Saturday, 09 November 2019 11:32

“ዕድሜ ጥሩ ነው አያራርቅም ዕድሜም በማዳን ሰው አይጣላም”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አያ አንበሶ የዱር አራዊትን አቤቱታ ለማዳመጥ በትህትና ተቀመጠ፡፡
ጦጢት ተነስታ “አያ አንበሶ ያስፈራሩናል፡፡ የልባችንን መናገር አልቻልንም” አለች፡፡
አያ ዝንጀሮ፡- “ምንም እንኳን የጦጢትን ያህል ፍርሃት ባይገባንም መፍራታችንማ መቼም አልቀረም!”
አያ ነብሮ፡- “አያ አንበሶን መፍራት አለብን ብዬ አላምንም! ምክንያቱም እኛ በሺዎች የምንቆጠር ነን፡፡ አያ አንበሶ ግን አንድና አንድ እንስሳ ነው፡፡
አያ ዝሆን፡-
“የአያ ነብሮ ንግግር ማርኮኛል፡፡ እኛ ስንት መንገድ ተጉዘናል ኢትዮጵያን ለማሸነፍ፡፡ አውቀን ይሁን ሳናውቅ ሁሌ እኛ እናሸንፋለን ብለን ብዙ ፈግተናል፡፡ ከተሳሰብን ግን ብዙ መንገድ የመሄድ ዕድል አለን፡፡ ብዙ ችግር እንፈታለን፡፡ ብዙ ተስፋ እንሰንቃለን፡፡
አያ አንበሶ፡-
“ይሄንን እንደ ዱለታ ነው የማየው፡፡ እኔ አንበሶ ጥፋትን ከልማት የማልለይ ይመስላችኋል? በጉልበት ልሠራው የማልችልስ ይመስላችኋል? እችላለሁ!!
ሁሉም፤ በህብረት፡-
“አያ አንበሶ፤ አሁንም ቢሆን በፍቅር፣ በስምምነት፣ በአንድነት በህብረት እንቁም፡፡ ጠላትና ወዳጅን በአግባቡ እንለይ ጥያቄዎቻችንን ለይተን እናሳይዎ! አግባብ ያለው መልስ ባናገኝ እንኳ፤ ሀሳባችን ከመልሳችን በታች እንደማይሆን እናውቃለን፡፡ ስለዚህ አያ አንበሶ፤ የህብረት መልስ እንዳለን እናስብና እንተማመን!!
***
ብዙ ሰው ይለናል፣ ይህ ያ ነው፣ ያ ያ ነው
ግን ከተሳሰብን፣ ቋንቋችን አንድ ነው!
***
ዕውነትን ፍለጋ በቆፈርነው ምድር
እህል ዘራንበት በልተን እንድናድር!
ይህ ግጥም የጥንት የጠዋት ነው፡፡ በሙሉ ዐይኑና በሙሉ ብሌኑ ለሚያየው ግን ከሙሉ በላይ ነው! ምክንያቱም አንድ ሙሉ ትውልድ በዚህ ግጥም ውስጥ ተሰድሯል - ስለአለፈ ትውልድ ሊመሰክር አለሁ ይላል፡፡
የወትሮዎቹን ገጣሚያን ደራሲ ከበደ ሚካኤልንና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማን በዚህ ወቅት መጥቀስ የግድ ይመስለናል!
“ለሁሉም ጊዜ አለው” ብሏል ሰለሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት እራሱ እሚሞት ምን ጊዜ እንደሆን?
(ከበደ ሚካኤል)
በሌላኛው ወገን ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ፡-
“ቀማኛን መቀማት ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ የድሆችን ጭንቅ
በኔ ቤት ጽድቅ ነው አንድ ሰው ይሙት
አንድ መቶ ሺ ሰው ኪኖር በምጽሞት፡፡
(ባለካባና ባለዳባ)
በሌላ ወገን የወሬ ሱስ፣ የነገር ሱስና የሀሜት ሱስ የት እንደሚያደርሰን አይታወቅም፡፡ አቤ ጉበኛ ጠዋት ነው ነገሩ የገባው፡፡ ለዚህ ነው ገና በማለዳ፤
“ሰማይን በአንካሴ ቆፍሬ ቆፍሬ
ለወሬ ሱሰኞች አገኘሁኝ ወሬ” ብሎ የፃፈው፡፡
 (መስኮት)
ፀጋዬ ገ/መድህንም በበኩሉ፤
“ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው ሚቆጨኝ
ዛሬ ለወግ ያደረግሺው ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞም የሠለጠነ እንደሁ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል”
ሐምሌት (ሼክስፒር - ፀጋዬ ገ/መድህን እንደተረጐመው)
ከላይ እንዳየነው ሁሉ ሰው ለትግል ተነሳ፡፡ ያን የትግል ሜዳ ግን የእህል መዝሪያ አደረገው::
ንጉሥ ሰለሞን፤ በምንም ስሜት ይበለው፣ የተለመደውን አካሄድ መጠየቅ ጤናማ አካሄድ ነው::  ይሄ መንፈስ ያለጥርጥር መልካም ሰፈር ያደርሰናል፡፡
የድሆችን ጭንቅ ማቃለል ድካም አለበት
ለወሬ ሱሰኞች ሰማይ ተቆፍሮም ወሬ እንደሚገኝ ማወቅ ፀጋ ነው፡፡
እንግዲህ ሰው ቢገባውም ባይገባውም፤ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ዋጋ አላቸው ብለን እናስባለን፡፡
ግጭቶች በየቦታው መንፈሳቸው አይቀርም፡፡
ህይወትም በየትም አቅጣጫ መፍሰሷ ግድ ነው
ዕድሜውን ይሰጠን እንጂ ሁሉንም ያሳየናል፡፡ ሁሉም ነገር ይለወጣል፡፡ ከለውጥ ህግ በስተቀር የማይለወጥ ነገር የለም (Everything changes except the law of change)
እስከዛሬ ያለፈው ሁሉ ለዛሬው ቀን ምክንያት ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ለነገ ምክንያት ነው፡፡
ዞሮ ዞሮ፤
“ዕድሜ ጥሩ ነው አያራርቅም
ዕድሜም በማዳን ሰው አይጣላም”
የሚባለው ለዚህ ነው፡፡

Read 11446 times