Saturday, 09 November 2019 11:49

ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

ብዙዎች እንደሚስማሙት ይህ ወቅት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ትልቅ የፈተና ወቅት ነው፡፡ መሻገራችን አይቀርም - እንሻገረዋለን፡፡ እስከምንሻገረው ግን ብዙ ብዙ መስዋእትነት ያስከፍለናል፡፡ ሰሞኑን በሀገራችን በርካታ ሁኔታዎች ተከስተዋል:: ከእነዚህ ክስተቶች መካከል ጎላ ያሉ ናቸው ብየ ባሰብኳቸው ላይ በዚች መጣጥፍ ትኩረት ላደርግባቸው ወደድሁ፡፡ በየንዑስ ርእሱ በተናጠል እንደሚከተለው አቀርባቸዋለሁ፡፡
ሰደድ እሳትና ውኃ ሙላት
በቀዳሚነት የማቀርበው ሰደድ እሳትን በተመለከተ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በትግራይ ክልል በቃፍታሽራሮ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙት ተፈጥሯዊ ሀገራዊ ሀብቶች አንዱ “የቃፍታሽራሮብሔራዊፓርክ” ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ብሔራዊ ፓርክ ዝኆንን ጨምሮ የተለያዩ የዱር እንስሳትንና አእዋፋትን በውስጡ የያዘ ፓርክ ነው፡፡ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የተከለለው ይህ ፓርክ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡
ሰሞኑን በሀገራችን ከተከሰቱ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች አንዱ የሰደድ እሳት መከሰት ነው:: ሰደድ እሳቱ የተነሳው ደግሞ የትግራይ ክልል ብቸኛ ፓርክ በሆነው በዚሁ “በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ” ላይ መሆኑ በመገናኛ ብዙሃን ተነግሯል፡፡ ለትግራይ ክልል “አንድ ለእናቱ” የሆነው ይኸው ብቸኛ የክልሉ ፓርክ አርባ ያህል ጠባቂዎች ያሉት ቢሆንም የእሳት ሰለባ ሆኗል፡፡
መገናኛ ብዙሃን እንደነገሩን ከሆነ ዛሬ ይህ ፓርክ በሰደድ እሳት እየተለበለበ ነው:: ከፍተኛ የውድመት አደጋ ተጋርጦበታል:: “ህገወጦች የለኮሱት እሳት” መሆኑንና ይህም እሳት ከሺ በላይ ሄክታር መሬት ማጥፋቱን መገናኛ ብዙሃን እየነገሩን ነው፡፡ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል እና የመከላከያ ሰራዊት በስፍራው ደርሰው የመከላከል ስራ እየሰሩ መሆኑንም ሰምተናል:: ይህንን ሰደድ እሳት በተመለከተ “የህገወጥ እሳት ጫሪዎች ጉዳይ በአስቸኳይ እልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡ቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ብቻውን ወርቅ ነው፡፡ እሳት ለሚበላው ወርቅ ሳንባ የሆነውን ተፈጥሮ በእሳት ማስበላት አይጠቅምም” የሚል አስተያየት ከአንድ ተጓዥ ጋዜጠኛ ማስታወሻ ላይ አንብቤያለሁ፡፡ ይህንን ሳነብ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር “ህገወጥ እሳት ጫሪዎች” የተሰኙ ወገኖች መኖራቸውን ነው:: እነዚህ የጥፋት ኃይሎች እነማን ናቸው? ይሄ ግልጽ መሆን አለበት፡፡
ብዙ ጊዜ የሰደድ እሳት የሚከሰተው ሞቃታማ በሆኑት በግንቦትና በሰኔ ወራት ነው፡፡ በዚህ በጥቅምት ወር ባልተጠበቀ ሁኔታ መከሰቱ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን ተመሳሳይ ቃጠሎ በአማራ ክልል በራስ ደጀን አካባቢ መከሰቱን ሰምተናል፡፡ አሁን ደግሞ በትግራይ ተከሰተ፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ በሌሎች ፓርኮቻችን ላለመከሰቱ ዋስትና የለንም፡፡ ለማንኛውም የጥንቃቄ ደወሉ በሁሉም አካባቢዎች ቢሰማና አስፈላጊው ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው:: እስካሁን ለደረሱት ቃጠሎዎች መንስዔ በሚመለከታቸው አካላት ሊጣራና የእርምት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡
ተፈጥሯዊ አደጋዎች “በህግ አምላክ” ተብለው የሚገቱ አይደሉም፡፡ ጥፋታቸውም የከፋ ነው፡፡ ለመከላከል የሚወስደው ጊዜና ጉልበት የትየለሌ ነው፡፡ ዘንድሮ እየወረደብን ያለው መከራ ብዙ ነው፡፡ ህዝብን ያንገላታው ሰደድ እሳት ብቻ አይደለም፡፡ የውኃ ሙላትም ያጥለቀለቃቸው አካባቢዎች ነበሩ፡፡ በሶማሌ ክልል ጎርፍና የውሃ ሙላት በሰውና በንብረት ላይ የከፋ አደጋ እያደረሰ መሆኑንም ሰምተናል:: እዚያም አዝመራ እየወደመ ነው፡፡ በደጋማው አካባቢዎች የክረምቱ ወራት ቢጠናቀቅም በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ ወቅት የዝናብ መጠን የሚጨምርበት መሆኑ ይነገራል፡፡ እናም በነዚህ አካባቢዎች አስፈላጊው ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው፡፡
የአንበጣ መንጋ
ሰሞኑን ትኩረት ከሳቡ ሀገራዊ ጉዳዮች አንዱ የአንበጣ መንጋ በሀገሪቱ መታየቱ ነው፡፡ መነሻውን ሶማሊያ እና የመን ያደረገ የአንበጣ መንጋ ወደ ሀገራችን ከገባ ቀናት ሳይሆኑ ሳምንታት መቆጠር ጀምረዋል፡፡ ይህ አውዳሚ የሆነ የአንበጣ መንጋ በትግራይ፣ በአፋር፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ታይቷል፡፡ ለአጨዳ በደረሰ አዝመራ ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ነው፡፡
ይህንን የአንበጣ መንጋ በሁለት መንገዶች ማጥፋት እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ:: ይኸውም በዘመናዊ መንገድ ለማጥፋት በሄሊኮፕተር የታገዘ የመርዝ ርጭት ማካሄድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ባህላዊ ዘዴ የአንበጣመንጋውንበጥይት ጩኸት፣በመኪና ጥሩምባ፣የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማንኳኳትና ከፍተኛ ድምጽ በማሰማት አንበጣውን ፋታ በመንሳት ማባረር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መላው ህዝብ ሴት ወንድ፣ ልጅና አዋቂ ሳይል በነቂስ ወጥቶ መረባረብ አስፈላጊ ነው፡፡
የበርሃ አንበጣ አሸዋ ላይ እንቁላል በመጣል ነው የሚራባው፡፡ አንድ አንበጣ እስከ 150 አንበጣዎችን ይፈለፍላል፡፡ ግን ሁሉም እንድጉም፡፡ ለማደግ በጣም ምቹ ሁኔታዎች መኖር አለባቸው፡፡ ለአንበጣ ምቹ መራቢያ የሚሆነው አሻዋማ የሆነና በጣም ሙቀት ያለበት ቆላማ ኣከባቢ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ያደገ አንበጣ ነው፡፡
አሁን ወደ ሀገራችን የገባው አንበጣ በምቹ አካባቢዎች ተፈልፍሎና አድጎ የመጣ በመሆኑ መራባቱ ስጋት አይሆንም ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ ነገር ግን ያደገ አንበጣ አዝመራን ሙሉ በሙሉ በማውደም ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ትልቅ አቅም አለው፡፡ መድኃኒት መርጨት በሌሎች እንስሳት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ጥንቃቄን እንደሚፈልግም ይናገራሉ ባለሙያዎቹ፡፡ ብዙ አድካሚና ሰፊ የሰው ኃይልን ቢጠይቅም ባህላዊ ዘዴው በተለይ ላደገ አንበጣ ማስወገድ ተመራጭ ነው፡፡
