Saturday, 02 November 2019 13:16

ቄሮ “መንፈስ” እንዳይሆን?

Written by  ኩርኩራ ዋፎ - ከለገጣፎ
Rate this item
(1 Vote)

 ጎማ ማቃጠል፣ መንገድ መዝጋት፣ ንብረት ማውደም፣ ሰዎችን መደብደብና መሳደብ … ለቄሮ ኦሮሞን ትልቅ ማድረግ ሳይመስለው አልቀረም፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር ግን ታላቁን የኦሮሞ ህዝብ፣ አቃፊውን የኦሮሞ ማህበረሰብ በዓለም ፊት ማዋረድ ነው፡፡

              ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ቀትር ላይ ለገጣፎ ንግድ ባንክ አጠገብ፣ አንድ ካፌ ውስጥ ቡና እየጠጣሁ ሳለ፣ መፈክር እያሰሙ ወደ አዲስ አበባ አቅጣጫ እየተመሙ የሚመጡ ወጣቶችን አየሁ፡፡ ከየት እንደመጡ፣ እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ ጠጋ ብዬ የሰልፈኞቹን ማንነት ለማየት ሞከርኩ፡፡ የለገጣፎ ነዋሪም መምህርም በመሆኔ ብዙዎቹን የአካባቢውን ወጣቶች አውቃቸዋለሁ፡፡ የአካባቢያችንን ሰው ፈልጌ ማግኘት ግን አልቻልኩም፡፡ አጠገቤ የነበሩ ሰዎች፤ ከወደ ለገዳዲ አቅጣጫ በአይሱዙ መኪና ተጭነው የመጡ ሰልፈኞች መሆናቸውን ሲያወሩ ሰማሁ፡፡ በርግጥም ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰልፈኞች ናቸው፡፡ እነዚህ “ጠጉረ ልውጥ” ሰልፈኞች የሚያስተጋቡትን መፈክር ስሰማ ይበልጥ ተደናገርኩ፡፡ (የሰማሁትን እዚህ መድገም አልፈልግም)
ሰልፉ ለምን እንደተደረገ ሳጣራ፣ ታዋቂው አክቲቪስት ጃዋር ሙሐመድ በፖሊስ በመከበቡ፤ “ተቃውሞህን አሰማ” ተብለው የተሰማሩ “ቄሮዎች” መሆናቸውን ሰማሁ፡፡ እነዚህ ሰልፈኞች ትንሽ እንደሄዱ ሦስት መቶ ሜትር የሚሆን መንገድ፣ በድንጋይና በግንድ መዝጋት ጀመሩ፡፡ “ቄሮ” ማለት እነዚህ ናቸው? “ቄሮ” ማለት አቶ ጃዋር “ውጡ” ባላቸው ጊዜ እየወጡ፣ ለምን ሳይሉ፣ መንገድ በድንጋይና በግንድ የሚዘጉ ናቸው ማለት ነው? --- የሚሉ ጥያቄዎች በአእምሮዬ ተመላለሱ፡፡
ከረቡዕ  ቀደም ብለው በነበሩት ቀናትም እንዲሁ ወደ አዲስ አበባ መግቢያ አቅራቢያ ባሉ ከተሞች አካባቢ መንገድ በመዘጋቱ፣ የሀገሪቱ የትራንስፖርት ፍሰት እክል ገጥሞት እንደነበር ሰምተናል፡፡ ይህንን ማን አደረገ? ሲባል፤ “ቄሮ” የሚል መልስ ይሰማል፡፡
ብዙዎቹ ሰልፈኛ “ቄሮዎች” የአርሶ አደር ልጆች ናቸው፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ ለአርሶ አደሩ የአዝመራ መሰብሰቢያ ወቅት ነው:: በዚህ የአዝመራ መሰብሰቢያ ወቅት አርሶ አደሩ ብዙ የሰው ኃይል ይፈልጋል፡፡ ቄሮ ትኩስ የሥራ ኃይል እንደመሆኑ በዚህ ወቅት አዝመራ በመሰብሰብ ወላጆቹን ማገዝ ሲገባው፣ መንገድ ለመዝጋት ከአቅሙ በላይ የሆነ ግንድና ድንጋይ በመሸከም ላቡን ያፈሳል፡፡ ወርቃማ ጊዜውንና ጉልበቱን ያባክናል፡፡ የሚገርም እንቆቅልሽ ነው፡፡
ወልደው ያሳደጉት፣ የሚያጎርሱትና የሚያለብሱት ወላጆቹ ሲያዙት፣ የፈሰሰ  ውሃ ቀና የማያደርግ ቄሮ፤ አቶ ጃዋር ሙሐመድ መንገድ ዝጋ ሲለው ግን የሚቀድመው የለም:: እንዲህ ያለው ነገር ለቄሮ ሽርሽር እንደ መሄድ ሳይቆጠር አልቀረም፡፡ ጎማ ማቃጠል፣ መንገድ መዝጋት፣ ንብረት ማውደም፣ ሰዎችን መደብደብና መሳደብ … ለቄሮ ኦሮሞን ትልቅ ማድረግ ሳይመስለው አልቀረም፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር ግን ታላቁን የኦሮሞ ህዝብ፣ አቃፊውን የኦሮሞ ማህበረሰብ በዓለም ፊት ማዋረድ ነው፡፡
እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ፣ እኛ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎችም፣ ባለፉት 27 ዓመታት፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ነበሩን:: የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ነበሩን፡፡ በተደረገው መጠነ ሰፊ ትግል፣ ያ ጨቋኝ ወያኔያዊ ኃይል ላይመለስ ተወግዷል:: ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሞ፣ የጦር ሚኒስትሩ ከኦሮሞ፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ከኦሮሞ፣ የደህንነት ኃላፊው ከኦሮሞ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ከኦሮሞ፣… በሆነበት ዘመን (በአንጋፋነታችን) ሌሎች ብሔር፣ ብሐረሰቦችን አስተባብረን መምራትና ለሁላችንም የምትበጅ ኢትዮጵያን ማጠናከር ሲገባን፣ ኦሮሚያን የጦርነት ቀጣና ማድረግ ተገቢ ነው? ይህስ ተግባር ፈጣሪን ማስቆጣት አይሆንም? ይህንን ሁኔታ ልብ ልንለው ይገባል፡፡
እንደኔ እንደኔ፣ አሁን እየታየ ያለው መንገድ መዝጋትም ይሁን ንብረት ማውደም---- ያው ሽፍትነት ነው፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ጠላት ማብዛት ነው፡፡ ይህ ለውጥ እንዲመጣ የህይወት ዋጋ የከፈሉት ቄሮዎች ዓላማ፤ በሀገራቸው ፍትህ እንዲረጋገጥና እኩል ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን እንጂ ወንጀል እንዲስፋፋ አልነበረም:: በለውጥ ኃይልነቱ ያወደስነው፣ ለአምባገነኖች አልንበረከክም በማለቱ ያሞገስነው “ቄሮ”፤ እንዲህ ያለ ለኦሮሞ ህዝብ የማይመጥን ተግባር ሲፈጽም ከማየት በላይ የሚያሳፍር ነገር የለም፡፡
ይሄ ሁሉ የሰሞኑ ሁከት ከበረደ በኋላ አንድ አንጋፋ መምህር ወዳጄን አገኘሁት፡፡ የተፈጠረውን ሁኔታ በተመለከተ አስተያየቱን ጠየቅሁት፡፡
“ጃዋር ለኦሮሞ ህዝብ ‘ላም እሳት ወለደች እንዳትልሰው እሳት ሆነባት፣ እንዳትተወው ልጅ ሆነባት’ እንዲሉ ነው የሆነበት፡፡ አንቅረን እንዳንተፋው ልጃችን ነው፡፡ እንዳንደግፈውም ተግባሩ የተሳሳተ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን ውጡና ተቃወሙ አለ፡፡ ወጣቶች ወጡ፣ ጥፋት ሰሩ፣ እነሱም ተጎዱ፡፡ ዓላማና ግቡ ላልታወቀ ሰልፍ ወጥተው ሞቱ ቆሰሉ፡፡ ምን ውጤት ተገኘ? ምንም የተገኘ ነገር የለም፡፡ ይባስ ብሎ ጃዋር በቴሌቪዥን ብቅ አለና ‘የሞተን ቅበሩ፣ መንገድ ጥረጉ፣ የቆሰለን አሳክሙ፣ ጠይቁ…’ ብሎን ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ለደረሰው ጉዳት ኀዘኑን እንኳ አልገለጸልንም፡፡ የሱን ትእዛዝ ሰምቶ ወጥቶ በዚያው የቀረ ወጣት ወላጆች፤ በዚህ ተግባሩ በጣም አዝነዋል…” ነበር ያለኝ፡፡ እኔም ይህንን የወዳጄን ሀሳብ እጋራለሁ፡፡ ጃዋር ሙሐመድም ሆነ ቄሮ፤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድን “ሌባ” ለማለት የሞራል ብቃት የላቸውም፡፡
አቶ ጃዋር ሙሐመድን በተመለከተ አንድ ነገር ለማለት እወዳለሁ፡፡ አቶ ጃዋር የኦሮሞን ህዝብ ትግል በፌስቡክ በማስተባበር ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ ድርጅት አቋቁመው 45 ዓመት የትጥቅ ትግል ካደረጉ የኦሮሞ ልጆች ይልቅ ጃዋር፣ የኦሮሞ ወጣቶችን በማህበራዊ ሚዲያ እየመራ የፈጠረው እንቅስቃሴ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ለዚህ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ዛሬ የዚህን ትግል ውጤት የምናጣጥምበት ወቅት መሆን ሲገባው፤ “ጃዋር ተከቧል፣ ጠባቂዎቹ ተነሱ፣ ሊታሰር ነው…” በሚል ብጥብጥ ውስጥ መግባት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ “የኛ ወገን የሆነ ሰው በህግ አይጠየቅ” ማለትም አግባብነት የለውም፡፡ ወያኔን የጠላናት እኮ “የራሷን ሰዎች” ልዩ ተጠቃሚ በማድረጓ፣ ወንጀለኞችን አቅፋና ሸፋፍና በመያዟ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም፡፡ ጃዋር ከህግ በላይ አይደለም፡፡ ዶ/ር ዐቢይም ከህግ በላይ አይደሉም፡፡ ይህ እውነታ መታወቅ አለበት፡፡
ጽሁፌን ከመቋጨቴ በፊት ስለ ቄሮ አንድ ነገር ለማለት ወደድሁ፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ የቅንጅት አመራር አባል የነበሩት ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ፤ “ቅንጅት መንፈስ ነው” ማለታቸውን በወቅቱ ከወጡ ጋዜጦች ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ይህ አባባል በወቅቱ አልገባኝም ነበር፡፡ ቅንጅት “መንፈስ” እንጂ “ተቋም” አለመሆኑን በግልጽ የተገነዘብኩት፣ የቅንጅት አመራር አባላት ሲታሰሩ ነው፡፡ የቅንጅት አመራሮች ሲታሰሩ፤ ቅንጅት የት እንደገባ ሳይታወቅ እንደ መንፈስ ተነነ፡፡ የቄሮም እጣ ፋንታ ከዚህ የተለየ ሆኖ አይታየኝም:: ምክንያቱም ቄሮ ተቋም አይደለም፡፡ ህጋዊ መዋቅር የለውም፡፡ የሚታወቅ የእዝ ሰንሰለት የለውም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር የለውም፡፡ “የቄሮ አለቃ ነኝ” የሚለው አቶ ጃዋር ራሱ፤ ምክትል እንኳ የለውም፡፡ በዚህ የተነሳ አንድ ቀን ቄሮም እንደ ቅንጅት መንፈስ ሆኖ ይተናል፣ ይበናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 9344 times