Saturday, 02 November 2019 13:39

ጃርትና ግጥሞቿ - (ማኅበራዊ ኂስ)

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋዬ
Rate this item
(0 votes)

     በመላ ሀገራችን አርሶ አደሮች ዘንድ ጃርት፣ ጦጣ፣ አሳማ፣ ዝንጀሮ፣ ነጎዴና ግሪሳ ወፎች  በአስቸጋሪነታቸውና በእህል ፈጂነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ በሰብል ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የቻለ በጦር እየወጋ፤ ያልቻለ በወጥመድ ወይም በመንቀፊሎ  እየያዘ፤ ሌላው ደግሞ በወንጭፍ ወይም በአበራሮ ጠጠር እየወነጨፈ  በመግደል ይከላከላል፡፡
በደጀን ዙሪያ ቆላ ደጋ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችም፣ ከነሐሴ እስከ ጥር ድረስ ባለው ጊዜ፣ ሰብላቸውን ከጃርትና ከተለያዩ አራዊት ጥቃት የሚከላከሉት ከላይ በተገለጸው ዘዴ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የጃርት፤ የአሳማና የዝንጀሮ መንጋ ጥቃት በእጅጉ ከፍተኛ ስለሆነ፣ አርሶ አደሮች፣ ሰብላቸውን ሌትም ቀንም በትጋት መጠበቅ አለባቸው፡፡ ሰብላቸውን በአግባቡ ካልጠበቁ በሰነፎች ላይ አራዊቱ ግጥም እየገጠሙ ይሳለቁባቸዋል፡፡ አዝመራቸውን በአራዊት አናስበላም ብለው የሚጠብቁትንም ጀግኖች፣ እነ ጃርት ያሞግሷቸዋል፡፡ ተወልጄ  ባደግሁበት በአለቅታም አቦና ሚካኤል አካባቢ ‘’አዘነጋሽ’’  የተባለች ጃርት ትኖር ነበር። የአገሬ አርሶ አደሮች ይህን ዓይነት ስም ያወጡላት በተለይ በመስከረም፤ በጥቅምት፤ በኅዳርና በታኅሣሥ  ወር ላይ አድብታና አዘናግታ ወደ ጓሮአቸው በመግባት፣ የደረሰ ዱባቸውን ሠርቃና ያፈራ በቆሏቸውን ሸልቅቃ ስለምትግጥባቸውና የባቄላ፤ የአተር፣ የዘንጋዳና የገብስ እሸታቸውን --  እየፈለፈለችና እየሸመጠጠች ስለምታጠፋባቸው ነው። ‘’አዘነጋሽ’ ይህንን የምታደርገው በሌሊት የማይነቃ ገበሬ ስታገኝ እንጂ ከልባሞችና ከንቁ ገበሬዎች ጓሮ ጨርሶ ዝር አትልም። ምክንያቱም ልባም ገበሬዎች በአንካሴ ስለሚወጓትና ወጥመድ እያጠመዱም ስለሚይዟት፣  በዱላም ስለሚደበድቧት ነው። እንዲያው አዘነጋሽ በተንኮሏ ስለታወቀች ነው እንጂ እርሷ የምትመራው የጃርት ባታሊዎን ጦር ብዙ ነው፡፡ የጃርት  ሠራዊት እንደ ተምች፤ እንደ ቸነፈር ስለሚቆጠር በሰብል ወቅት ላይ መከላከያውን አንካሴ የማያስል፤ ጦርና ዘገር የማያዘጋጅ፤ ጨርቅ የለበሰ ጭምብል በየጓሮው የማያቆም አርሶ አደር አይኖርም፡፡ የባለብረቴዎቹ ወንድማማቾች  የእነ አቶ አሰጌ ኪዳኔና የእነ አቶ አዳነ ኪዳኔ  ገበያም የሚደራው በሰብል ወቅት ላይ ነው፡፡ በዚህ ወቅት መጥረቢያ፤ ማጭድ፤ አንካሴ ወይም ጦር፤ ዘገር የማያስል ሰው አይኖርም፡፡