አንድ ወዳጄ በትግራይ የነበረውን ተሞክሮ እንዲህ በማለት ጽፎልኛል፤ “አሁን ወደ እኛ እየመጣ ያለው የመጨረሻ ትልቁ ደረጃ ደርሶ ነው። በጣም እህል አውዳሚ ነው፡፡ ሲበላ ሙሉ ለሙሉ የማውደም አቅም አለው። የመጀመርያ ዙር በአፋርና በራያ አዘቦ ነበር ወደ ትግራይ የገባው፡፡ የመጨረሻ ያለቀው ዓዲግራት ላይ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ጥዋት ከንጋቱ 10 ሰኣት ጀምሮ በእጅ መርጭያ መሣሪያ መድሃኒት ይረጭበታል፡፡ ከዛም ከመንደር መንደር ባልተቋረጠ ሁኔታ አንድም ቦታ ሳያርፍና  በጥይት፣ በኣምቡላንስ ድምፅ፣ በርችት፣ ቆርቆሮ በማንኳኳት፣ የሲኖ ትራክ  ክላክ  እና ሌሎች ድምፅ የሚያወጡ ነገሮችን እየተጠቀምን አዝመራ እንዳይበላና በጉዞው እንዲደከም በማድረግ ጭምር አባረርነው:: በነጋታው የተራረፉትን ለማጥፋት እንደገና መድኃኒት በመርጨት ለማትፋት ጥረት ተደርጓል” ብሎኛል፡፡
በሰሜንና በደቡብ ወሎ በተመሳሳይ ሁኔታ በድምፅ የማባረር ስራ እየተሰራ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ የአንበጣ መንጋው ወደ ደጋማ አካባቢዎች አይሄድም፡፡ ቢሄድም ቅዝቃዜው ስለማይመቸው ያልቃል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ሌሎች ቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች መዛመቱ ግን የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለሆነም የአንበጣ መንጋው ከተከሰተባቸው አካባቢዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት በማድረግ ከላይ የተጠቀሱትን ባህላዊም ዘመናዊም የመከላከል ዘዴዎችን እንደ አስፈላጊነቱ በመጠቀም ለማስወገድ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተማሪዎችና የከተማ ነዋሪዎች ጭምር ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኢኮኖሚ መድቀቅና ምርጫ
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ሰው ሰራሹም ተፈጥሯዊም አደጋ ተጋርጦብናል:: በበኩሌክፉ ስራችን ፈጣሪን እንዳስቆጣ አስባለሁ፡፡ በእሳትም፣ በውኃም፣ በአንበጣም እየቀጣን ያለው ለዚሁ ይመስለኛል፡፡ ተጸጽተን ከክፉ ተግባራችን ካልተመለስን ቅጣቱ በእሳትና በውኃ አሊያም በአንበጣ መንጋ የሚቆም መስሎ አይታየኝም፡፡ የርሃብ አለንጋ የተዘጋጀልን መሆኑም በርቀትይታያል፡፡ ከፊት ለፊታችን የተደቀኑ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በማሳየት መጪውን ጊዜ አብረን እንይ፡፡ ከኢኮኖሚው እንጀምር፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት (ማለትም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ) በሀገራችን ከጫፍ እስከ ጫፍ አለመረጋጋት ነበር፡፡ ሁከት ነበር፡፡ መንገድ መዝጋት፣ ንብረት ማውደም፣ ሰው መግደል… በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የኢንቨስትመንት አዝመራ ጭምር በእሳት ጋይቷል፡፡ ፋብሪካዎች ተቃጥለዋል፡፡ ትኩስ የሥራ ኃይል የሆነው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ለተቃውሞ ወደ ጎዳና በመውጣቱ ሥራ አልተሰማራም፡፡በዚህም ምክንያት የአርሶ አደሩ ማሳ ጦሙን ማደሩ ታይቷል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ኢኮኖሚውን ክፉኛ አድቅቆታል፡፡ የዋጋ ንረቱን አባብሶታል፡፡
