሚቀነቀነው ሁኔታ መዘናጋትን ፈጥሮ፣ አጥፊዎችን ለይቶና አጣርቶ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ፣ የምናየውን እንድናየው ሆኗል፡፡
በእርግጥ ለችግሩ መንግስትን ብቻ መኮንን አይቻልም፡፡  በማህበረሰቡም በኩል አሁን ለተከሰተው ግጭት መነሻ የሆነውን ግለሰብ ለመደገፍ ከሚሊዮን በላይ ህዝብ ተሰብስቦ፣ ጥቂቶች በሌላቸው የፈራጅነት ስልጣን እነሱው ወንጅለው፣ እነሱው በአደባባይ ሲሰቅሉ፣ ብዙዎቻችን ሃይማኖታችንን እንኳን ትተነው ለህሊናችንና ለሞራል እሴቶች መገዛት ባለመቻላችን፣ በካሜራ እየቀረፅን፣ አብረን ቁልቁል ከሰቀሉት እኩል መተባበራችን መንግስትዎ፣ እኔ ምን ላድርግ፤ ህዝቡስ እንዲል በር ከፍተንለታል፡፡
ከአፈናቃዮች ጋር አብረን አፈናቅለናል፡፡ የአጥፊዎችን ሃሳብ ገዝተን አከፋፍለናል፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት እንደ መንግስት በዚህ ሁሉ ጊዜ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የታሰበው ዲሞክራሲ እውን እንዲሆን በማለት የህግ የበላይነትን በሙሉ ሀይሉ ለማስከበር የሚያቀርባቸውን የመቻቻልና ምህዳር የማስፋት እሳቤ እንደ አለመቻል የቆጠሩ አካላት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መስመራቸውን በመቀያየር፣ እያመሱንና እየገደሉን ይገኛል:: ለዚህም ዓላማቸው መሳካት የህዝቡ ረብሻን አልቀበልም ባይነት እሴት መሸርሸርና ወንጀለኞችን ከጥፋታቸው ይልቅ በዘራቸው በማየት፣ የእኛ ስለሆኑ አትንኩብን ማለቱ፣ ትልቅ መደበቂያ ዋሻ ሆኗቸው ፣በአደባባይ ፎክረው ይተኩሳሉ፤ ተኩሰው ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ይቀጥፋሉ:: መሳሪያ ባይኖራቸው ዓላማቸው መግደል ነውና፣ እንደ ሮማውያን ዘመን፣ በድንጋይ ወግረው ይገላሉ:: የተለያዩ ቤተ እምነቶችን ያቃጥላሉ፡፡ በሚዲያ ዘራፍ ያዙኝ ልቀቁኝ ባይነታቸው፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ እንደገባ ወረርሽኝ ከዳር ዳር እየተስተጋባ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ተው የሚል አካል ባለመኖሩ፣ ይኸው እሳቱ እየፈጀን ይገኛል፡፡ ስለዚህ መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ባለመቻሉ፣ ሃገር እየታመሰች እንደሆነ አውቆ፣ ለነገ በማሰብ መንቀሳቀስ ዋና ሥራው እንደሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የዚህ ችግር መፍትሔ በመራቁ አሁንም መንግስትንና ህዝብን ንቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት፣ በአራቱም ማዕዘናት ማየት የተለመደ ነው፡፡
የገዢው ፓርቲ መከፋፈል
ኢህአዴግ የሚባለው አካል ሀገሪቱን ሲመራት አሁን ለደረስንበት መከፋፈል መሰረቱን የቆፈረው እሱ በመሆኑ በአሸዋ ላይ እንደተገነባ ቤት ሃሳቡ ሁሉ ሲፈራርስ ማየታችን እሙን ቢሆንም፣ የማናውቃቸውን የሃገራችንን ብሔር ብሔረሰቦች እንዲታወቁ የፈጠረው እድል እውቅና የሚያስቸረው ነው፡፡ በእርግጥ መንግስታት ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ለአገዛዛቸው የተሻለ ሆኖ ስለሚታያቸው፣ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት ለህዝቡ ከማሳየት ይልቅ ከአንድነት የሚያስወጣ ልዩነት ላይ ብቻ በመሰራቱ አሁን ለደረስንበት ውድቀትም ኢህአዴግ  ተጠያቂ ነው:: ምንም እንኳን ለልማት ከወጣው ገንዘብ እኩል የግለሰቦችን ካዝና ያደለበ ከኢሕአዴግ ውጭ በዓለማችን  ሌላ መንግስት መኖሩን ባንሰማም፣ ከሙስና በተረፈው ገንዘብ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች መሥራቱ ቀልጣለች እንደተባለላት ቅንጥብጣቢ ሥጋ ሊያደርጋት ይችል ነበርና፣ ሳናመሰግነው አናልፍም፡፡