ቢሆንም ብረት ያሳለው ሁሉ ጀግና ሆኖ  ጃርት ላይወጋ ይችላል፡፡ ይኸ ሁሉ ጦር ለእርሷና ለወገኖቿ  የተዘጋጀ መሆኑን በደመ ነፍስ ብታውቅም፣ እንደ አይጥ «እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል» እያለች፣ ማምለጫዋን ጭምር ታዘጋጃለች፡፡ ሰነፉን አርሶ አደር ደግሞ አዘነጋሽና አጥቂው ሠራዊቷ ስለሚያውቁት፣ በሌሊት የነቃው ታታሪ አርሶ አደር አጣድፎ ሲያባርራቸው፣ ወደ አያ ሰነፌ፤ ወደ ጋሽ አይነቄ ጓሮ ይዘምታሉ እንጂ ጭራሽ በርግገውና አገር ጥለው አይሸሹም፡፡ እነ አዘነጋሽ  ሲደረስባቸው ጦርነት ይገጥማሉ፤የጃርት ወስፌያቸውን ወደ ጠላት እያስፈነጠሩ ይፋለማሉ፡፡ የጃርት ጦር በቀላሉ ዓይን ላይ ሊሰካ ስለሚችል፣ ጃርት ጠባቂ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አርሶ አደሩን  በምትኃቷ አሞኝታ፤ አዘንግታና አድብታ፤ ወደ ጓሮ ከገባች ደግሞ የዓመቱን አዝመራ በአጭሩና በዕንጭጩ ለማስቀረት ችሎታው አላት። እና ከዕለታት በአንዱ ሰነፍና አምቦዛላጭ ከሆኑት ከአቶ አዳሙ ፈረደ ጓሮ ገብታ፣ በቆሎ ስትሸለቅቅ፣ የአቶ አዳሙ ባለቤት ሰምተው ኖሮ፤  «አዳሙ እረ ተነሥ! ጃርት ገብታ እያጠፋችን’ኮ ነው›› ይላሉ፡፡ አቶ አዳሙም ከእንቅልፋቸው መነሣት ስላስጠላቸው ‹›ሴትዮ አርፈሽ ተኚ፤ ጃርቷ የለችም››  ብለው ለጥ ይላሉ፡፡ ጃርትም የልቧን አድርሳ ከጠገበች በኋላ እንደዚህ ብላ ዘፈነችባቸው፡-
“አዳሙ ፈረደ እንዴት ይወድደኛል፤
ከመሃል ቁጭ ብዬ የለችም ይለኛል፡፡»
ተንኮለኛይቱ ጃርት
አንዲት የነጋባት የመስከረም ጃርት፣ ሰው አየኝ አላየኝ ብላ፣ ሁልጊዜ የዓይን አሩን (ጩቁን) ከማይጠርገው ከአያ ምንተስኖት ጓሮ ሹልክ ብላ በመግባት፣ የልቧን ትሠራለች ማለት ነው:: በራስጌ በኩል ገብታ እያሰሰች፣ በግርጌ በኩል ስትወጣ፣ አያ ምንተስኖት ዓይኑን  እያጭለመለመ፣ ወደ ጓሮው ሲመጣ ታየዋለች:: ነገሩ አስገረማትና፡-
“በራስጌ ገብቼ በግርጌ ስወጣ፤
አያ ምንተስኖት ጩቁን ጠርጎ መጣ‘’
በማለት ተመፃድቃበታለች፡፡ አቶ አሞኘ የኔሁን ደግሞ /የኔ አጎት/ የነቃና ታታሪ አርሶአደር በመሆኑ፣ ገና ወደ ጓሮ ለመግባት ስትሞክር፣ ነቅቶ ስለሚያባርራትና ስለሚመታት፡-
