Saturday, 09 November 2019 11:47

የቤተ ክርስቲያኒቱና ምዕመኖቿ መብት ተቆርቋሪ ኮሚቴ፤ ከመንግስት በቂ ምላሽ አላገኘሁም አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  በቤተ ክርስቲያኒቱና ምዕመኖቿ ላይ የሚደርሰው ጥቃትና እንግልት በተለይም በኦሮሚያ ክልል መጠናከሩን ያስታወቀው የመብት ተቆርቋሪ ኮሚቴው፤ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል በመንግስት ላይ የተለያዩ ግፊቶችን ለማድረግ መወሰኑን አስታወቀ፡፡
ኮሚቴው ትናንት ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫው፤ ቀደም ሲል በቤተክርስቲያኒቱ ጥያቄዎች ላይ ከመንግሥት ጋር ችግሮችን ተወያይቶ ለመፍታትና ምላሽ ለማሰጠት እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ቀነ ገደብ አስቀምጦ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከሚመለከታቸው የክልልና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሲወያይ መቆየቱን ይገልጻል፡፡
በዚህ ውይይትም አብዛኞቹ ችግሮች መኖራቸውን በማመን፣ የማስተካከያ ርምጃዎችን ለመውሰድ መተማመን ላይ መደረሱንና የማስተካከያ እርምጃዎቹን በአፈፃፀም ሲከታተል መቆየቱን የጠቀሰው ኮሚቴው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየሰጠ ካለው ተግባራዊ ምላሽና በአንፃራዊነት በአማራ፣ በደቡብ፣ በሃረርና በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከተሰጡት በጎ ምላሾችና ጅምር ስራዎች በቀር ስምምነቱ በተሟላ ሁኔታ ሊተገበር አልቻለም ብሏል፡፡
‹‹እንዲያውም በአንዳንድ ክልሎች ከውይይቱ በኋላ ጥቃቶቹና በደሎቹ ከቀድሞው በከፋ ሁኔታ ተባብሰው ቀጥለዋል›› ያለው የኮሚቴው መግለጫ፤ በዋናነት የኦሮሚያ ክልል ችግሮችን ለመፍታት ለዘብተኝነት አሳይቷል ብሏል፡፡
በክልሉ ምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ፣ ባሌ ሮቤ፣ ምዕራብ አርሲ፡- ዶዶላና ኮፈሌ፣ ምሥራቅ ሸዋ፡- አዳማና ቢሾፍቱ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ፡- ሰበታና ወለቴ በሰሞኑ ጥቃት ‹‹ከ40 በላይ ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ በገጀራ ተቀልተው፣ ሰውነታቸው ተቆራርጦና ተቃጥሎ፣ በዱላ ተቀጥቅጠው ተገድለዋል›› ብሏል - በመግለጫው፡፡
‹‹እምነታቸውን እንዲለውጡ የተገደዱ፣ አስክሬናቸው በየሜዳው እንዲጎተት የተደረጉ ሰማዕታት በርካቶች ናቸው›› ያለው መግለጫው፤ ‹‹ድርጊቶቹ ሲፈፀሙ የመንግሥት አስተዳደር አካላትና የፀጥታ ሀይሎች በቸልታ ተመልክተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች እንዲያውም የፀጥታ አካላት በእኩይ ድርጊቶቹ ተሳታፊ ነበሩ›› ብሏል፡፡
መንግስት ለቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊና ሥርዓታዊ የደህንነት ዋስትናን የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን በመውሰድ ሕግ የማስከበር ግዴታውን ሲወጣ ብቻ መፍትሄ ሊገኝ እንደሚችል የገለፀው ኮሚቴው፤ የመንግስት የመፍትሄ እርምጃዎች እውን እስኪሆኑና እስኪተገበሩ ድረስ የተለያዩ ግፊቶችን ለማድረግ መወሰኑን ጠቁሟል፡፡
በቀጣይ የሚያደርጋቸውን የሰላማዊ ትግልና እርምጃዎች በዝርዝር ለይቶም ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ኮሚቴው በመግለጫው አስገንዝቧል፡፡     

Read 9649 times