የትምህርት ጥራት ጥያቄ ውስጥ ቢሆንም ታላላቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መገንባቱ ዛሬ ከመገንባት ይልቅ በተገነባው ላይ ሥለ ጥራት እንድናወራ በር ከፍቷልና እሠየው ቢባል አይበዛበትም ባይ ነኝ፡፡ በሌሎቹም ዘርፎችም እንዲሁ አዎንታዊነቱንና አሉታዊነቱን እያነሱ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ ማለቴ ይህ ፓርቲ መንግስት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ለሰራው መልካም ውጤትም ይሁን ጥፋት ከመካከሉ የአንድ ፓርቲ የበላይነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎቹን ግንባር ድርጅቶች ለምስጋናውም ይሁን ለጥፋቱ ኃላፊነት ከመውሰድ አያድናቸውም፡፡ ለዚህም በየጊዜው የነበሩ የግንባር ድርጅት መሪዎች፣ ለህሊናቸው ታማኝ ሆነው ማገልገል ሲገባቸውና ችግርም ካለ መስዋዕትነት ከፍለው አጀንዳውን ለህዝብ አለማቀበላቸው፣ የእነሱ ችግር በመሆኑ፣ ተጠያቂነቱ እኩል ሊያርፍባቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
ክቡር ሆይ፤ ታዲያ እርስዎን የግንባሩ ሊቀ መንበር አድርጎ የመረጥዎት ድርጅት፣ የነበረበትን ድክመትም ይሁን ጥሩ ጎን እኩል መቋደስ ሲገባ፣ ስኬቱን በጋራ ወስዶ ጥፋቱን ወደ አንድ ወገን ብቻ መግፋቱ፣ በመርህ ደረጃ የማያስኬድ በመሆኑ፣ ይኸው እርስ በእርስ ተለያይታችሁ የምትወራውሯቸው መግለጫዎች፣ ሰላሳ ዓመት አብራችሁ የሰራችሁ መሆኑ ቀርቶ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ጠላት መሆናችሁን የሚያሳይ መሆን ከጀመረ ከራርሟል፡፡
በእርግጥ ይህ የፓርቲያችሁ ጉዳይ ነው ብለን እንዳንተወው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተከሰቱ ያሉ ጥፋቶች መነሻቸው የፓርቲዎቻችሁ ጎራ መለየት መሆኑ፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ትልቅ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ፓርቲዎች በህግ የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፈን አንሰጥም ማለታቸው አሁንም ወንጀለኞች እንዲበራከቱ መንገድ ከፍቷል፡፡ ማህበረሰቡም የእነ እከሌ ወንጀለኛ ሳይጠየቅ የኛ ወንጀለኛ እንዴት ተደርጎ እንዲል የፈቀደ ሲሆን ክቡርነትዎ ቢቻል ሁላችሁም ተቀራርባችሁና ተነጋግራችሁ እንዳማረባችሁ፣ ከእነ ልማታችሁም ይሁን ከእነ ጥፋታችሁ አብራችሁ ብትቀጥሉ፤ ያ ካልሆነ ደግሞ በወጉ ተለያይታችሁ መስመር ለይታችሁ ብትሰሩ የተሻለ ነውና ቀላል የቤት ሥራ ባይሆንም የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡ ጉዳዩ የእርስዎን ያላሰለሰ የሰላም ጥረትና ከጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በኋላ የሚደረግ ውሳኔ ይጠብቃል፡፡  
ሰዎችን ከሚገባቸው በላይ ማግነን
