Print this page
Saturday, 09 November 2019 11:09

የስፖርት አድማስ የታሪክ ማስታወሻ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ


        ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ 43ኛ ዓመቱን ከወር በፊት ነው፡፡ በብራዚል ዋና ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ የተወለደውን ሮናልዶ፤ የዓለም የእግር ኳስ አፍቃሪ ሊዘነጋው አይችልም፡፡ ፖርቱጋላዊው ክርስትያኖ ሮናልዶ በአሁኑ ዘመን ገንኖ መውጣቱ  የትልቁ ሮናልዶን የላቀ ታሪክ ያደበዘዘው ቢመስልም፡፡ ከምንግዜም የእግር ኳስ ምርጥ አጥቂዎች በቀዳሚነት የሚነሳ ነው፡፡
ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ ሙሉ ስሙ ቢሆንም በታዋቂ የቅፅል ስሞቹ  Il Fenomeno, R9 የሚጠሩት ብዙ ናቸው፡፡ በብሄራዊ ቡድን እና በክለብ ደረጃ የሚለብሰውን 9 ቁጥር ማልያ በእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛ ክብር እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ የዓለማችን የእግር ኳስ ተንታኞች በ9 የማልያ ቁጥርና የመጫወቻ ስፍራ ፍፁም የተሳካለት ተጨዋች በማለትም መስክረውለታል፡፡ ሮናልዶ በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ምንግዜም ከሚደነቁ ኮከብ የአጥቂ መስመር ተጨዋቾች ተርታ የሚጠቀሰው ደግሞ በተጎናፀፋቸው የተለያዩ ድሎች ነው፡፡  በተጨዋችነት ዘመኑ ከብራዚል ብሄራዊ ቡድን ጋር ሁለት የዓለም ዋንጫ ድሎችን አጣጥሟል፡፡ በደቡብ አሜሪካ ሁለት የኮፓ አሜሪካ የሻምፒዮናነት ክብሮችን ከማግኘቱም በላይ የኮንፌደሬሽን ካፕ ዋንጫን ተጎናፅፏል፡፡ በክለብ ደረጃ ደግሞ በደቡብ አሜሪካ እና በአውሮፓ በሚገኙ ትልልቅ ክለቦች ሲጫወት በኮከብ ተጨዋችነትና ከፍተኛ ግብ አግቢነት ተሳክቶለታል፡፡ በብራዚል፤ በሆላንድ ፤ በስፔንና በጣሊያን ታላላቅ ክለቦች  ባሳለፈባቸው የውድድር ዘመናት የየሊጎቹን ዋንጫዎችን ሰብስቧል፡፡ በፊፋ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫን ለሶስት ጊዜያት እንዲሁም የወርቅ ኳስ ሽልማትን ለ3 ጊዜ ያሸነፈም ነው፡፡ ይህ የስፖርት አድማስ የታሪክ ማስታወሻ ብራዚላዊውን ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ የሚያስተዋውቅ ነው፡፡


        ሮናልዶ ‹‹ከየት ነህ››
እኔ ‹‹ከኢትዮጵያ ነኝ፡፡››
በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ ባስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ነው፡፡ ብራዚላዊው ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ ዓለም ዋንጫውን እንዲያሟሙቁ ከተጋበዙ የእግር ኳስ ባለታሪኮች አንዱ ነበር፡፡ በዓለም ዋንጫው የመክፈቻና የመዝጊያ ስነስርዓቶች ላይ በክብር እንግድነትና በልዩ የአምባሳደርነት ሚናው  ተሳትፏል፡፡ በሞስኮው