Saturday, 09 November 2019 11:33

በ‹‹ሰኔ 15 ግድያ ብንጠረጠርም የታሰርነው በማንነታችን ምክንያት ነው››

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ሰኔ 15 በአማራ ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎችና በመከላከያ አዛዦች ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ ተጠርጥረው ታስረው የነበሩና ከአራት ወራት በኋላ የተለቀቁት ግለሰቦች፤ “የታሠርነው በማንነታችንና በምናቀርበው የተለየ ሃሳብ ነው” ሲሉ ትናንት በባለ አደራው ም/ቤት ቢሮ ተገኝተው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
አቶ ማስተዋል አረጋ የገቢዎች ሚኒስቴር ሠራተኛ እንደነበረ ጠቅሶ፣ በሚሠራበት መስሪያ ቤት በሚያነሳቸው ሃሳቦች እና በብሔር ማንነቱ ምክንያት መታሰሩን ገልጿል፡፡ ይሄንንም በምርመራ ወቅት ከቀረበለት ጥያቄ መረዳቱን ተናግሯል፡፡
ድርጊቱ ተፈፀመ ከተባለ በኋላ ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ‹‹በዚሁ ሰበብ አስራችሁ እሹት›› የሚል መመሪያ ከገቢዎች ተሰጥቶ መታሠሩንም በመግለጫው ላይ አስረድቷል፡፡
‹‹ለ33 ቀናት ጨለማ ቤት ነበርኩ›› ያለው አቶ ማስተዋል፤ በምርመራ ወቅት አንድም ጊዜ ከግድያው ጋር የተያያዘ ጥያቄ እንዳልቀረበለትም ገልጿል፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ እንደሆነ የገለፀው አቶ ህሩይ ባዩ በበኩሉ፤ ‹‹ጠ/ሚኒስትሩ ከፍትህ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ባነሳሁት ጥያቄ ነው የታሰርኩት እንጂ ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር በተያያዘ አይደለም” ብሏል፡፡
በወቅቱ ጠ/ሚኒስትሩ “አንተ ፖለቲከኛ ፖለቲከኛ ትሸተኛለህ” ብለውኝ ነበር ያለው የህግ ባለሙያው ህሩይ፤ በታሰርኩበት ወቅት ከግድያው ጋር በተያያዘ ምንም ምርመራ አልተደረገልኝም ብሏል፡፡
የአብን የፋይናንስ ሃላፊ መሆኑን የገለፀው አቶ ሲያምር ጌቴ፤ የአብን አባልና የፓርቲው  የድጋፍ ገቢ አሰባሳቢ በመሆኑ ድርጅቱን ለመጉዳት ሆን ተብሎ እንደታሠረ ገልጿል፡፡ በምርመራ ወቅትም “የባላደራው ም/ቤት አባል ናችሁ ወይ? ዐቢይን ትደግፋላችሁ? አብን ድጎማውን ከየት ነው የሚያገኘው?” የሚሉና ሌሎች ከግድያው ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ጥያቄዎች እንደቀረቡለት ነው ያስረዳው - የአብን አባል የሆነው አቶ ሲያምር ጌቴ፡፡
ከእስር የተፈቱት ተጠርጣሪዎች ከጐናቸው የቆሙትን ወገኖች ያመሰገኑ ሲሆን በዋናነትም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Read 1183 times