Saturday, 02 November 2019 13:41

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


                      “ጥበብ ባለበት ስልጣኔ፣ ስልጣኔ ባለበት ደግሞ ሰብዓዊነት አለ”
                             
              በድሮ ቀልድ እንጀምር፡- ሰውየው አክራሪ አማኝ ነው፡፡ እግዜርን ግን አያውቀውም፡፡ አንድ ቀን ከድልድይ ላይ ተንሸራቶ ትልቅ ወንዝ ውስጥ ወደቀ፡፡ ሰዎች ጮኸው ዋና የሚችል መንገደኛ ተገኘ፡፡ ዋናተኛው ልብሱን ማወላለቅ ሲጀምር አጅሬው “በፍፁም እንዳትነካኝ የሚያወጣኝ አምላክ እያየኝ ነው” በማለት ከለከለው፡፡ ትቶት ሄደ፡፡ ሌላ ዋናተኛ መጣ፡፡ አሁንም አሻፈረኝ አለ፡፡ ጋላቢው ውሃ ወደ መሃል እየጐተተው ይደፍቀው ጀመር፡፡ የከተማዋ አደጋ መከላከያ ድርጅት ሄሊኮፕተር መጣች፣ የገመድ መሰላል ላከችለት፡፡ አልሞክረውም  አለ፡፡ ወዲያው ሰመጠና  ሞተ፡፡
አምላኩን እንዳገኘውም፡-
“ምነው ጌታዬ?”…አለው
“አቤት ልጄ”
“ስመካብህ ጉድ ታረገኝ?”
“ምን አጠፋሁ?”
“ስለ ምን ከደራሽ ውሀ አላወጣኸኝም?”
“ለማንም አድርጌ የማላውቀውን እኮ ነው ያደረኩልህ”
“ምን አደረግህልኝ?”
“ሁለት ዋናተኞች አከታትዬ ላኩልህ፤ አትድረሱብኝ አልካቸው፡፡ ሄሊኮፕተር ላኩልህ፤ እንቢየው አልክ፡፡ እንግዲህ “እንትን” ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡ መቼም እኔ አልመጣ!” ብሎት እቅፍ አደረገው - እግዜር፡፡
“እንትን ማለት?” ሲል ጠየቀው፡፡
እግዜርም መለሰለት፡፡ ምን ብሎት ይሆን?
** *
ወዳጄ፡- የውሃ ታሪክ የሰው ልጅ ታሪክ ነው:: የጥፋት ውሃና ኖህ፣ ሙሴ፣ ነገደ እስራኤልና ዮርዳኖስ ወንዝ፣ ኢየሱስ፣ ዮሐንስና ጥምቀት፣ ዮናስ፣ ማዕበሉና ዓሳው፣ ህንዶችና ጋንዲ --- ኧረ ስንቱ!
ታላቁ ቄሳር ክላውዴዎስ “ወንዞቻችን እያሉ አንራብም” ሲል እንደነበር “ክላውዴዎስ አምላክ (Cloudios the God”) በተባለው መጽሐፍ ሰፍሯል፡፡ ታላቁ ዎልፍጋንግ ገተን ጨምሮ ብዙ ፀሐፍት ስለ ሬኔ ወንዝ ተቀኝተዋል፤ ለዳንዩብ ወንዝ ከተፃፉትና ከተነገሩት በተጨማሪ ታላቅ ሙዚቃ ተደርሶለታል፡፡ “Blue Danube” የሚል፡፡ ማርክ ትዌን “ሚሲሲፒ” የሚል መጽሐፍ አለው፡፡ አሌክሳንደር ሾሎኮቭ ደግሞ “የደን ወንዝ በፀጥታ ይፈሳል (And quite flows the Don”) የተሰኘ አስገራሚ መጽሐፍ ጽፏል፡፡
ወዳጄ፡- ውሃ ባለበት ህይወት አለ፡፡ ሕይወት ባለበት ደግሞ ጥበብ፡፡ ጥበብ ባለበት ስልጣኔ፣ ስልጣኔ ባለበት ዳግሞ ሰብዓዊነት አለ:: የጥንታዊቷ ፐርሽያና ጐረቤቶቿ የስልጣኔ ከፍታ የጀመረው በኤፍራጦስና ጢግሮስ ወንዞች ዳርቻ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ታላቁ አርስቶትል ለቁጥር በሚያታክት የዘመን ጉዞ ላይ በሚከሰት የተፈጥሮ ዑደት ሳቢያ አዳዲስ ባህሮች፣ አዳዲስ አህጉራት እንደሚፈጠሩ፣ የነበሩትና ያሉትም ተሸርሽረው ወይም በውሃ ተውጠው ሊጠፉ ወይም መልካችውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ በጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ካለፉት ውስጥ “ዘ ሎስት ኮንቲኔንት” የምትባለው አትላንቲክን፣ ከመጪው ደግሞ በስምጥ ሸለቆ ስንጥቅ ምክንያት ምስራቅ አፍሪካ አንድ ቀን ለሁለት ሊከፈል የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን እንደ ምሳሌ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