ሉዝሂንኪ ስታድዬም ራሽያ ከሳውዲ አረቢያ በተገናኙበት የዓለም ዋንጫው የመክፈቻ ጨዋታ በፊት በነበረው ልዩ ስነስርዓት  ሮናልዶ ራሽያ 2018 የሚል ፅሁፍ ያረፈበትን ቲሸርት ከለበሰ ህፃን ጋር ወደ መሃል ሜዳ ገብቶ ነበር፡፡ 21ኛ የዓለም ዋንጫ የተካሄደባትን ኦፊሴላዊ ኳስ ይዘው ነበር፡፡ በፓኪስቷና ከተማ ሲያልኮት የሚገኘው የአዲዳስ ፋብሪካ  ያመረታት ስትሆን፤ አዲዳስ በ1970 የመጀመርያዋን ኳስ ለዓለም ዋንጫ ማቅረቡን በዲዛይኗ የምታንፀባርቅ ናት፡፡ Adidas Telstar 18 የተባለችው ኳሷ ከዓለም ዋንጫው መጀመር በፊት ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ተልካ የነበረ ሲሆን፤ ከጠፈርተኞች ጋር  ተገናኝታ  ለ4 ወራት በጠፈር ቆይታ አድርጋለች፡፡ ወደ 21ኛው የዓለም ዋንጫ የተመለሰችው ውድድሩ  1 ወር ሲቀረው ሲሆን ወደ ሞስኮ ከተመለሰች በኋላ በመከፍቻው ጨዋታ በሮናልዶ የተዋወቀች ነበረች፡፡
የ21ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ በሞስኮው ሉዚሂንኪ ስታድዬም  ፈረንሳይ እና ክሮሽያ ሲገናኙ በድጋሚ ሮናልዶ ሊውዝ ናዛሪዮ ልዩ እንግዳ ነበር:: የዓለም ዋንጫው በፈረንሳይ አሸናፊነት ተጋባድዶ  ርችት ተተኩሷል፡፡ ከዚያም የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በተገኙበት በሉዚሂኒክ ስታድዬም የተካሄደ ልዩ ስነስርዓት ነበር፡፡ ዓለም ዋንጫውን በተሳካ መስተንግዷቸው ያሳመሩትን በጎ ፈቃደኞችን ለማመስገን የተዘጋጀ ነበር፡፡ ታላላቅ የእግር ኳስ ተጨዋቾች፤ የዓለም ትልልቅ ሚዲያዎች፤ ፊፋ እና የራሽያ ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ የወከሉም ተሳትፈውበታል፡፡  የዓለም ዋንጫው ሙሉ ለሙሉ አብቅቶ ሉዚሂኒኪ ስታድዬም 4ኛ ፎቅ ላይ ከነበረው የሚዲያ ማዕከል ወደ ምድር ለመውረድ ሊፍት ውስጥ ገባሁኝ፡፡ ወዲያውኑም ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ ከማናጀሩ ጋር ተሯሩጠው ብቻዬን የነበረኩበት ሊፍት ውስጥ ገቡ፡፡ በኮሪደሩ ላይ በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ሌሎችም የስታድዬሙ ታዳሚዎች የማስታዋሻ ፎቶ ለመነሳት የፈጠሩትን ግርግር ሸሽተው ይመስላል:: ሊፍት ውስጥ ለነበርኩት ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ከሮናልዶ ጋር ፊት ለፊት መገናኘት እጅግ አስደናቂ እና የማይታመን አጋጣሚ ነበር፡፡ ከሮናልዶ እና ከማናጀሩ ጋር ወደ ምድር በሊፍት እየወረደን ቁልጭ ቁልጭ ስል ቆየሁ፡፡ ልክ ስንወርድ ትልቁን ሮናልዶ በአድናቆት ፈዝዤ መመልከቴን አቁሜ አብሬው ፎቶ ለመነሳት እንደምፈልግ በትህትና ጠየቅኩት፡፡ በመጀመርያ ላይ ላቀረብኩት ጥያቄ ትኩረት አልሰጠውም ነበር:: ማናጀሩም  በጣም ብዙ ሰው ያስቸግረው ስለነበር አልፈቀደችልኝም፡፡ ሮናልዶ ግን ጉጉቴን የተረዳው ይመስለኛል፡፡ ቆም አለና ‹‹ከየት ነህ›› Where are you from ? የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ:: የእኔም ምላሽ I am from Ethiopia ‹‹ከኢትዮጵያ ነኝ›› የሚል ነበር:: ‹ኦ ኢትዮጵያ›› አለኝና አስገራሚውን የማስታወሻ ፎቶ አብረን እንድነሳ ፈቀደልኝ፡፡