በከተሞች ብዙ የስራ እድል ፈጥረው የነበሩ የመንገድ ፕሮጄክት፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጄክት፣ የኮንዶሚንየም ቤቶች ግንባታ ፕሮጄክት ከሞላ ጎደል ቁመዋል፡፡ አዳዲስ የመንግስት ግንባታዎች ተገትተዋል፡፡ በሀገሪቱ የነበሩ ኢንቨስትመንቶች ባለፉት 5 ዓመታት እየተዳከሙ መጥተዋል፡፡ ብዙዎቹ በሰላም መታጣት ምክንያት ተዘግተዋል፡፡ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ቢሯቸውን ዘግተው ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ሁኔታው ሲረጋጋ ቢመለሱ እንኳ የወደመውን ንብረታቸውን አስልቶ መንግስት ካሳ እንዲከፍላቸው ከመጠየቅ በዘለለ ደግመው ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡ አይመስሉም፡፡ ቢገቡም ቀጥታ ወደ ምርት ማምረት ሳይሆን የተቃጠለን መልሶ በማቋቋም ላይ እንደሚያተኩሩ የሚጠበቅ ነው፡፡
በያዝነው ዓመት ሀገራዊ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በግሌ ይህ ምርጫ ሰማንያ በመቶ አይካሄድም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ፡፡ ከተካሄደ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፖለቲከኞች የሚፈጥሩት ግለት የህዝብን ስሜት ከመለኪያ በላይ ያወጣዋል፡፡ በዚህም መዋከብ ምክንያት መደበኛ ስራ መስራት የምንችልበት ሁኔታ የሚኖር መስሎ አይታየኝም፡፡ ምርጫው ካልተካሄደም ሌላ አጣብቂኝ የፖለቲካ ሁኔታ ይከሰታል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይኸውም፡- ፓርላማው የስራ ዘመኑን ይጨርሳል፡፡ እናም ምርጫው እስኪፈጸም የሽግግር መንግስት ይቋቋማል ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ የሽግግሩ ጊዜ በእነማን ይቋቋም? የሽግግሩ አባላት እነማንን ያካትት? በምን መስፈርት ይመረጡ? የሽግግሩ ዘመን ስንት ዓመት ይሁን? በሽግግሩ ጊዜ ምን ይሰራ? ህገ መንግስቱ በሽግግሩ ጊዜ ይሻሻል?... የሚሉ በርካታ ፈታኝ ጥያቄዎች ፊት ለፊታችን ተደቅነዋል፡፡ ፖለቲከኞቹ በነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ሰፊ ንትርክ እንደሚያደርጉ የሚገመት ነው፡፡ ሶሻል ሜዲያውና አክቲቪስቶች ይህንን ንትርክ በስፋት በማራገብ ህዝቡን እንደሚያንገላቱት የሚጠበቅ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መደበኛ ስራ የሚሰራበት ሁኔታ አይኖርም ብየ አስባለሁ::
መደበኛ ስራ ካልተሰራ፣ ምርት ካልተመረተ፣ ፋብሪካዎች ካልተንቀሳቀሱ፣ ኢንቨስትመንቶች ካልተስፋፉ የደቀቀው ኢኮኖሚ ይብስ ይደቃል:: ወደ ገበያ የሚወጣ ምርት አይኖርም፡፡ ከእሳት፣ ከጎርፍና ከአንበጣ መንጋ ተርፋ የተሰበሰበች ምርት እንኳን ወደ ገበያ ልትቀርብ አርሶ አደሩን መመገብ የምትችል መስላ አትታየኝም:: በፖለቲከኞች ውዝግብ የሚታመሰውና በሶሻል ሜዲያ የሚላጋው ከተሜ ለእለት ጉርሱ የሚሸምተው እህል ገበያ ላይ ስለማግኘቱ አላህ ይወቅ፡፡ የርሃብ አለንጋ በያንዳንዳችን ቤት ግድግዳ ላይ ተሰቅላ ትታየኛለች የምለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ዛሬ ብዕሬ ጨለምተኛ ሃሳብ መክተቧ ያልተለመደ ነው፡፡ ምንም ማድረግ አንችልም:: ከፊት ለፊታችን ድቅድቅ ጨለማ መኖሩ ነብይነትን የሚጠይቅ አይደለም፡፡“ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል” የሚለውን ብሂል እያስተጋባን በተስፋ መጠበቅ ትርጉም የሚኖረው ነገሮችን ቀድመን አስተውለን አንዳንድ ሁኔታዎችን ከወዲሁ ማስተካከል ከቻልን ብቻ ነው፡፡
    ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.Error! Hyperlink reference not valid.ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 9351 times