አርስቶትል ኢጂፕት የተሰራችው፣ ጥንታዊ ስልጣኔዋንም የገነባችው የዓባይ ወንዝ እየሸረሸረና እያግበሰበሰ ለዘመናት ባደላደለው መሬት ላይ መሆኑን፣ (Egypt is the work of the Nile, the Product of its deposits through a thousand centuries) የሰው ልጅ ስልጣኔ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ጫፍ እየደረሰ እንደ ሲሲፐስ ቋጥኝ ወደ ኋላ ሲንከባለል እንደነበረ፣ ሰውም አንዴ በድንቁርናና በጥሬነት፣ አንዴም በዕውቀትና በማስተዋል መሃል ሲዋዥቅ መስተዋሉን ጽፎልናል፡፡
“…Great catastrophes have periodically denuded the Earth and reduced man to his first beginnings, like Sisyphus. Civilization has repeatedly neared its Zenita only to fall back into barbarism” (Grant, Arstotel, 1887 p. 18)
በዚሁ መጽሐፍ ላይ ታላቁ ሊቅ፣ ተማሪው ለነበረው ንጉሥ ታላቁ እስክንድር ባቀረበው ሃሳብ መሰረት፤ ስለ ዓባይ ወንዝና ወቅት እየጠበቀ ስለሚገነፍልበት ምክንያትም መጠናቱ ተጠቅሷል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አጥኚዎች፣ በዚያን ጊዜ የሚከሰተው  የውሃ ሙላት (ጐርፍ) ምክንያት፣ ከኢትዮጵያ ተራሮች ጫፍ እየቀለጠ የሚወርደው በረዶ እንደነበር (The melting snow on the mountains of Abyssinia) ሪፖርት አድርገዋል፡፡ የጀምስ ብሩስን መጽሐፍ ባናገኘውም ምናልባት መጽሐፉ በዚህ ጥናት ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ፡፡
ወዳጄ፡- ታላቁ የዓባይ ወንዝ ከፀጋነት ወደ ራስ ምታትነት፣ ከደስታና ብልጽግና አመንጪነት ይልቅ የግጭትና ያለመግባባት ምክንያት እንዳይሆን አንዳንዶች ይሰጋሉ፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የአልጄዚራው ቴሌቪዥን Inside the story አንድ  ዘገባ አቅርቧል፡፡ ስለ ጉዳዩ ዕውቀት አላቸው የተባሉ ከሱዳን፣ ከምስራቅ ለንደን ዩኒቨርስቲና ከኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የተጋበዙ ሶስት ሰዎች ሃሳባቸውን ሲያካፍሉ ተደምጠዋል፡፡ በግብጽ በኩል ያለው ስጋት “የውሃ እጥረት ሊገጥመኝ ይችላል” የሚል እንደሆነም አውስተዋል፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ ዘጠና በመቶው የውሃ ሃብቷ የዓባይ ወንዝ ነው፡፡ እንደ መንግስት፣ እንደ ህዝብና አገር፣ ስለ ህልውና መጨነቅ ክፋት የለውም:: ክፋት የሚሆነው “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንደሚባለው ከሆነ ነው፡፡ ግብጽ “ቅር” ያላት ጠ/ሚኒስትራችን ለፓርላማ ንግግር ሲያደርጉ፤ “ግድቡን ከማጠናቀቅ ማንም አያቆመንም” ማለታቸውን ከሃይል አጠቃቀም ጉዳይ ጋር አያይዛ በመተርጐሟ ነው፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ጠ/ሚኒስትሩ ማለት የፈለጉት፤ ከድህነት ለመላቀቅ ህዝባችን የሚያደርገው ትግል አካል የሆነው፣ አንጡራ ሃብታችንን ያፈሰስንበት ግድብ ሊጠናቀቅ የቀረው አንድ ሶስተኛ ያህል ነው፡፡ እሱን ከመጨረስ የሚያግደን ነገር አይኖርም --- ነው፡፡ ይሄ ማለት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከሆኑት ግብፃውያን ጋር “ጥርስ የሚያናክስ” ችግር ገጥሞናል ማለት አይደለም፡፡ ችግሩ በትክክል የመረዳት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡
ወዳጄ፡- ካሁን ቀደም እንዳልነው፣ የዘመኑ መርህ “ኑር፣ እንኑር (Live and let live”) የሚል ነው፡፡ ግብጽን “ግብጽ”፣ ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ”፣ ቻይናን “ቻይና”፣ አውስትራሊያን “አውስትራሊያ” ያደረጋት በተፈጥሮ ዑደት የተፈጠረ አጋጣሚ እንጂ በሰዎች ምርጫና ፍላጐት አይደለም፡፡ አገርን ለመጠበቅና ራስን ለመከላከል ዝግጁ መሆን ተገቢ እንደሆነ ሁሉ ሌሎችን ህዝቦች እንደ ራስ መውደድና መረዳት ደግሞ የበለጠ ተገቢ ነው፡፡ ሐገር መውደድ የዜግነት ኃላፊነት ነው፡፡ ጭፍን አገር ወዳድነት (Blind patriotism)  ግን አደጋ ነው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የጀርመንና የጣሊያንን ህዝቦች ያሸማቀቀው፣ ጭፍን አገር ወዳድነት ያስከተለው ውድቀት እንደነበረ መገንዘብ ያስፈልጋል:: በዚህ ዘመን የሚያዋጣው በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን መፍታት መቻል ነው፡፡ “እኔ ሰው ነኝ፣ እኔ የዓለም ዜጋ ነኝ፣ የሌሎች ሰዎች ህመም የኔ ህመም ነው” ብሎ ማሰብ ሰብዓዊነትም ብልህነትም ነው፡፡ በችግራችን ጊዜ የደረሱልን የዓለም ህዝቦች መሆናቸውን አንዘነጋም፣ “We are the world” ተብሎ በመዘመሩ ነበር እርዳታ እንደ ወንዝ ሳያቋርጥ የፈሰሰብን፡፡ ምስጋና ለውዶቹ አርቲስቶች!!
ወዳጄ፡- የወንዝ ነገር ሲነሳ “አዌቱ” ትዝ አለችኝ፡፡
አዳሪ፣ ኪቶ፣ ሲሚኒ
ገራገሮቹ ውሃዎች
ፀጥ ብለው ተኝተው
ዓሶቹ ሲያንሾካሽኩ
መቼ ይሰማል ድምፃቸው?... ተብሎላታል…
እንደ ዐቅሚቲ ለእነ ዓባይ፣ አዋሽ፣ ጊቤ፣ ተከዜ፣ ባሮ ሲዘፈን፣ ሲገጠም እሷስ ለምን ይቅርባት? በውሃ ሞተር፣ በመብራት ሞተር፣ በመናፈሻ -- ጅማን “ጅማ” ያደረገችው እኮ አዌቱ ናት፡፡
እምጷ!! --- እዚህ ጋ በ “ታላቋ” አዌቱ አሳበን፣ ታላቅ ቁም ነገር ከታላቁ ጄይ ዜድ ብንማር ምን ይለናል?
“Indentity is a prison you can never escape, but the way to redeem your past is not to run from it, but to try to understand it, and use it as a foundation to grow” … ትስማሚያለሽ ወዳጄ?
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፣ እግዜር ለሰውየው፣ “ሁለት ዋናተኞችና ሄሊኮፕተር ብልክልህ አሻፈረኝ ያሰኘህ “እንትን ቢሆን ነው ብዬ ነው የጠራሁህ” ነበር ያለው፡፡ “ናፍቆት” ይሆናል ብዬ ጠርጥሬ ነው ማለቱ ነበር፡፡ ወዳጄ፡- ለማንኛውም አዌቱ መናፈሻ ጠብቂኝ!
 ሠላም!


Read 729 times