ክቡር ጠቅላያችን፤ ይህ ለውጥ የብዙሃን ደም የተከፈለበት፣ የብዙሃን ወጣትነት የተጨናገፈበት፣ ብዙዎች ህልማቸው በአጭር የተቀጨበትና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በወላጆቻቸው ቀብር እንኳን እንዳይገኙ መስዋዕት የከፈሉለት ነው፡፡ አሁንም ብዙዎች ሞተው ያመጡትን ለውጥ በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ለውጡ የታሰበለትን ግብ እንዲመታ፣ የኑሮ ውድነቱ አደባባይ እንዲወጣ እየገፋው የዳቦ እጦት እያሰቃየው፣ የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ስራ አጥ አድርጎት፣ በመኖርና ባለመኖር ውስጥ ሆኖ በተለይ  ለውጡ ገብቷቸው እርስዎን ለማገዝ ደፋ ቀና የሚሉ ባለስልጣናትን በመመልከት፣ የሆዱን በሆዱ አድርጎ በተስፋ እየጠበቅዎት ቢሆንም፣ የለውጡን ውጤት የተወሰኑ ቡድኖችና ግለሰቦች ብቻ እንዳመጡት ተደርጎ በመወሰዱ፣ ህዝቡ በእነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች የህሊና ባርነት ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡ እነዚህም ቡድኖች የሞቱለትን ዓላማ ዘንግተው፣ በተቃራኒው ጎራ በመቆም ሰውን የሚያህል ክቡር ፍጥረት በድንጋይ ወግረው እስከ መግደል እየደረሱ ነው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ ለተስፋ ሰጭ ለውጥ ዋጋ የከፈለው ሰፊው ህዝብ ተዘንግቶ -- ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዛርማ፣ ኤጄቶ….. እና ግለሰቦች ለውጡን እንዳመጡት ከበቂ በላይ በመቀንቀኑ፣ ይኸው እነዚህ አካላት ከአቅማቸው በላይ የሆነ ክብር መሸከም ባለመቻላቸው፣ ለፍፁም አምባገነናዊ አመለካከት በቅተዋል፡፡
ሰሞኑን የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ድርጊቱን አለማውገዙና በጉዳዩ ላይ መንግስትዎን ማብራሪያ አለመጠየቁ ትንግርት ሆኖብናል:: ምክንያቱም ከለውጥ በፊት ቢሆን ግለሰቦች እንዲህ አይቀብጡም፤ ቢቀብጡም እኛም መፅናኛ ቃል አንጠብቅም፡፡ ግን አሁን የእርስዎ ዘመን ነውና  በሚዲያ ወጥቶ፣ የእንባ አድርቅ ቃላት የሚወረውር አንድ የፌደራል ባለሥልጣን መጥፋቱ ለምን ይሆን አስብሎናል፡፡
እንግዲህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ሃሳቦች፤ የህግ የበላይነት እንዳይከበር ካደረጉት ምክንያቶች በጣም ጥቂቶቹ ናቸውና አሁንም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ፤ መልካም የሆነውን ኢትዮጵያዊ ራዕይዎትን ለመተግበር፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርና ህዝቧ ሊኖሩ የግድ ነውና፣ አውቀው አፍነው ይዘውት አንድ ቀን እሳቱ እርስዎንም በልቶዎት ከማየታችን በፊት አልፎ አልፎ በንግግር የሚያሳዩንን ቁርጠኝነት መሬት ላይ አውርደው፣ የሚመጣውን አብረን ዋጋ እንክፈልበት፡፡ ሀሳብዎት ገዢ በመሆኑ አለመደገፍ ባንችልም፣ ሃሳብዎትን ለማስፈፀም የሚችሉበትን ሜዳ እያጠበቡት መመልከታችን ያሳስበናል፤ከዚያም አልፎ ሀገራችን ነችና ያገባናል፡፡
መቼም እርስዎ የየቤተ ዕምነቱን አስተምህሮ የሚያውቁት በመሆኑ፣ ለታላቁ መጽሐፍ ቃል አዲስ ባይሆኑም “ለሰነፍ ሰው እራስህን ዝቅ አታድርግ…” ይላልና የእርስዎ ትህትናና ሆደ ሰፊነት፣ ሰነፎችን የልብ ልብ እየሰጠ በመሆኑ እባክዎት ሆደ ሰፊነትን ሊቀበለው ለማይፈልግ ጊዜ ማባከን ነውና በአንድ ወቅት “ብዙ ኮማንደሮች በተለያዩ ሀገራት እየሰለጠኑ ነውና መጥተው ሰው እንዳይፈጁ እሰጋለሁ” ያሏቸውን አስመጡና የህግ የበላይነትን አስከብሩልን:: ይህችን ወድ ሀገር ለመታደግ አብረንዎት ለመሰለፍ ቁርጠኛ ነንና “ልብ ያለው ልብ ይበል” እንደተባለው ልብ ያድርጉልን፡፡
ቸር ሰንብቱልኝ !     


Read 1745 times