‘’ሲሄድ እንዳሞራ ሲማታ ልብራስ፣
ከአያ አምኘ ጓሮ አልቀምስም አንድራስ”
እያለች ትናገር ነበር። እንደዚሁም ተዘራ የተባለ ወፍራም ሰው፣ በዚያው በአለቅታም ውስጥ ይኖር ነበር። አያ ተዘራ እግሩን የዝሆኔ በሽታ ስለያዘው፣ ሲራመድም ቀስ እያለ ነውና፣ ጃርቲቱ አዘነጋሽ የሰውየውን ሁኔታ አጥንታ አንድ ዕለት ከጓሮው ዘው ብላ በመግባት፣ ዱባውንና በቆሎውን ሙልጭ አድርጋ
 በላችበት። ጥፋቷ ሳያንሳት ደግሞ በአቶ ተዘራ ላይም እንደዚህ ስትል ተረተችበት፡-
‘’ተዘራ በቀለ የጠብደል ኮሳሳ፣’’
በልቼ እጠግባለሁ እግሩን እስቲያነሣ፡፡”
የአቶ ተዘራ በቀለ ባለቤት ወ/ሮ ዓይኔ ቢሠነብት፣ ጃርቷ /አዘነጋሽ/ ባለቤቷን በመስደቧ ‘’ቆይ ይህችን መልከ ጥፉ አሳያታለሁ፤ ከእርሷ የከፋ ኩስና  አስቀያሚ ፍጥረት አለ እንዴ?” እያለች በጃርቷ ላይ መፎከር ታበዛለች፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የዓይኔ ቢሠነብት ዓይን ሸውራራ ነበር። ጃርትም ይህንኑ ታወቀው ስለነበር ሁለቱን መልከ ጥፉ ባልና ሚስት ልታዋርዳቸው ጊዜ ትጠብቅ ጀመር። አንድ ቀን ያያ ተዘራ ታናሽ ወንድም አቶ  ዘገየ በቀለ፣ ልጁን ይድር ነበርና ጃርት እያጨበጨበች ወደ ዳስ በመግባት፣ የሚከተለውን ዘፈን በአቶ ተዘራና በወ/ሮ ዓይኔ ላይ ዘፈነችባቸው፡፡  
«ግምን ግም አይስተው ውብን ውብ
አይስተው፣
ዓይኔን ለተዘራ ማን አመለከተው፡፡
ዘገየ በቀለ አንተ የዋልክበት፤
ሠርግህ ያማረ ነው ሸጋ  የበዛበት፡፡»
ብላ ስትዘፍን ለሠርግ የተጠራው ሁሉ በተዘራና በዓይኔ ላይ ሣቀባቸው። እንዲሁም ሠርግህ ያማረ ነው ያለችው  አቶ አማረ የተባለ አርሶ አደር ሲናገር፣ ድምጹ የትም ቦታ  ይሰማ ስለነበር፣ ከብቶቹን ነድቶ ከመኖሪያ ቤቱ «ዛዳ» እስከተባለው የእርሻ ቦታው እስኪደርስ፣ ባቄላውን በልታ ጠግባ፣ ከድንበር ላይ ተጎምራ በመዝናናት ላይ እያለች፣ የሰውየውን ድምጽ የሰማቺው አዘነጋሽ  በዚህ ተገርማ፡-
«አንተ በርቀት ላይ ከንቱ ስታገሳ
ባቄላው ያለቀው ገና ሳትነሣ፡፡
አያ አማረ እጅጉ አርፍደህ ማለዳ፤
ድሪቶህን ለብሰህ  ከብቶች ስትነዳ፣
እኔ ዛዳ ሆኚ በሣቅ ልፈነዳ፡፡»
ብላ አንጎራጉራበታለች። ዛዳ የበቆሎ፣ የአተር፣ የባቄላና የገብስ አዝመራ የሚበቅልበት የአለቅታሞች የእርሻ ቦታ ነው፡፡ የአዘነጋሽና የወገኖቿ ምሽግም እዚያው የዛዳ ቁጥቋጦና ጫካ ነበር። በተመሳሳይ ብላታ እውነቱ አለማው /የአካባቢው አጥቢያ ዳኛ/ ሳይቀሩ ከመንገድ ዳር በቆሎ ዘርተው መጠበቅ ሲገባቸው፣ በመስከረም ወር ጠንታ ከተባለ ቦታ የሚኖሩ የሩቅ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ስለሄዱና እንደ ልቧ አዘነጋሽ በደረሰ በቆሏቸው ላይ ስለፈነጨችበት፡-