በርግጥ ዓለም ዋንጫውን ለመዘገብ በራሽያ በቆየሁባቸው 31 ቀናት ከዓለማችን ታላላቅ የእግር ኳስ ባለታሪኮች በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገናኝቻለሁ:: በቃለምልልሰ ያነጋገርኳቸው፤ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥያቄ ያቀረብኩላቸውና፤ አብሬያቸው የሰልፊ ፎቶ ከተነሳኋቸው መካከል ደግሞ የሆላንዱ ማርኮ ቫንባስተን፤ የናይጄርያው ዳንኤል አሞካቺ፤ የክሮሽያዎቹ ማንዱዚክ እና ሞድሪች ይጠቀሳሉ፡፡
ስለ ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ ማወቅ የጀመርኩት በ1998 እኤአ ላይ ፈረንሳይ ካዘጋጀችው 16ኛው የዓለም ዋንጫ ጀምሮ ነበር፡፡  በተለይ ደግሞ በ2002 እኤአ ላይ ጃፓን እና ኮርያ ባዘጋጁት 17ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ብራዚል ሻምፒዮን በሆነች ማግስት በወቅቱ የምሰራበት የስፖርት ጋዜጣ ላይ ሙሉ የህይወት ታሪኩን ፅፌ እንደነበር አስታውሳለሁ:: ስለሮናልዶ የፃፍኩትን የስፖርት ጋዜጣው አንባቢዎች ከወደዱልኝ በኋላ የታላላቅ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን የኳስ ዘመንና የህይወት ታሪክ በየጊዜው ለመፃፍ መነሻ ሆኖልኛል፡፡ ለዚህም ነው ለእግር ኳሱ የምንግዜም ኮከብ አጥቂ ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ ልዩ ክብር የሰጠሁት፡፡ ስለዚህም በሞስኮው ሉዝሂንኪ ስታድዬም የስታድዬም ውስጥ አሳንሰር ይህን የዓለማችን የምንግዜም ምርጥና ኮከብ ተጨዋች መገናኘቴ በጣም አስደስቶኛል፡፡ በስፖርት ጋዜጠኝነት ባሳለፍኳቸው 16 ዓመታት ከገጠሙኝ ክስተቶች አስገራሚው መሆኑን ብገልፅ ማጋነን አይሆንም፡፡
በክለብ ደረጃ በ4 አገራት፤ በ3 አህጉራት፤
በ7 የተለያዩ ክለቦች
በ18 የውድድር ዘመናት 347 ጨዋታዎችና 247 ጎሎች
በክለብ ደረጃ መጫወት የጀመረው በ16 ዓመቱ በብራዚሉ ክለብ ክሩዝዬሮ በ1993 እኤአ ላይ ሲሆን፤ ከዚያም በኋላ በ3 አህጉራት በመዘዋወር፤ በአራት አገራት በሚገኙ 7 የተለያዩ ክለቦች እየተጫወተ 18 የውድድር ዘመናትን አሳልፏል፡፡
በብራዚሉ ክሩዝዬሮ ከ1993 እስከ 1994 እኤአ በ14 ጨዋታዎች 12 ጎሎች፤ በሆላንዱ ፒኤስቪ አየንድሆቨን ከ1994 እስከ 1996 እኤአ በ46 ጨዋታዎች 42 ጎሎች ፤ በስፔኑ ባርሴሎና ከ1996 እስከ 1997 እኤአ በ37 ጨዋታዎች 34 ጎሎች፤ በጣሊያኑ ኢንተርሚላን ከ1997 እስከ 2002 እኤአ በ68 ጨዋታዎች 49 ጎሎች፤ በስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከ2002 እስከ 2007 እኤአ በ127 ጨዋታዎች 83 ጎሎች፤ በጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ከ2007 እስከ 2008 እኤአ በ20 ጨዋታዎች 9 ጎሎች እንዲሁም በብራዚሉ ኮረንቲያስ ከ2009 እስከ 2011 እኤአ በ31 ጨዋታዎች 18 ጎሎች አስመስግቧል፡፡ በአጠቃላይ በብራዚል፤ በሆላንድ፤ በስፔንና ጣሊያን ክለቦች ባሳለፈባቸው 18 የውድድር ዘመናት 343 ጨዋታዎችን አድረጎ 247 ጎሎቹን በስሙ የታሪክ መዝገብ ላይ አስፍሯል፡፡
