Print this page
Saturday, 02 November 2019 12:45

“ጥቁር ሽታ” የፊታችን ሰኞ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)


            በደራሲና ገጣሚ መሐመድ ነስሩ (ሶፎንያስ አቢስ) የተጻፈው “ጥቁር ሽታ” የአጫጭር  ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍ፣ የፊታችን ሰኞ ከቀኑ በ11:00 ሰዓት፣ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በሚከናወን ልዩ የኪነ-ጥበብ መርሃ ግብር በይፋ ይመረቃል፡፡
በዕለቱ ደራሲና ገጣሚ እንዳለጌታ ከበደ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ደራሲና ገጣሚ ዶ/ር በድሉ ዋቅጂራ፤ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ዮናስ ባህረ ጥበብ፤ ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው፣ ገጣሚት ትዕግስት ማሞ፣ ደራሲ ህይወት እምሻውና ገጣሚ ደምሰው መርሻን ጨምሮ ሌሎች አንጋፋና ወጣት የኪነ ጥበብ ሰዎች በአቅራቢነት እና በእንግድነት የሚገኙ ሲሆን፣ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ፅሑፍ መምህር የሆኑት አቶ ዘመዱ ደምስስ በመጽሐፉ ዙሪያ አጭር ሒሳዊ ዳሰሳ እንደሚያደርጉም ተነግሯል፡፡
 በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አጫጭር ልቦለዶችን በ203 ገጾች አካትቶ በቅርቡ ለገበያ የበቃው “ጥቁር ሽታ”፤ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በ120 ብር  እየተሸጠ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡
በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለረጅም አመታት በስሙና “ሶፎንያስ አቢስ” በተሰኘው የብዕር ስሙ የተለያዩ መጣጥፎችን፣ ልቦለዶችንና ወጎችን ለንባብ ያበቃው ወጣቱ ደራሲና ገጣሚ መሐመድ ነስሩ፤ ከዚህ በተጨማሪም መዝናኛ፣ አዲስ ነገርና ፍትህን ጨምሮ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ጥልቅ ሃሳቦችን ያዘሉ ጽሁፎቹን ለአንባቢያን ሲያደርስ የቆየ ሲሆን አሁንም በፍትህ መጽሔት በአምደኝነት እየጻፈ ይገኛል፡፡
ደራሲ መሃመድ ነስሩ፤ ከዚህ ቀደምም በሳል ግጥሞች የተካተተበትንና የመጀመሪያ ስራው የሆነውን “አሌፋት” የተሰኘ የግጥም መድበል ለንባብ ያበቃ ሲሆን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተማሪነት ቆይታውም መቅረዝ በተባለው የኪነጥበብ ቡድን ውስጥ ደማቅ ተሳትፎ ከሚያደርጉና ተወዳጅ ከነበሩ የስነጽሁፍ ሰዎች አንዱ እንደነበር ወዳጆቹ ይናገራሉ፡፡



Read 8720 times