Saturday, 09 November 2019 11:51

መልዕክቶቻችሁ

Written by  ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
Rate this item
(2 votes)

    ለገዥው መደብ ፅንፈኛ ልሂቃን ጥሪ!
                        
         በይቅርታ እንሻገር፥ በፍቅር እንደመር ለሚለው ወንድማችሁ ውጋት እየሆናችሁ፥ ዛሬ ላይ ሰው እንደ እንስሳ ሲጨክን እንድናይ ሆኗል:: አሁንም እየተሰበሰባችሁ “የኦሮሞ አንድነት” እያላችሁ ለይስሙላ አስሬ ከምትፈራረሙና ልባችንን ከምታደርቁ፥ “የኢትዮጵያ አንድነት” ብላችሁ የአኖሌን የጡት መቁረጥ የጠብ ሃውልት ለፍቅር ስትሉ በማፍረስ አቃፊ ለመሆን ዳዴ በሉ። ያኔ ኦሮሞ ይከብራል፥ በመልካም ስምና ፍትሃዊነት እንደ ማንነቱ ይገዛል።  የተጨቆነው ደጉ የኦሮሞ ሕዝብ አሁን በመንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ ሲገዛ፥ ተፈውሶ ፈውስን ለመላው ኢትዮጵያ ሊያመጣ አምላኩን የሚፈራ ሆኖ ሳለ፥ እናንተ በአስተሳሰባችሁ ገና ነፃ ስላልወጣችሁ፥ ትላንት በረከት ሆናችሁ፥ ዛሬ ወደ መርገምነት ተቀይራችኋልና፥ አንገታችሁን ማደንደን ትታችሁ ተመለሱ።
ኢትዮጵያን ስትበትኑ ኦሮሞን እንደምትበትኑ  እወቁ፡፡ የሚገዛ በመጀመሪያ አቃፊ መሆን አለበት። ከኦሮሞ የተገኘው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሲሰበስብ፣ እናንተ ከስር ከስሩ ትበትናላችሁ። እሱ ሲተክል፣ ትነቅላላችሁ። ኦሮሞ መንገሱን ሳይሆን የፈለጋችሁት፥ እናንተ ራሳችሁ መንገስ ነውን? ኢትዮጵያን ስታደሙ፥ ትልቁን የኦሮሞን ሕዝብ ስም ከመቸውም ጊዜ የበለጠ እያደማችሁ መሆኑን እንዳትዘነጉ:: ወገናዊነትን እያቀነቀናችሁ ዛሬን አታላችሁ ትኖሩ ይሆናል፥ ግን ነገ የታሪክ ጥላሸት ሆናችሁ እንዳትቀሩ እሰጋለሁ፡፡
አሁንም ጊዜ ሳያልፍ የኦሮሞ መፍትሄ ሁኑ።  እንዴት ብትሉ፣ ሽማግሌ በመሆን ነው። እናንተን ለመመለስ ወደ እናንተ የሚቀርብ ተስፋ የማይቆርጥ፣ እንደ እኔ ያለ ጉደኛ ብቻ ነው። ምክንያቱም እናንተ እርቅ ሳይሆን ጠብ አትራፊ ንግድ ሆኖላችኋልና፡፡ ግን ይህ ንግድ መጨረሻው በኦሮሞ ሕዝብ መተፋት ነውና፣ በጊዜ ነቅታችሁ ሽማግሌ ሁኑ። ሽማግሌ ስትሆኑ በመጀመሪያ እናንተ ራሳችሁ በአጭር የንግስና ዘመናችሁ፣ ክፉ ዘር በመዝራታችሁ፣ በምድራችን ስለታየው ሰቆቃ ይቅርታ ጠይቁ። ከዚያ በድሮው የገዥ መደብ ሥር ተበደልን ስለምትሉት ሁሉ፥ እኛ በሕይወት ያለነው በሞቱት ፈንታ ቆመን ይቅርታ እንጠያየቃለን።   
የኢትዮጵያ መዳን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው!

Read 1199 times