በዓለም አቀፍ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ በከፍተኛ ሂሳብ ተደጋጋሚ ሪከርዶች
እስከ 124 ሚሊዮን ዶላር
ሮናልዶ በተጨዋችነት ዘመኑ ልዩ ብቃት ላይ በነበረባቸው ዓመታት በዓለም አቀፍ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ በከፍተኛ ሂሳብ ተደጋጋሚ ሪከርዶችን አስመዝግቧል፡፡ በአንዱ የውድድር ዘመን በዝውውር ገበያው የነበረው የዋጋ ተመን እስከ 150 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ ከብራዚል ወደ ሆላንድ፤ ከሆላንድ ወደ ስፔን፤ ከስፔን ወደ ጣሊያን፤ ከጣሊያን ወደ ስፔን ከዚያም ወደ ብራዚል ክለቦች በፈጨማቸው ዝውውሮች ከ124 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተከፍሎበታል::  በምርጥ አቋሙ ላይ በነበረባቸው የውድድር ዘመናት ዓመታዊ ደሞዙ በዚያን ወቅት ከፍተኛ የሚባለው እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡
በ1996 እኤአ ላይ የሆላንዱን ክለብ ፒኤስቩ በመልቀቅ ወደ ስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ሲዛወር ለዝውውር የወጣበት 19.5 ሚሊዮን ዶላር ሂሳብ በተጨዋቾች ዝውውር ገበያው ያስመዘገበው የመጀመርያው  ክብረወሰን ነበር፡፡ ከዚያን በኋላም ባርሴሎናን በመልቅቅ ወደ ጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ሲቀላቀል 27 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሎበት በመሆኑ አሁንም በወቅቱ ለዓለም እግር ኳስ አዲስ ክብረወሰን ሊሆን ችሎ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታም ከማራዶና በኋላ ለሁለት ጊዜያት የዓለም የተጨዋቾች የዝውውር ሂሳብ ሪከርዶችን በማስመዝገብ ሁለተኛው ተጨዋች ያደረገው ነበር፡፡ ኢንተር ሚላንን በመልቀቅ ወደ ስፔን ሲመለስ በወቅቱ የጋላክቲኮዎች ስብስብ የነበረውን ሪያል ማድሪድ የተቀላቀለ ሲሆን በወቅቱ ለዝውውር የተከፈለው 46 ሚሊዮን ዩሮ አንዲስ ክብረወሰን ከመሆኑም በላይ በመጀመርያው ቀን በሪያል ማድሪድ ክለብ የሚለብሰው ማልያው የተሸጠበት ብዛት ሪከርድ ሽያጭ የተገኘበት መሆኑ ይታወሳል፡፡
በብሄራዊ ቡድን ደረጃ 2 የዓለም ዋንጫ ድሎች
ከፔሌ ቀጥሎ ከፍተኛ የብራዚል አግቢ