«አያ እውነቱ አለማው ለነፍሱ ያደረ፣
ከመንገድ ዳር ዘርቶ ጠንታ ተሻገረ፡፡»
ብላ ዘፍናባቸዋለች፡፡ ጠንታ፡- ከደጀን ማዶ ጉበያ አካባቢ የሚገኝ መንደር ነው፡፡ እንደዚሁም ዋሌ ዓለሙ የተባሉ አርሶ አደር ሌሊት ጓሯቸውን መጠበቅ ሲገባቸው ተኝተው እያደሩና ማለዳ ብቻ እየተነሡ በቆሏቸውና የባቄላ አዝመራቸው በጃርት /በአዘነጋሽ/ መበላቱን ባዩ ቁጥር፤ «እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ወይኔ ዘንድሮ!  መሰደዴ ነው፤ ያገር ያለህ፤ የዘመድ ያለህ፤ በአዝመራዬ  ተጫውታበት የለ አንዴ? ወይኔ ወይኔ!» እያሉ ሲያለቅሱና ሲያዝኑ  ጃርት ሰምታቸው ኖሮ፤
‘’እንኳን በራስጌው ላይ በግርጌ ተጥሶ፣  
ማነው የሚከርመው ያያ ዋሌን ለቅሶ፡፡
ማለዳ ማለዳ እያለቃቀሰ፤
አያ ዋሌ መጣ ዓይኑን አባበሰ፡፡
በቆሎውን ነቅቶ መቅራት ነበረበት፣ ሌት
እየፎከረ፤
ስሜን ያጠፋዋል ተኝቶ እያደረ፡፡”
በማለትና አልቃሻ መሆናቸውን ገልጣ፣ ጃርቲቱ እንደቀለደችባቸው ባላገሮቹ ይናገራሉ:: አቶ ተሜ እምሩና ወይዘሮ ሰገድ የተባሉ ሁለት ሀብታም ባልና ሚስት በዚያው በአካባቢ ይኖራሉ፡፡ ለሀብትና ለገንዘብ ግድ የሌላቸው መሆናቸውን ለካ አዘነጋሽ አስቀድማ አውቃለች:: እናም የጓሮ በቆሏቸውን ሙልጭ አድርጋ ስትበላ ሳይናገሯትና ሳይቆጧት በመቅረታቸው የልብ ልብ ተሰማትና፡-
«ተሜ ባይናገር ሰገድ ባትቆጣ፤
ከማጀት ገብቼ ቅራሪ ብጠጣ»
--- አለች ይባላል፡፡
እንደዚሁም አቶ አያሌው ትሳሱ የተባሉት ቁመታቸው አጭር መሆኑን ጃርቲቱ ስላወቀች፣ ባወጣ ያውጣው ትልና ከጓሯቸው በመግባት ትልቅ ዱባ አንሥታ ይዛባቸው ስትሮጥ፣ እርሳቸውም እየሮጡ ይከተሏታል፡፡ ግን ሳይደርሱባት ስለቀሩና ስላመለጠች እንዲህ ብላ ቀለደችባቸው፡-
“አያሌው ትሳሱ ድኩሜ ድኩሜ፤
አልደርስብኝ አለ ዱባ ተሸክሜ፡፡”
ይህ ሁሉ ስለ ምንና ማኅበራዊ ሂስ የሚያሳየን፤ አርሶ አደሮች በማኅበራዊ ሕይወታቸው  ምን ያህል እንደሚግባቡ፤ እንደሚተራረሙና ንቃት፤ ጥንቃቄ፤ ኅብረትና ትጋት የቱን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ ቀልድ መሰል ማኅበራዊ ኂስ አማካይነት፣ እርስ በርስ እየተሣሣቁና እየተግባቡ፣ ከስሕተታቸው ይማሩበታል እንጂ መቀያየም ብሎ ነገር በእነርሱ ዘንድ  የለም፡፡   


Read 1316 times