ለብራዚል መጫወት የጀመረው በ1993 እኤአ ላይ ለ17 ዓመት በታች ቡድን በመሰለፍ ሲሆን በ1996 ለብራዚል ከ23 ዓመት በታች ቡድን መጫወቱን ቀጥሎ ዋናውን ብሄራዊ ቡድን በ1994 እኤአ ላይ በመቀላቀል በወቅቱ በአሜሪካ በተካሄደው 15ኛው የዓለም ዋንጫ ብራዚል ሻምፒዮን ስትሆን በአንድም ጨዋታ ባይሰለፍም የቡድኑ ተመራጭ ሆኖ ነበር፡፡ በብራዚል ብሄራዊ ቡድን እስከ 2011 እኤአ ድረስ ለ17 ዓመታት ለመጫወት ሲበቃ በአጥቂ መስመር እየተሰለፈ 91 ጨዋታዎችን አድርጓ 58 ጎሎችን አስመዝግቧል፡፡ በ6 ታላላቅ የእግር ኳስ ውድድሮች 5 ዋንጫዎችንም ሊሰበስብ በቅቷል፡፡ በ1994 እና በ2002 እኤአ ሁለት የዓለም ዋንጫ ድሎች፤ በ1997 እና በ1999 እኤአ ሁለት የኮፕአሜሪካ ዋንጫዎችን፤ በ1997 እኤአ ላይ የፊፋ ኮንፌደሬሽን ካፕን በማሸነፍ ነው፡፡ እንዲሁም በ1996 እኤአ በኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፏል፡፣፡ በብራዚል ብሄራዊ ቡድን ሲጫወት በ1993 በሀ 17 ቡድን በ7 ጨዋታዎች 5 ጎሎች፤ በ1996 በብራዚል ሀ23 ቡድን በ8 ጨዋታዎች 6 ጎሎች እንዲሁም  ከ1994 እስከ 2011 እኤአ በዋናው ብሄራዊ ቡድን በ98 ጨዋታዎች 62 ጎሎችን አስመዝግቧል፡፡ በሶስት ዓለም ዋንጫዎች የተሳተፈ ሲሆን ለብራዚል 15 የዓለም ዋንጫ ጎሎች በማስመዝገብ በውድድሩ ከፍተኛ ግብ አግቢነት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ከብራዚል ብሄራዊ ቡድን ሲሰናበትም  በ62 ጨዋታዎች ለአገሩ 68 ጎሎችን በማስመዝገብ ከፔሌ ቀጥሎ በታሪክ ሁለተኛው ተጨዋች በመሆን ነበር፡፡
በእድሜ ወጣቱ የዓለም ኮከብ
በፊፋ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫ ሶስት ጊዜ ካሸነፉ ምርጥ ተጨዋቾች አንዱ ሲሆን (1996, 1997 and 2002) ለ3 ጊዜያት የባሎን ደኦር ወይም የወርቅ ኳስ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በ1996 እኤአ በባርሴሎና፤ በ1997 እኤኤ በኢንተርሚላን እንዲሁም በ2002 እኤአ በሪያል ማድሪድ ክለቦች እየተጫወተ የተሸለማቸው ናቸው፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ደግሞ ለ2 ጊዜያት በ1997 በኢንተርሚላን እንዲሁም በ2002 እኤአ በሪያል ማድሪድ ክለቦች እየተጫወተ ተሸልሟል፡፡
ጫማውን ሲሰቅል
በ2011 እኤአ ላይ ከእግር ኳስ በመሰናበት ጫማውን ሲሰቅል በጉዳቶች መደራረብ እና በአኗኗር ሁኔታው ካጋጠመው ውፍረት ጋር በተያያዘ ነበር:: በወቅቱ ጡረታ ስለመውጣቱ ‹‹በጣም ደስተኛ ከሚያደርገኝ ሙያ መሰናበት አሳዛኝ ነው፡፡ በአዕምሮዬ የጨዋታ ዘመኔን መቀጠል እፈልግ ነበር፡፡ መላው ተክለሰውነቴ ግን ይህን ሙሉ ብቃት አልነበረውም፡፡ አዕምሮዬ ጠንካራ ቢሆንም ሰውነቴ ግን ጫና መቋቋም አልቻለም:: በቃኝ ማቆም ግድ ሆነብኝ፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡ ከብራዚል ብሄራዊ ቡድን በክብር የተሰናበተው ለዋናው ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ከተሰለፈ ከ5 ዓመታት በኋላ በሳኦፓውሎ ብሄራዊ ቡድኑ ከሮማኒያ ጋር ባደረገው ጨዋታ ሲሆን ለ15 ደቂቃ ተሰልፎ ስንብቱን አድርጓል፡፡
የተጨዋችነት ዘመኑ ካበቃ በኋላ ገቢው፤ ናይኪ
የስፖርት ትጥቅ አምራቹ ኩባንያ ናይኪ ዋናው ስፖንሰሩ ሲሆን በ1996 እኤአ ላይ ከኩባንያው ጋር በ10 ዓመት የኮንትራት ውል እስከህይወት ዘመኑ መጨረሻ ስፖንሰር አድርጎት 180 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሎታል፡፡ በ1996 እኤአ ላይ ናይኪ Nike Mercurial R9 የተባለ ታኬታ በስሙ ሰርቶለታል፡፡
በትውልድ ከተማው ሪዮ ዲጀኔሮ የዋጋ ግምት ያለው መኖርያ ያለው ሲሆን Ferrari, Audi A8, Lamborghini and Mercedes-Benz.የተባሉ ውድ መኪናዎችም ባለንብረት ነው፡፡ በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም UNDP በጎ ፈቃድ አምባሳደርነቱን የቀጠለ ሲሆን በዚሁ ዓለም አቀፍ ተቋም ሲያገለግል ከ18 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ብራዚል ባስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ የውድደሩ አምባሳደር ሆኖ ሲያገለግል ጫማወን ከሰቀለ ወዲህ ደግሞ  9ine Sports and Entertainment በተባለ ኩባንያ 45በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ይዞ እየሰራ ሲሆን በአሜሪካ ሶከር ሊግ Fort Lauderdale Strikers በተባለ ክለብም ባለድርሻ ነው፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ በእግር ኳስ ዘመኑ ወሳኙን ምዕራፍ ከፍቷል፡፡ በስፔኑ ክለብ ሪያል ቫላዶሊድ ክለብ ባለቤትነት ስፖርቱን ለማገልገል በመወሰኑ ሲሆን፤ በወቅቱ የክለቡን 51 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ የገዛው በ30 ሚሊዮን ዩሮ ነበር፡፡‹‹ለዚህ ሃላፊነት ለመድረስ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ያሳለፍኩት ተመክሮ እና ስልጠና የላቀ ነው፡፡ እግር ኳስ የሙያ ፍቅር ነው:: በጋራ ሆነን ምርጥ ቡድን ለመገንባት እንሰራለን፡፡ አስተዳደራችንም ግልፅ እና ዘመናዊ አሰራር ያለው ነው፡፡›› ማለቱ ተወስቷል
ታላላቅ ተጨዋቾች ስለሮናልዶ ከተናገሩት
‹‹ሮናልዶ ማንም አይቶት የማያውቀውን ነገር ይሰራል፡፡ የመሃል አጥቂ መስመር ተጨዋችን ሚና ያጎለበቱት እሱ ሮማሪዮና ጆርጅ ዊሃ ናቸው፡፡ ከፍፁም ቅጣት ክልል ወጥተው መሃል ሜዳ ድረስ በመምጣት ኳስ ይቀበላሉ፤ ተመልሰው በክንፍ በኩል ይገሰግሳሉ፤ የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮችን በዙርያቸው ሰብስብው በልዩ የአብዶ ችሎታቸው ማምለጥ ይችላሉ፡፡››
ቲዬሪ ኦንሪ
‹‹በጣም ልክ የሆነ የኳስ ቁጥጥር በፍጥነት በማድረግ እንደሱ የሚችል አልገጠመኝም፡፡ እሱን መመልከት የቪድዮ ጌም ጨዋታ ላይ ያለን ገፀባህርይ እንደማየት ነው››
ማርሴይ ዴሳይ
‹‹በህይወት ዘመኔ አይቼው የማላውቅ ምርጥ አጥቂ ነበር፡፡ ፈጣን ነው ከምንም ተነስቶ ጎል ያስቆጥራል፡፡ የሚመታውን ሹት ማንም ሲያደርገው አላውቅም››
 ሊዮኔል ሜሲ
‹‹ሁሉንም ያሟላ ምርጥ አጥቂ፤ እንደ ክንፍ መስመር ተጨዋች አብዶ ይሰራል እንደአጭጥር ርቀት ሯጭ ይፈተለካል፡፡ እንደሱ በአጥቂዎች ላይ ዘላቂ ተፅእኖ የፈጠረ የለም፡፡ ››
ዝላታን ኢብራሞቪች
‹‹ በመከላከል ለማቆም በህይወቴ ካቃተኝ ዋናው ነው፡፡ ልታቆመው በፍፁም አትችልም››
ፋብዮ ካናቫሮ


Read 1469 times